
አሰላ፡- በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ ፍሳሽ ቆሻሻን ወደ ንጹህ ውሃ የሚቀይር ማጣሪያ በ185 ሚሊዮን ብር እየተገነባ መሆኑን የአሰላ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።
የከተማዋ ምክትል ከንቲባ አቶ አብዱላሂ ሃሙ የሚዲያ አመራሮችና ጋዜጠኞች በከተማዋ እየተገነባ ያለውን ፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ በጎበኙበት ወቅት እንዳስታወቁት ፤ በ185 ሚሊዮን ብር ወጪ በፌዴራል መንግሥትና በክልሉ መንግሥት ድጋፍ ማጣሪያው እየተገነባ ነው።
ማጣሪያ ከኮሪዶር ልማቱ ጋር ተዳምሮ አሰላ ከተማን ንጹህ ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ እንድትሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ያሉት ምክትል ከንቲባው ፤ በአሁኑ ሰዓት ግንባታው 60 በመቶ መድረሱን ጠቁመዋል ። ፕሮጀክቱ በስድስት ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን ፤ የመሬቱ ባለቤት ለነበሩ አርሶ አደሮችም የ35 ሚሊዮን ብር ካሳ ተከፍሎ ወደ ሥራ እንደተገባ አመልክተዋል።
የሥራ ሂደቱ ሁለት ምዕራፎች እንዳሉት የገለጹት ምክትል ከንቲባው ፤ የመጀመሪያው ምዕራፍ ማጣሪያውን ሠርቶ በማጠናቀቅ ፍሳሽ ቆሻሻን ከየቤቱ እና ከየድርጅቱ በቦቴ እየወሰዱ እንዲጣራ ማድረግ መሆኑን ጠቁመዋል። በሁለተኛው ምዕራፍ ቦቴውን ሊተካ በሚችል ሁኔታ የከተማውን ፍሳሽ ቆሻሻ ከያለበት ቦታ በቱቦ ወደ ማጣሪያው የመውሰድ ሥራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሚጣራው ንጹህ ውሃ ለመስኖ እና አረንጓዴ ልማት ማገልገል እንደሚችል አስረድተው፤ ይህም የከተማ ግብርናን ለማስፋፋት የራሱን አስተዋጽኦ ይኖረዋል ብለዋል። አርሶ አደሮችን በማነጋገር ቦታ የማዘጋጀቱ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ፤ በከተማው የሚገኘው አደጋ ስጋት መከላከል ቢሮ የመስኖ ሥራ ለማከናወን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የከተማዋ ቆሻሻ በከተማዋ ዳርቻ በተለምዶ ቆሼ ሜዳ በሚባል አካባቢ እንደሚጣል ገልጸው፤ የቆሻሻ ማስወገጃዎቹ ሥራ ሲጀምሩ ከጽዳት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ችግሮች እንደሚቃለሉና የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱ የተሻለ እንደሚሆን አመልክተዋል። ፍሳሽ ቆሻሻው ሲጣራ የሚቀረው ዝቃጭ ወይም ደረቅ ክፍልም ማዳበሪያ ሆኖ የሚያገለግል ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
አሰላ ከተማ በጭላሎ ተራራ አቅፍ ውስጥ ያለች እንደመሆኗ፤ በደንብ ከተሠራ ከተማዋን አረንጓዴ፣ ንጹህ፣ ውብና ለኑሮ ምቹ ለማድረግ የቆሻሻ ማስወገጃዎቹ አስተዋጿቸው ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸው፤ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት እንዲይዝ መደረጉ በከተማዋ እየተሠራ ያለውን የኮሪዶር ልማት የሚደግፍ ስለመሆኑም አስታውቀዋል።
በቀጣይ ደረቅ ቆሻሻን ማስወገድ የሚችል ፕሮጀክት ለመጀመር የዲዛይን ሥራ ተሠርቶ ፤ ለግንባታው የሚያስፈልገውን በሀብት የማፈላለግ ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
በኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 28 ቀን 2017 ዓ.ም