
ዜና ሐተታ
የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ለኢኮኖሚው ማህበረሰብ አገልግሎት ለመስጠትና መብታቸውን ለማስጠበቅ ጥር 9 ቀን 1999 ዓ.ም ተመሠረተ። ምርትና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ እና በሀገር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተደራሽ ለማድረግ የንግዱን ዘርፍ ማህበረሰብ ልምድ ማለዋወጥ አስፈለገው። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በተለያዩ ከተሞች የንግዱን ዘርፍ ማህበረሰብ ልምድ ያለዋውጣል፤ ከመንግሥት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ያደርጋል።
የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት 13ኛውን ዙር ፕሮግራም ከሸገር ከተማ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ጋር በመተባበር ባለፈው ቅዳሜ በሱሉልታ ከተማ ውይይት እና የልምድ ልውጥጥ አድርጓል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት እና በንግድ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ አበበ ተስፋዓለም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የልምድ ልውውጥ መደረጉ የንግዱ ማህበረሰብ እርስ በእርስ እንዲተዋወቅ ያደርጋል፤ የአንዱን አካባቢ የአሠራር ባህል ለማወቅ እና የየአካባቢውን የንግድ ባህሪ ለማወቅ ያግዛል። የንግዱ ማህበረሰብ እርስ በርሱ መተዋወቁና መከባበሩ ለመንግሥት አሠራርም ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል፤ ነጋዴው ሲመካከርና ልምድ ሲለዋወጥ ለደላላ እና ለሕገ ወጥ አጭበርባሪዎች አይዳረግም ብለዋል።
‹‹የልምድ ልውውጡ በኦሮሚያ ውስጥ የሚገኙ ሀብቶች እንዲተዋወቁ ያደርጋል›› ያሉት አቶ አበበ፤ ዘመኑ የቴክኖሎጂ ስለሆነ ገበያን ዓለም አቀፍ ማድረግ ይቻላል። የልምድ ልውውጡም በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች መደረግ እንደሚገባው ይመክራሉ።
የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሚገኙ የንግዱን ማህበረሰብ መጋበዙን አመስግነው፤ ይህ አሠራር በሁሉም ክልሎች ልምድ መሆን አለበት ነው ያሉት።
ሌላኛው ተሳታፊ አቶ ጫኔ ቢተው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ የንግዱን ማህበረሰብ ልምድ ማለዋወጥ እና ከመንግሥት አካላት ጋር መመካከር የሀገሪቱ ንግድ ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን ያደርጋል። የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብ እንዲህ አይነት ዕድል ሳያገኝ በመቆየቱ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የንግድ እንቅስቃሴ ለመፍጠር አዳጋች ሆኖ ቆይቷል። የልምድ ልውውጥ እና ምክክር መደረጉ ግን በአደረጃጀት እና በቴክኖሎጂ የተዋቀረ እንዲሆን ያግዛል ብለዋል።
‹‹የንግዱ ማህበረሰብ ከመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር ምክክር ማድረጉ ያሉበትን ችግሮች ለማስተካከል ያግዛል›› ያሉት አቶ ጫኔ፤ ምክክሩ የንግዱን ማህበረሰብ እና መንግሥትን በማቀራረብ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ይላሉ።
የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰብስብ አባፊራ አባጆቢር እንደገለጹት፤ የልምድ ልውውጡ እና ምክክሩ ምክር ቤቶች ብቁ ሥልጠና መስጠት እንዲችሉ ያደርጋል። የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች የንግዱ ማህበረሰብ መብት ላይ እንዲሠሩ፣ የአባላትን አቅም እንዲያሳድጉ የንግዱ ዘርፍ ለሀገር ኢኮኖሚ ጠንካራ እንዲሆን ያደርጋል። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ሲደረግ በቆየው የልምድ ለውውጥም ልምድ ተገኝቶበት የንግዱ እንቅስቃሴ ዘመናዊ እንዲሆን አድርጓል። በኦሮሚያ የሚገኙ የንግዱን ማህበረሰብ አስተዋውቋል፤ የክልሉ የንግድ እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል።
