የመልክዓ ምድራዊ አመልካች ጥበቃ ሥርዓት የአምራቾችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ ነው

አዲስ አበባ፡- የመልክዓ ምድራዊ አመልካች ምርቶች ጥበቃ ሥርዓት የአምራቹን ሙሉ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆኑን የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለፀ።

የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በመልክዓ ምድር ጥበቃ ሥርዓት ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ጉባኤ ትናንት ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ የኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ለመሆን የሄደችበት ርቀት እና የዲጂታል ጉዞዋ ወደ ዓለም አቀፉ ሥርዓት እየገባች መሆኑ ማሳያ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ረቂቅ መመሪያ በማዘጋጀት፤ የመልክዓ ምድር ጥበቃ ሥርዓት ለመዘርጋት ወደ ሥራ እየገባች ነው ብለዋል፡፡

የመልክዓ ምድር አመልካች ሥርዓት ከሕግ ማሕቀፍ የበለጠ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የእሴት ሠንሠለት ተዋናዮችን እና የገጠር ማኅበረሰቦችን ለማብቃት እንዲሁም፤ ሐሰተኛ እና ኢ-ፍትሐዊ የሆነ የንግድ ውድድርን ለመከላከል ያስችላል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

የሥርዓቱ መዘርጋት የኢትዮጵያን ምርቶች የገበያ ዋጋ እና የወጪ ንግድ አቅም ለማሳደግ ከመርዳት በተጨማሪ፤ ሸማቾች የምርት ሂደቱን እንዲከታተሉ እና ትክክለኛ የሆነ ምርት አረጋግጠው እንዲገዙ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የአዕምሯዊ ንብረት ጥበቃ ለሀገር ልማት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ፤ አርሶ አደሮች፣ አምራቾች እና ምርቱ የተገኘበት ማኅበረሰብ የምርቱን ልዩ ባሕሪ በማስጠበቅ፤ ፍትሐዊ የገበያ መዳረሻ እንዲያገኙ ዕድል ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከቅርስና ከባህል ጥበቃ አንጻርም፤ በተለያዩ አካባቢዎች እና ክልሎች የተካተቱ ባህላዊ ቅርሶች እና ቁሳቁሶች እንዲጠበቁ የሚያስችል መሆኑን በማመላከት፤ አዕምሯዊ ንብረት ለልማት አስፈላጊ እንደመሆኑ አካታች እና ተፈጻሚ መሆን አለበት ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የዓለም አዕምሯዊ ንብረት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዳረን ታንግ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የመልክዓ ምድር አመልካች ጥበቃ ሥርዓት፤ የአዕምራዊ ንብረት ምዝገባ አካል በመሆን እንደ ሕግ ማሕቀፍ የሚያገለግል ነው፡፡ ሥርዓቱም ለባህል፤ ለግብርና እና ለተፈጥሮ ሀብቶች ጥበቃ በማድረግ የገጠር ልማትን ያጠናክራል፡፡

ይህን ሥርዓት መዘርጋት የሥራ ዕድል በማስፋፋት፣ ኢንቨስትመንትን በመሳብ በማኅበራዊ እና በኢኮኖሚው ዘርፍ ትልቅ ጠቀሜታ ከማበርከቱ ባለፈ፤ ለአምራቹ ማኅበረሰብ ጠንካራ ጥበቃ ያደርጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በተለይም ቡና፣ ማር፣ ጨርቃጨርቅ እና የሌሎች በርካታ የግብርና ምርቶች ባለቤት እንደሆነች ያነሱት ዳሬን ታንግ፤ የመልክዓ ምድር አመላካች ምርቶች ሥርዓት መተግበር ከሚሰጠው ሕጋዊ መብቶች ባለፈ ለዘርፉ እድገት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ምርቶችን ተደራሽና ተመራጭ በማድረግ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ፣ እሴት ለመጨመር እና ዋጋን ለማሳደግ እንደሚያስችል አመልክተው፤ ይህንን ለማሳካት ባለድርሻ አካላት በጋራ በመሥራት ጠንካራ እና ዘላቂ የመልክዓ ምድር ምልከታ ሥርዓት መገንባት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሥርዓቱን እንደ ሀገር ለመዘርጋት እንቅስቃሴ የተጀመረው ከሁለት ዓመት በፊት ሲሆን፤ ረቂቅ መመሪያው ተዘጋጅቶ በተለያዩ አካላት ተገምግሟል፡፡ አጠቃላይ ሥራው ተጠናቆ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ ሥራ እንደሚገባ እና የጉባኤው ዓላማም ለረቂቅ መመሪያው ከዓለም ማኅበረሰብ ግብዓት ለማግኘት ያለመ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You