
አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ስድት ዓመታት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር 40 በመቶ የደን ሽፋንን ለመጨመር የሚያስችል ሥራ መሠራቱ ተገለፀ። በተያዘው ዓመት በክረምቱ ለሚከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ወደ 5.2 ቢሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውም ተጠቁሟል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የደን ልማትና እንክብካቤ ዳይሬክተር አቶ ከተማ አብዲሳ በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ባለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ የተሠሩ ሥራዎችንና የዚህን በጀት ዓመት እቅድ አስመልክተው ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ባለፉት ስድስት ዓመታት በክልሉ የተለያየ ጠቀሜታ ያላቸውና ወደ 40 በመቶ የደን ሽፋንን መጨመር የሚያስችሉ ወደ 23 ቢሊዮን ችግኞች ተተክለዋል። በችግኝ የሚሸፈነው መሬት ከዘጠኝ ሚሊዮን ሄክታር ወደ 11 ሚሊዮን ሄክታር ከፍ ብሏል።
ከአፈርና ውሃ ጥበቃ ጋር በተያያዘ በየዓመቱ የተራቆቱ ተራራማ አካባቢዎችን በደን ማልበስ ሥራዎች መከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎችን እያስገኘ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ከተማ፤ የክልሉ የደን ሽፋን ከነበረበት 17 በመቶ፤ ወደ 19 በመቶ ከፍ ማለቱን አመልክተዋል። ለምግብ ዋስትና የሚውሉ ምርቶችን ማምረት መቻሉንና እንዲሁም የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ ከደን ጋር ተያያዥነት ያላቸው እንደ ንብ ማነብ፣ ከብት ማድለብ ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት ዕድል መፍጠሩንና በዚህም በሺዎች ለሚቆጠሩ ወጣቶችና ሴቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል።
እንዲህ ያለውን ውጤት ማስመዝገብ የተቻለው የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ፤ አርሶአደሩና አርብቶአደሩ በእርሻ ማሳው ላይ ከሚያከናውነው ጋር እየተመጋገበ በመከናወኑ እንደሆነ እንዲሁም አረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር በ2011ዓ.ም ሲጀመር የተስተዋሉ ክፍተቶችን ፈጥኖ የማስተካከያ ርምጃ በመውሰድ ጭምር መሆኑን ገልፀዋል።
በተወሰዱ የማስተካከያ ርምጃዎችም፤ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ የሆኑ የዛፍ ችግኞችን መምረጥና እንክብካቤንም በመጨመር ሰፊ ሥራ መሥራቱን የጠቀሱት አቶ ከተማ፤ በአንዳንድ አካባቢ የተከናወነው የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤ የላቀ ሆኖ መገኘቱን ገልፀዋል።
ጥሩ ተሞክሮ ያላቸውን ወደኋላ ለቀሩት መልካም ተሞክሮ እንዲሆኑ በማድረግ ሌሎችንም በማነቃቃት ሥራዎች መሠራታቸውን ጠቅሰዋል። በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ችግኞችን በማዘጋጀት፣ በተከላው በመሳተፍ፣ የራሱ ሥራ አድርጎ በመንቀሳቀስ፣ ማህበረሰቡ ትልቁን ድርሻ እንደሚይዝም ጠቁመዋል።
አቶ ከተማ አያይዘውም የ2017 ዓ.ም የችግኝ ተከላ መርሃግብር ዝግጅትን በተመለከተ እንደገለጹት፤ በክረምቱ ወደ ወደ 5.2 ቢሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል። ከተዘጋጁት ችግኞች ወደ አምስት መቶሺህ የሚሆኑት ለምግብነት የሚውሉ ችግኞች ናቸው። በዚህ የዝግጅት ምዕራፍም እንደየአካባቢው የአየር ፀባይ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ተገብቷል።
ለችግኝ ተከላው የአየር ፀባያቸው ምቹ በሆነባቸው የክልሉ አራት ዞኖች ውስጥ የችግኝ ተከላው እየተከናወነ መሆኑንና እስካሁን ከተዘጋጁት ችግኞች ወደ 137 ሚሊዮን ችግኞች መተከላቸውን አቶ ከተማ ገልፀዋል። ክረምቱ እየገፋና በቂ እርጥበታማ የአየርፀባይ ሲኖር ፈጥኖ ችግኞቹን ለመትከል የጉድጓድ ቁፋሮ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል። ከባለፉት ዓመታት የተሻለ አፈጻፀም በማስመዝገብ የደን ሽፋኑን የበለጠ ለመጨመር፣ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ ጎን ለጎን እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።
በለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም