
-ኢትዮጵያ ታምርት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ከሚያሳዩ ትልሞች መካከል አንዱ መሆኑ ተጠቆመ
ጎንደር፦ የኢትዮጵያ ታምርት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ከሚያሳዩ ትልሞች መካከል አንዱ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ። 3ኛው የኢትዮጵያ ታምርት ክልላዊ የማጠቃለያ ፕሮግራም በጎንደር ከተማ ተካሂዷል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በመርሐ ግብሩ ላይ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ሸማች ብቻ ሳይሆን አምራችም ሸማችም መሆን አለባት። የኢትዮጵያ ታምርት የኢትዮጵያን ማንሰራራት ከሚያሳዩ ትልሞች መካከል አንዱ ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሁሉም የኢንዱስትሪ ምርቶች በስፋትና በጥራት እየተመረቱ ይገኛሉ ያሉት አቶ ተመስገን፤ በንቅናቄው ተሳትፎ ለነበራቸው አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
መድረኩ በጎንደር የተካሄደው የትናንት፣ የዛሬና የነገ ሥልጣኔ መገናኛ የአምራች ኢንዱስትሪ ኮሪዶር እየሆነች መሆኗ ነው ያሉት አቶ ተመስገን፤ ጎንደር እንደሀገር ልዩ ትኩረት በተሰጠው የአምራች ዘርፍ ልማት ላይ በትኩረት እየሠራች መሆኗን ገልጸዋል።
የአማራ ክልል በችግር ጊዜም የልማት አርበኛ ሆኖ ለመቀጠሉ ጎንደር ምስክር ናት ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ጎንደር እንደ አዲስ እየተወለደች፣ እየተሠራች፣ እየፈካች መሆኗን አመልክተዋል። ሕዝቡም ከፍተኛ የልማት ፍላጎት እንዳለውና ከዚህም የሚያደናቅፈውን እንደማይፈልግ ገልጸዋል።
ይህንን ልኳንና መልኳን የኢትዮጵያ መንግሥት ጠንቅቆ ይገነዘባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አኳያ በገበታ ለሀገር ከተሠሩ ሪዞርቶች ውስጥ አንዱ በጎንደር ጎርጎራ እንዲሆን አድርጓል፤ ለዘመናት መሠረታዊ ጥገና አጥቶ የቆየውን የፋሲል ቤተመንግሥት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ አድሷል ሲሉ ጠቅሰዋል።
የጎንደር ከተማ መልክ እንደገና እንዲወጣ ያደረገ የኮሪዶር ልማት እያፋጠነ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ጎንደር ሰላምን በማስጠበቅ እና በማጽናት ልማትን የማስቀጠል፤ ለልማትም የመትጋት ደማቅ ማሳያ ናት ብለዋል።
የክልሉን ሰላም ወደነበረበት ለመመለስ አስተዋፅዖ ላበረከቱ የፌዴራልና የክልል ፀጥታ አካላት በተለይም ደግሞ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ምስጋና አቅርበው፤ መንግሥት አሁንም የሰላም አማራጭ መርጠው ከሚመጡ አካላት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ለመወያየት በሩ ክፍት መሆኑን ገልፀዋል። በተጨማሪም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ የተገነባውን ከአኩሪ አተር ግብዓት በከፊል የተቀነባበረ ዘይት የሚያመርት ቲቲኬ የዘይት ፋብሪካን መርቀው ሥራ አስጀምረዋል።
በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግርም፤ ፋብሪካው እንደሀገር ለጀመርነው የአምራች የኢንዱስትሪ ልማት ሁነኛ ምሳሌ መሆኑን ገልፀዋል።
በ373 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ይህ ፋብሪካ፤ በቀን 120 ቶን የአኩሪ አተር ዱቄት እና በከፊል የተጣራ ዘይት የማምረት አቅም እንዳለው ተጠቁሟል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አረጋ ከበደ በበኩላቸው፤ ክልሉ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ልማት ትሩፋቶችን በማስመዝገብና በኢንዱስትሪ ዘርፍ ያለው ኢንቨስትመንት በማበረታታት ተስፋ ሰጪ ውጤቶች አስመዝግቧል ብለዋል።
ንቅናቄው የዘርፉን ተዋንያን አምራቾችን ከሸማቾች አገናኝቷል፣ መንግሥትና ባለሀብቱን በማገናኘት የኢንዱስትሪ ዘርፉን ዕድገት በማረጋገጥና በማሻሻል በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልፀዋል።
ወደ ውጭ ሀገር የሚላኩትን ሆነ ተኪ ምርቶችን የምርት መጠን በማሳደግ በሥራ ዕድል ፈጠራና የቴክኖሎጂ ሽግግር በማካሄድ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የነበረው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ዘርፉን አሁንም በርካታ ተግዳሮቶች እየተፈታተኑት ያለ እንደመሆኑ ከፍተኛ የመንግሥት ትኩረት ተሰጥቶት መመራት እንደሚገባው የገለፁት ርዕሰ መስተዳደሩ፤ በተለይ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መገንባት አስፈላጊ መሆኑን አብራርተዋል። ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ እንቅፋቶችን ለመፍታት ክልሉ በቁርጠኝነት እንደሚሠራ አመልክተዋል።
በክብረአብ በላቸው
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም