
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥራና ክህሎት ቢሮ 996 አባላትን ያቀፉ 87 የተርሚናል ኢንተርፕራይዞችን አስመርቆ ወደ ሥራ ማሰማራቱን ገለፀ።
በምክትል ከንቲባ ማእረግ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ እንደገለፁት፤ ዜጎች ፍትሐዊ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል እና በከተማችን ያሉ ሴቶች እና ወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው በዚህ ዓመት ከተያዘው ዕቅድ መካከል የተርሚናል ኢንተርፕራይዝ አንዱ ነው።
በተርሚናል አገልግሎቶች በፓርኪንግ እና ሌሎች መሰል የሥራ እድል የሚፈጥሩ የአገልግሎት ዘርፎች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በተርሚናል አገልግሎቱ ወጣቶች እና ሴቶችን በማደራጀት ሥራ ማስጀመር ያስፈለገበት ዋና ዓላማ የከተማችንን ነዋሪዎች ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ነው ሲሉ ተናግረዋል።
እነዚህ መሠረተ ልማቶችም አሠራርን ከማዘመን እና የህብረተሰቡን ጥያቄ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር ከብልሹ አሠራር የፀዳ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል።
አገልግሎት የሚሰጡት ሰዎች የሠለጠኑ እና ለማገልገል የተዘጋጁ፤ የሕዝቡን እንግልት ለመቀነስ የሚተጉ እና የተደራጀ መሆን እንደሚገባቸው አመልክተው፤ በተለይም አዛውንቶችን፣ ሴቶችን እና አቅመ ደካሞችን በአገልጋይነት ስሜት ለማስተናገድ እንዲቻል የሠለጠነ የሰው ሃይል የተሟላላቸው የልማት ሥራዎችን መሥራት ችለናል ሲሉ ተናግረዋል።
በተርሚናሎች የሚከናወን ክፍያ ዲጂታላይዝ መሆናቸው ፤ ኢንተርፕራይዞችም በሚሠማሩበት ቦታ ላይ ወንጀል ለመከላከል የሚያስችል ሥልጠና መውሰዳቸው መሠረታዊ ጉዳይ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከፀጥታ አስተዳደር መዋቅሮች ጋር በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ ተርሚናሎቹ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር የከተማዋ የልማት እና የፀጥታ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ኃላፊነትን የሚወጡባቸው ናቸው ብለዋል፤ ከዚህ ቀደም በዘርፉ ላይ የሚስተዋሉ የስርቆት እና የሥነ ምግባር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ እንደሆኑም አመልክተዋል።
ሁሉን አቀፍ አገልግሎት በመስጠት ሕዝቡ በተርሚናሎች እና መኪና ማቆሚያዎች በአግባቡ ተጠቃሚ እንዲሆን በሥነ-ምግባር የታነጹና እና የተደራጁ አገልጋዮች እንዲኖሩ ዋነኛ ትኩረታችን ነው ያሉት ኃላፊዋ፤ በተለይ በአካባቢው ወንጀሎች ቢፈፀሙ በምን መልኩ ማጋለጥ እንዳለባቸው እንዲሁም የሥራ ቦታው ደህንነቱ የተጠበቀ እንዲሆን ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር አብረው የሚሠሩበት ሁኔታ እንዳለ ጠቁመው፤ ለቀጣይም ሥልጠና ይሰጣል ሲሉ ገልፀዋል።
ኢንተርፕራይዞቹ ከዚህ ቀደም የነበሩ ወንጀልን የመከላከል ውስንነቶችን በመቅረፍ የፀጥታና የደህንነት ሥራዎችን በማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
በሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም