“የሚገነቡት መንደሮች አርሶ አደሩ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ ናቸው”– ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፡- በገጠር ኮሪዶር ሞዴል የሚገነቡት የመኖሪያ መንደሮች አርሶ አደሩ የግብርና ሥራ እያከናወነ የተሻለ ሕይወት እንዲኖር የሚያስችሉ ናቸው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የአርሶ አደሮች የመኖሪያ መንደር ግንባታ ሲጠናቀቅ የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘዬ የሚቀይሩ እና ጤናማ ሕይወትን የሚያላብሱት ናቸው ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አራተኛውን እና የክረምት በጎ ፍቃድ ሥራ አካል የሆነውን የገጠር ኮሪዶር ልማት ሥራ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ስልጤ ዞን ሁልባረግ ወረዳ ወራበት ሻማ ቀበሌ ሞዴል የአርሶ አደሮች የመኖሪያ መንደር ግንባታ አስጀምረዋል።

እነዚህ መኖሪያዎች ተገንብተው ሲጠናቀቁ የአርሶ አደሩን የኑሮ ዘዬ የሚቀይሩ እና ጤናማ ሕይወትን የሚያላብሱት መሆናቸውን በማኅበራዊ ትስስር ገፃቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በዞኑ በነበራቸው ቆይታ የግሉ ዘርፍ በአግሮ ኢንዱስትሪ ላይ ያለውን ተሳትፎ መመልከታቸውንም ጠቁመዋል።

እንደማሳያ አቶት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪን ተዘዋውረን ተመልክተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ እንዲህ ያሉት ሥራዎች በሌማት ትሩፋት ውጤት ለማስመዝገብ የተጀመረውን ተግባር ከግብ ለማድረስ በጎ ጅምሮች በመሆናቸው ሊበረታቱ ይገባል ብለዋል።

በተያያዘም በከተማ የተጀመሩ የክረምት በጎ ፍቃድ ልማት ሥራዎች ከገጠሩ ክፍል ጋር የማስተሳሰር አካል በሆነው የገጠር የኮሪደር ልማት ሥራ እያስጀመርን ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃዲያ ዞን ሌሞ ወረዳ ዱባንቾ ቀበሌ በገጠር ኮሪደር ሞዴል የአርሶ አደሮች መኖሪያ መንደር የማስጀመሪያ መርሐ ግብር መካሄዱንም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የቤት ልማት ፕሮጀክቶችን በሰፊው የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሐግብር አካል አድርገው ከውነዋል። ከአዋሬ አካባቢ ስኬታማ የመኖሪያ ከባቢ የመለወጥ ሥራቸው በመቀጠል መርሐ ግብሩን በመላው ሀገሪቱ አዲስ በተጀመረው የገጠር ኮሪዶር ውጥን አካል አድርገው የዘንድሮውን የበጎ ፈቃድ ሥራ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አስጀምረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቀጥተኛ ድጋፍ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የሚገኙ የሀላባ፣ የከንባታ፣ የሀዲያ እና የስልጤ ዞኖች ሞዴል የሚሆኑ የገጠር ኮሪዶር ሥራዎች ግንባታ ይከናወንላቸዋል። እነዚህ ግንባታዎች በመላው ሀገራችን የገጠሩን ማኅበረሰብ የኑሮ ደረጃ የማሻሻል ዓላማ ያነገቡ ናቸው።

ወጪ ቆጣቢ እና የባሕል እሴትን የጠበቁ በመሆን የሚገነቡት መኖሪያ ቤቶች በዘመናዊነት እና ባህላዊነት መሐከል ሚዛን እንዲጠብቁ ሆነው የታቀዱ መሆናቸው ተጠቁሞ፤ ከተፈጥሮ ከባቢ ጋር መስማማት፣ ዘላቂ እና አቅምን ያገናዘቡ ቁሳቁሶችን መጠቀም፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ውጭ የመሥራት አቅም የሥራዎቹ መልኮች ናቸው ተብሏል።

የውሃ እጥረት መሠረተ ልማት፣ የእንስሳት የተለየ ማቆያ እና የባዮጋዝ ማምረቻ ሥርዓት የገጠር ኮሪዶሩ የዲዛይን ዕቅድ አካል ናቸው። በተጨማሪ በዘላቂ የተፈጥሮ ጥበቃ ኃላፊነት የተደገፉ የምግብ ዋስትና ሥርዓቶችን በአትክልት ማምረቻ ስፍራዎች ማረጋገጥ የሥራው መልክ ይሆናሉ ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መረጃ አመልክቷል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You