‹‹መሶብ›› በሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አዲስ ለውጥ አምጥቷል

አዲስ አበባ፦ ‹‹መሶብ›› የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከወረቀት ነጻ የዲጂታል አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አዲስ ለውጥ ያመጣ ነው ሲሉ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀሚድ ኪኒሶ ገለጹ።

አቶ ሀሚድ ኪኒሶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት 12 ተቋማት እና 41 የፌዴራል አገልግሎቶች የተካተቱበት ነው። ክፍያን ጨምሮ ሙሉ ለሙሉ ከወረቀት ነጻ የዲጂታል አገልግሎት ይሰጥበታል። በማዕከሉ አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ውስጥ የፌዴራል ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት ተጠቃሽ ነው ብለዋል።

ተቋሙ አሠራሮቹን ቀደም ብሎ ዲጂታላይዝ ማድረግ በመጀመሩ በቀላሉ ከማዕከሉ ዓላማ ጋር መጣጣም መቻሉን የገለጹት አቶ ሀሚድ፤ በዚህም ተቋሙ ውክልና፣ ኪራይ፣ ብድር፣ ሽያጭና የውጭ ጉዳይ አገልግሎትን ጨምሮ ስድስት አገልግሎቶችን በማዕከሉ አገልግሎት እንዲሰጡ አድርጓል ብለዋል።

‹‹መሶብ›› የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከወረቀት ነጻ የዲጂታል አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑ የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ አዲስ ለውጥ ያመጣ ነው ያሉት አቶ ሀሚድ፤ በቀጣይም ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶችን በማዕከሉ ለማካተት እየተሠራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ ተቋሙ አደረጃጀቱን እና አሠራሩን በማዘመን ለተገልጋዮች ቀልጣፋና ተደራሽነት ያለው አገልግሎት በመስጠት ላይ ነው። በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ600 ሺህ በላይ ጉዳዮችን በኦንላይን አገልግሎት መስጠት ችሏል። ይህም ከጠቅላላ አገልግሎቶች ከ80 ከመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ ይሸፍናል። በዚህም ባለጉዳይ የሚፈልገውን አገልግሎት በኦንላይ አጠናቆ መሄድ የሚችልበት ሥርዓት ተፈጥሯል።

ተቋሙ በ2017 በጀት ዓመት በሶስተኛ ሩብ ዓመት 684 ሺህ 580 ሰነዶችን አረጋግጦ መዝግቧል። በዚህም ከቴምብር ቀረጥና ከአገልግሎት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ሰብስቧል። የአገልግሎት ክፍያዎቹ የሚፈጸሙት በቴሌ ብር፣ በሲቢኢ ብር እና በሞባይል ባንኪንግ የክፍያ ሥርዓት መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግሥት በቅርቡ ‹‹መሶብ ›› የተሰኘ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫን ወደ ሥራ ማስገባቱ ይታወሳል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወይዘሮ አለምፀሐይ ጳውሎስ ይህ ማዕከል ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ ላለው ከፍተኛ ችግር እንደ መፍትሔ የቀረበ መሆኑን ገልጸዋል።

በማዕከሉ አሁን ላይ በፌዴራል ደረጃ በዲጂታል ከሚሰጡ ከ800 በላይ አገልግሎቶች መካከል 41 አገልግሎቶችን ለይቶ ወደ ሥራ ገብቷል። በቅርቡ ተጨማሪ 11 አገልግሎቶች ወደዚሁ ሥርዓት እንደሚገቡ ተገልጿል።

በሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You