‹‹የልምድ ለውውጡ በመላው ሀገራችን ያሉትን የንግድ ዘርፎች የሚያቀራርብ ነው›› ያሉት አቶ ሰብስብ፤ የንግዱ ዘርፍ መጠናከርና መመካከር አልሚዎችን ወደ ሸገር ከተማ እና ወደ ሌሎች የኦሮሚያ ከተሞች ለመሳብ ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ። ይህም በአንድ ክልል ብቻ የሚሠራ ሳይሆን ከመላው ሀገሪቱ ባለድርሻ አካላት ጋር የሚሠራ ስለሆነ የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በቀጣይ በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ አካባቢዎች የልምድ ልውውጥ ያካሂዳል ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ(ዶ/ር) በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ በዚህ ዘመን በዓለም ላይ የሚካሄድ የንግድ እንቅስቃሴ በዕሴት ሰንሰለት እና በንግድ ትስስር የተቃኘ ነው። ሀገራት በዚህ ትስስር የቆዬ ታሪክ አላቸው። ድንበር ተሻጋሪ ግንኙነት ከሚደረግባቸው ጉዳዮች አንዱ ንግድ ነው። የኦሮሚያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በንግዱ ማህበረሰብ የልምድ ልውውጥ እና ምክክር ማድረጉ ሀገር አቀፍ እና ዓለም አቀፍ ሁኔታን የሚያጠናክር ነው። የንግዱን ማህበረሰብ ልምድ መለዋወጥና መመካከር በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ሲሉ ገልጸዋል።
‹‹የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች የግሉ ዘርፍ ልማት የጀርባ አጥንት፣ የንግዱ ማህበረሰብ ድምጽ እና በመንግሥት ፖሊሲና ትግበራ መካከል አገናኝ ድልድይ ናቸው›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ ለንግድ ተስማሚ ማሻሻያዎችን በመደገፍ የአነስተኛና ጥቃቅን ኢንዱስትሪዎችን ተወዳዳሪ የሚያደርጉ ናቸው ብለዋል። እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ለውጥ ለማምጣት የንግዱን ማህበረሰብ ሚና መለየትና ማጠናከር ያስፈልጋል። በዚሁ መሠረት በለውጡ መንግሥት ወቅቱን የሚመለከቱ የፖሊሲ አመራጮችን በመቅረጽ የንግድን ስብራት ለመጠገን የሚያስችሉ ርምጃዎች ተወስደዋል። በተወሰዱ ርምጃዎችም ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ በተደረጉ የንግድና ኢንቨስትመንት የፖሊሲና የንግድ ማሕቀፍ ማሻሻያዎች ለውጭ ባለሀብቶች ዝግ ሆነው የቆዩት የወጪ፣ የገቢ፣ የጅምላ እና የችርቻሮ የንግድ መስኮች ክፍት ተደርገዋል። ይህም ዘርፉን የውድድር በማድረግ ሀገራዊ ተጠቃሚነትን ከፍ ያደርጋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የንግድ እውቀቶችን በሀገር ውስጥ አስማምቶ ለማልማት የሚያስችል አማራጭ ነው። የሀገር ውስጥ አቅምን በመጠቀም የሀገር ውስጥ ሀብቶችን ለዓለም ገበያ ተደራሽ እንደሚያደርግም ይገልጻሉ።
‹‹መንግሥት ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተቀናጀ ሂደት ላይ ይገኛል›› ያሉት ሚኒስትሩ፤ በሀገር ውስጥ የንግድ ዘርፍ መሠረታዊ ለውጥ ካመጡ የለውጥ ሥራዎች አምራቹን እና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙት የቅዳሜ እና የእሁድ ገበያዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል። ይህም በአቅርቦትና ፍላጎት መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት የተመጣጠነ እንዲሆን አድርጓል ።
መንግሥት ኢትዮጵያ ከዓለም ገበያ የሚገባትን እንድታገኝ እየሠራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ለዚህ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና መሥራች አባል እንደመሆኗ በቅርቡ የሙከራ ንግድ ትጀምራለች ብለዋል። ለዚህም የንግዱ ማህበረሰብ ተወዳዳሪ እንዲሆን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ሲያካሂድ ቆይቷል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ የንግዱ ማህበረሰብ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ ለመሆን ግንዛቤ ከሚያገኝባቸው መድረኮች አንዱ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቶች መድረክ ነው። የዓለም የንግድ ሥርዓት ከልማዳዊ አሠራር ወጥቶ ዲጂታል እየሆነ ስለመጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስቀመጡት አቅጣጫ መሠረት ኢ-ንግድ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጠዋል። ለዚህም መንግሥት ከንግድና ዘርፍ ማህበራት ጋር በቅርበት እንደሚሠራና ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ ቀነኒሳ ለሚ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በነበረው ልማዳዊ አስተሳሰብ ንግድ ማለት ፉክክር የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ዘመን ግን የሚጠይቀው ውድድር ነው። ለዚህም የንግዱን ማህበረሰብ ማስተዋወቅና አብሮ እንዲሠራ ማድረግ ያስፈልጋል።
የሀገራት ኢኮኖሚ በከፍተኛ አቅም የሚደገፈው በግሉ ዘርፍ ስለሆነ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የለውጡ አካል በመሆን ዘርፉን ለማጠናከር በመላው ሀገሪቱ ይሠራል ብለዋል። በዚህ ዘመን ንግድን የሚመራው ዓለም አቀፍ ሕግ ስለሆነ የንግዱ ማህበረሰብ የሚገፋፉበት ሳይሆን የሚደጋገፉበትና ለዓለም ገበያ የሚወዳደሩበት መሆን እንዳለበት አመልክተዋል።
በዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም