
በሕዝብ ስም እየተማለ በሀገር ላይ የሚፈጸም የጥፋት ተልዕኮ ለሀገራችን እንግዳ አይደለም። ብዙ ዋጋ ያስከፈለን እና ዛሬም እያስከፈለን ያለ ትልቁ የፖለቲካ ስብራታችንም ነው። ዘመናትን ያስቆጠረው የግጭት ታሪካችን እና ከዚህ ለመውጣት የምናደርገው ጥረት እያስከፈለን ያለው ያልተገባ ዋጋ የዚሁ እውነታ አንዱ መገለጫ ነው።
ከዘመነ መሳፍንት ጀምሮ ያለውን እንኳን ብንመለከት የሀገሪቱ ፖለቲካ በዘመኑ በነበሩ የየጎጡ ጉልበተኞች በጎፈቃድ ላይ የተመሠረተ፤ ይሄዱበት የነበረው የፖለቲካ መንገድም ኃይልን መሠረት ያደረገ፤ አሸንፎ እየፎከሩ መግዛትን፤ ተሸንፎ አንገት ደፍቶ መገዛትን የሚጠይቅ ነበር። ይህም እንደ ሀገር ለዘመናት ልንወጣው ያልቻልነው የግጭት አዙሪት ውስጥ የጨመረን የፖለቲካ ስብራታችን ነው። የብዙ ንፁሐንን ሕይወትም ነጥቆናል።
በዘመኑ የነበሩ የየጎጡ ጉልበተኞች በጎጡ ያለውን ሕዝብ የራሳቸው ፈቃድ መገልገያ ዕቃ አድርገው ከማየታቸው የተነሳም፤ በሆነው ባልሆነው፣ በኃይል አሰላለፍ ስሌት ስህተት፣ በውሸት እና የቀልድ ትርክት እና አዝማሪ በሚፈጥረው ሞቅታ ሕዝቡን ብረት አሸክመው ባልተገባ እና በማይጨበጥ ተስፋ ወደ ሞት የመንዳታቸው እውነታ የተለመደ ነው።
ይህ የዚያ ዘመን የፖለቲካ ትርክት ዋንኛ መገለጫ ነው። በዚህም ምክንያት በተፈጠሩ ግጭቶች፣ ሀገር እንደሀገር ለከፋ ጥፋት እና ውድመት ተዳርጋለች። እንደ ሕዝብ መታደስን የሚያመጣ የሰላም፣ የመረጋጋት እና የስክነት ዘመን መፍጠር ሳንችል መቶ ዓመታትን በተመሳሳይ የግጭት አዙሪት ውስጥ ለማለፍ ተገድደናል።
እያንዳንዱ የግጭት ትርክት በራሱ ያለ እና የነበረ የትውልዶችን ተፈጥሯዊ የመነሳት መነቃቃት/የለውጥ መንፈስ እየገደለ፤ ትውልዶች የመሆን መሻታቸውን ተጨባጭ አድርገው ከማየት ይልቅ፤ ከሩቅ አይተውት፤ መልሰው ሊያስቡት በማይችሉበት ግራ መጋባት ውስጥ ኖረው እንዲያልፉ አድርጓቸዋል። ይህም በብዙ ትውልድ ውስጥ ማኅበራዊ ድባቴን ፈጥሯል ።
እውነታው በ19ኛው ክፍለ ዘመንም መልኩን እና ቋንቋውን ቀይሮ በተለያየ ስያሜ እና ቀለም፤ በሕዝብ ስም ራሱን አግዝፎ የዘመኑን ትውልዶች ተፈጥሯዊ የመነሳት መነቃቃትን/ የለውጥ መንፈስ ጠልፎ በመውሰድ ሀገርን በተመሳሳይ የግጭት አዙሪት ውስጥ ከቷል። ሕዝብን አሳንሶ የፖለቲካ ፍላጎቶች ማስፈጸሚያ እቃ አድርጎ ማየት፤ ይህንንም በአደባባይ ሳይቀር በድፍረት መናገር የፖለቲካ ትምክህት የሆነበት እውነታም ተፈጥሮ ቆይቷል ።
በሕዝብ ስም እየማሉ እና እየተገዘቱ፤ በሕዝብ ላይ በአደባባይ ለሚፈጽሟቸው ወንጀሎች እልልታ እና ጭብጨባ የሚጠብቁ፤ ራሳቸውን ጀግና አድርገው፤ እንደ ቀደመው ዘመን በጀግና ጀግና ጫወታ ስተው ትውልድ የሚያስቱ፤ ሕዝብን የፖለቲካ ቁማር መቆመሪያ ካርድ አድርገው ከማየት ባለፈ የራሱ ፈቃድ ያለው ፍጥረታዊ ማንነት እንዳለው ለማሰብ የሚከብዳቸው የስም ነፃ አውጪዎች ጥቂት አይደሉም። እንደሀገር በ21ኛው ክፍለ ዘመን እያስከፈሉን ያለው ዋጋም ከቀደሙት ዘመናት የከፋ ስለመሆኑ ለማሰብ የሚከብድ አይሆንም።
እነዚህ ኃይሎች ለዚህ ሙት እና ትውልድ ገዳይ ሀሳባቸው የትኛውንም አይነት ወንጀል በሕዝብ ስም ለመፈጸም ሁለቴ ለማሰብ የሚገደድ ሕሊና የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ያተርፈናል ወደሚሉት ግጭት ለማግባት የትኛውንም ኃይል ከጎናቸው ለማሰለፍ፤ የትኛውንም ሴራ ለመተግበር ችግር የለባቸውም።
ሚሊዮኖች ቢያልቁ፤ ትምህርት እና የጤና አገልግሎት ቢቋረጥ፣ ትውልድ ያለተስፋ ቢቀር፤ ሀገር ብትፈርስ እነሱ የሚፈልጉትን ርካሽ የፖለቲካ ዓላማ እውን ማድረግ እስካስቻላቸው ድረስ ጉዳያቸው አይደለም። ትውልድ ደም ቢቃባ፤ ምድር አኬልዳማ ብትሆን፤ ለእነርሱ የፍላጎት ስኬት የተከፈለ ዋጋ እስከሆነ ድረስ ጥያቄአቸው አይደለም፤ ለዚህ የሚሆን የደነደነ ልብ እና በራስ ወዳድነት የተገነዘ ማንነት ባለቤት ናቸው። ስለሆነም መፍትሔው እነዚህን በሕዝብ ጠበቃነት እና በነፃ አውጪነት ስም የሚነግዱ የፖለቲካ ቆማሪዎችን እምቢ አንሰማችሁም ማለት እና እኩይ ዓላማቸውን ማክሸፍ ብቻ ይሆናል!
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም