የሀገራዊ ምክክሩ ሂደትና መዳረሻው

የዘርፉ ምሁራን እንደሚሉት ሀገራዊ ምክክር በአንድ ሀገር ውስጥ የሚገኙ ልዩ ልዩ ባለድርሻ አካላት በፖለቲካ ቀውሶች ጊዜ ቀውሶቹ ወደ ለየለት ብጥብጥ እና የእርስ በርስ ጦርነት እንዳያመሩ፤ በጥልቅ የፖለቲካ ሽግግር ጊዜ አዲስ ማኅበራዊ ውል ወይንም ሕገ መንግሥት ቀረፃ ለማካሄድ እንዲሁም ከእርስ በርስ ጦርነቶች በኋላ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሀገሬው ባለቤትነት የሚካሄድ የግጭት መፍቻ ሂደት ነው፡፡

አሁን ባለው የሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ብሔራዊ ምክክር ለማካሄዱ ከላይ የተጠቀሱት ሦስቱም ነጥቦች ምክንያት ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እያካሄደ የሚገኘው የምክክር ምዕራፍ 14ኛ መድረኩን ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ አካሂዷል። ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ጉዞ በአሥራ አንድ ክልሎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በርካታ ባለድርሻዎችን እና ተሳታፊዎችን ያካተቱ ውይይቶችን አከናውኗል። ሲካሄዱ በቆዩት መድረኮች የተሰበሰቡት ሁሉም አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ቋት ገብተዋል። በቀጣይ ከሚካሄዱት የትግራይ ክልል እና የዲያስፖራ አጀንዳ የማሰባሰብ መድረኮች በኋላ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ዋና የምክክር ጉባኤ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል።

ለመሆኑ ሀገራዊ ምክክር እንዲሳካ ወይም እንዳይሳካ የሚያደርጉት ምክንያች ምንድን ናቸው? ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችው ሀገራዊ ምክክር የእስካሁን ሂደት ምን ይመስላል? ሲጠናቀቅ ያመጣል ተብሎ የሚጠበቀው ውጤትስ ?

ትኩረቱን በሀገራዊ ምክክር ዙሪያ አድርጎ የሚሠራ መንግሥታዊ ያልሆነ ድጅት ውስጥ የሚሠሩት አቶ መስፍን ጌታቸው እንደሚናገሩት ኢትዮጵያ የምታካሂደው ሀገራዊ ውይይት በአዋጁ እንደተገለፀው ከሚወስደው ጊዜ እና አሳታፊነት አንፃር ሰፊ እና የረጅም ጊዜ ዓላማ ይዞ የሚሄድ ነው። ሀገራዊ ውይይቱ የተሳካ እንዲሆን ወይንም እንዲከሽፍ የሚያደርጉ አውዳዊ እና የሂደት ጉዳዮች አሉ።

በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች አተኩረው ከሚያነሱዋቸው የብሔራዊ ምክክር የስኬት እና የውድቀት አውዳዊ ምክንያቶች ውስጥ አንዱ የሕዝብ ድጋፍ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ያሳያሉ የሚሉት አቶ መስፍን፣ ምክክሮች በረዘሙ ቁጥር ደግሞ የሕዝብ ድጋፍም እየቀነሰ ተቀባይነትም እያጣ የመሄድ እድሉ ይጨምራል። ስለዚህም የማኅበረሰቡን ድጋፍ ይዞ ለመቀጠል የጊዜ ሰሌዳውን መመጠን ያስፈልጋል ባይ ናቸው፡፡

ሌላኛው ጉዳይ የሊሂቃን ድጋፍ ወይም ተቃውሞ መሆኑን ጠቁመው፣ ሊሂቃን በማኅበረሰብ ውስጥ ከቀሪው ማኅበረሰብ ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ ያልሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አቅም ያላቸው ቡድኖችን የሚወክሉ ናቸው። እንደነዚህ አይነት ቡድኖች ሀገራዊ ምክክር ወደ ስምምነት እንዲደርስ እና እንዲፈፀም የማድረግ ወይንም የማደናቀፍ አቅም አላቸው። ይህ ሚናቸውም በሁሉም ምክክሩ ደረጃዎች ሊተገበር የሚችል እንዲሁም ከምክክሩ ብኋላ ሳይቀር ውሳኔዎችን የማስቀልበስ አቅም ያለው ነው። ስለዚህም ከእነዚህ ቡድኖች ፍጹም ባይሆንም ቢያንስ ሂደቱን ከመሰናከል በሚጠብቅ ደረጃ ቅቡልነትን ማግኘት ይገባል ነው የሚሉት፡፡

የቀጠናዊ እና የዓለማቀፍ ማኅበረሰብ አካላትም ራሱን የቻለ ሚና አላቸው። እነዚህ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በምክክሩ ላይ ተፅዕኖ ሊያደርሱ ይችላሉ። ከቀደሙ አወቃቀሮች እና ግንኙነቶች ጥቅም የሚያገኙ አካላትም ለለውጦች እንቅፋት የሚሆኑበት ዕድል አለ። ስለዚህም በሀገር ደረጃ የሚካሄዱ ምክክሮች ውጤታማ እንዲሆኑ በተቻለ መጠን የቀጠናዊ እና የዓለማቀፍ ማኅበረሰብ አካላትን ትብብር ማግኘት ያስፈልጋል ሲሉም ያክላሉ።

አንዱ ቁልፍ ጉዳይ የምክክር ባሕል መዳበር ወይም አለመዳበር መሆኑን የሚያነሱት አቶ መስፍን፣ በምክክር ግጭትን የመፍታት ባሕል፣ ምክክርን የማመቻቸት ክህሎት፣ የማደራደርና የማሸማገል ልማዶች ወደ ስምምነት ለማድረስ ከሚያግዙ ወይንም ከሚያደናቅፉ ጉዳዮች ውስጥ ይካተታሉ። የቀደሙ የድርድር እና ምክክር ተሞክሮዎች ደግሞ ካለፉ ስህተቶች ትምህርቶች ተወስደው እንዳይደገሙ ሊረዱ ይችላሉ ብለዋል።

በተለይም በምክክር ወቅት የሚኖሩ ግጭቶችና ብጥብጦች ሂደቱንም ሆነ የሚገኘውን ውጤት የመቀየር ከፍተኛ አቅም እንዳላቸው ሲያመላክቱ፣ ግጭቶችና ብጥብጦች ስምምነት ላይ መድረስን እና የትግበራ ሂደትን ሊገድቡ ይችላሉ ነው የሚሉት። የተለያዩ ሀገራት በግጭት ውስጥ በነበሩባቸው ወቅቶች ምክክሮችን ማካሄድ መቻላቸውን ጠቅሰው፣ ግጭቶቹ ግልጽ ተጽዕኖ ማሳደራቸውን አውስተዋል።

ሀገራዊ ምክክር ከሚያልፍበት ሂደት አንጻር በርከት ያሉ ጥናቶች መደረጋቸውን የሚጠቁሙት አቶ መስፍን፣ የተሳታፊዎች ምርጫ፣ ቁጥር እና ወካይነት ተአማኒ እንዲሁም ተቀባይነትን የሚጨምር መሆን አለመሆኑ፤ የውሳኔ አሰጣጥ መንገዱ አሳታፊ፣ ግልፅ እና ተቀባይነት ያለው መሆንና አለመሆኑ፤ የአመቻቾች እና የሸምጋዮች ምርጫ ገለልተኝነት፣ ቅቡልነት ያለው መሆንና አለመሆኑ፤ የምክክሩ ጊዜ ርዝመት ወይንም እጥረት ስምምነት መድረስ ላይ ተፅዕኖ ባይኖረውም ጥናቶች እንደሚያሳዩት ምክክሮች በረዘሙ ቁጥር ተፈፃሚነታቸው እየቀነሰ ይሄዳል። የድጋፍ መዋቅሮች መኖርና አለመኖራቸው እንዲሁም በምክክሩ ውስጥ የሚፈጠሩ ጥምረቶችም ምክክሩን ሊያሳኩ ወይንም ሊያደናቅፉ የሚችሉበት ዕድል አለ። ስለዚህም እነዚህን አውዳዊ እና የሂደት ጉዳዮችን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራችን ለጀመረችው ምክክር መሥራት ይገባል ሲሉ ይመክራሉ።

ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተጠራቀሙትን ሁሉንም ችግሮቻችንን በአንድ ጊዜ ይፈታልና ብለን መጠበቅ እንደማይገባን አሳስበው፣ በትንሸ ከኖርንበት የግጭት አዙሪት ሊያወጣን እንደሚችል እንደ አንድ ወሳኝ መሳሪያ ልንገነዘበው ይገባል። ምክክር፣ ንግግር፣ ድርድር፣ እና ሽምግልና ብቸኞቹ የግጭት መፍቻ መንገዶቻችን እንዲሆኑ በማመን የተጀመረው የምክክር ሂደት እንዲሳካ የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አባባ ባካሄደው የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ጉባዔ ላይ ሲሳተፉ አግኝተናቸው ሀገራዊ ምክክሩ እያለፈበት ስላለው ሂደት እና ይገኛል ተብሎ ስለሚጠበቀው ውጤት ያላቸውን አስተያየት የጠየቅናቸው ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪም እንደሚሉት፤ በጦርነት ውስጥ አልፈናል ከውድመት በቀር የፈየደልን ነገር የለም። እስከዛሬ ድረስ ባልሞከርነው ሀገራዊ ምክክር ተስፋ ሰንቀን በንቃት እና በነጻነት መሳተፋችን ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት ይረዳል ብዬ አምናለሁ። እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ እየተነሱ ያሉት ሀሳቦች ብንነጋር ለመግባባት እንደማንቸገር የሚሳዩ ናቸው።

በምክክር መድረኩ በርካታ ሃሳቦች ሲነሱ መስማታቸውን የጠቆሙት ፕሮፌሰሩ፣ ከሂደቱ መረዳት እንደሚቻለው በመነጋገር ለማንኛውም ጉዳይ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል። የመድረኩ ተሳታፊዎች ሃሳባቸውን ሲገልጹ የተገነዘብኩት ልዩነቶችን ቁጭ ብሎ በንግግር የመፍታት ባሕል ብናዳብር ኖሮ ሀገራችን በብዙ ደም አፋሳሽ ግጭቶች ውስጥ እንደማታልፍ ነው። አሁንም ቢሆን ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በ21ኛው ክፍለ ዘመን እንዲህ ያለው አካሄድ እንዳበቃለት በመረዳት አለን የሚሉትን ጥያቄ በሰላማዊ መንገድ ጠረጴዛ ላይ ማቅረብ አለባቸው ነው የሚሉት።

በሀገራዊ ምክክሩ ገና ከጅምሩ ብዙ ስጋቶች ያደሩባቸው ወገኖች እንደነበሩ አስታውሰው፣ የምክክር ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት ነጻና ገለልተኛ መሆኑን አስመስክሯል። በርካቶችም ሂደቱን በመመርመር ወደተሳትፎ መጥተዋል። እኔም እንደ አንድ ዜጋ በነበረኝ ተሳትፎ ያረጋገጥኩት ይሄንኑ ነው። ኮሚሽኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጽ በነጻነት እንዲሰማ እያደረገ መሆኑን ተረድቻለሁ። በየጥጋ ጥጉ ስሙን ለማጠልሸት የሚራገበው አሉባልታ መሰረት የሌለውና ሀገር እንድትገነባ የማይፈልጉ የአፍራሾች የፈጠራ ወሬ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ ምክክር ጥሩ ውጤት ያስገኛል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ያት ፕሮፌሰር አለማየሁ፤ ከማንም በላይ ከዚህ ምክክር ተጠቃሚ የሚሆኑት ወጣቶች ናቸው። ይህች ሀገር የወጣቶች ናት። ነገን የሚረከቡት እነሱ ናቸው። ሀገራዊ ምክክርና ውይይት በዚህ ደረጃ ስፋት ባለው መንገድ ሲካሄድ መመልከታቸውና በሂደሩም መሳተፋቸው በቀጣይ በሀገራችን ልዩነቶችን በንግግር የመፍታት ባሕል እንዲገነባ በር የሚከፍት ነው። አሁን የሚካሄደው ምክክር የሚያስተላልፈው ትልቁ መልዕክት ይህ ነው። ኢትዮጵያውያን ተነጋግረው የራሳቸውን ችግሮች ራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል፡፡

በምክክሩ ማጠቃለያ ላይ በሰጥቶ መቀበል መርህ አብዛኞቹን ችግሮቻችንን እንፈታለን፤ ልዩነቶቻችንን እናጠባለን የሚል እምነት አለኝ። ስምምነት ላይ ያልደረስነባቸው ጉዳዮች ካሉም በቀጣይ እያየናቸው እንሄዳለን። እኔ በዚህ ሀገራዊ ምክክር ውጤት ዙሪያ የሚታየኝ ብሩህ ተስፋ ነው። ያለጥርጥር ስኬታማ እንደሚሆን እምነቴ ነው ሲሉም አክለዋል።

አያይዘውም፤ ኢትዮጵያውያን ቂም በቀልን ሳያሳድሩ ችግሮቻቸውን የሚፈቱባቸው የመልካም ባሕሎች ባለቤቶች ናቸው። እነዚህን የኖሩ መሳሪያዎች በመጠቀም ከግጭት አዙሪት መውጣት አለብን በሚል ቆርጠን መነሳት አለብን። ልዩነቶችን በመከባበር መንፈስ ቁጭ ብሎ በመነጋገርና በመደማመጥ የመፍታት ባሕላችን ከዳበረ ኢትዮጵያን ዳግም ወደ ነበረችበት የታላቅነት ማማ የማትመለስብት ምንም አይነት ምክንያት የለም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተደጋጋሚ የሚያቀርበውን ጥሪ ባለመቀበል አሁን ድረስ በምክክሩ ሂደቱ ላለመሳተፍ አቋም የያዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የታጠቁ ኃይሎች እንዲሁም በእስካሁኑ ሂደት ዙሪያ ጥያቄዎችን የሚያነሱ ሊህቃን በዋነኝነት የሚያነሱት ጥያቄ የኮሚሽኑ ገለልተኝነት ላይ የሚያጠነጥን ነው። ሀገራዊ ምክክሩ ለዚህ ጥያቄ ተደጋጋሚ ግንዛቤ መፍጠር ሥራ ሲሠራ ቢቆይም፣ እንዲሁም በተጨባጭ መሬት ላይ ባለው ሂደት የተለያዩ ተሳታፊዎች ምስክርነታቸውን የሰጡ ቢሆንም ዛሬም የዳር ተመልካች መሆኑን የመረጡ አካላት አሉ፡፡

መንግሥትም በበኩሉ ለሚቀርብበት ውንጀላ በየጊዜው መልስ ከመስጠት አልተቀቆጠበም። ለአብነትም ባሳለፍነው ሳምንት በአዲስ አበባ ከተማ የተካሄደውን የፌዴራል ባለድርሻ አካላት የአጀንዳ ማሰባሰብ ጉባዔን አስመልክቶ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ፣ መንግሥት ኮሚሽኑ የሚያከናውነውን ምክክር በገለልተኝነት እንዲያከናውን የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

መንግሥት ሀገራዊ ምክክሩን ከጥንስሱ ጀምሮ አሁን እስካለበት ደረጃ ስለደገፈበት ሂደት ከስር ባሉት ሦስት አንቀጾች ስለራሱ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡

ሀገራችን በበርካታ ጉዳዮች በተቃርኖዎች ውስጥ ለረዥም ዘመናት ስትናጥ እና በአስከፊ ግጭቶች ውስጥ ስታልፍ ቆይታለች። በተለይም ለረዥም ዓመታት እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በፖለቲካ እና በሐሳብ መሪዎች እንዲሁም በኅብረተሰቡ ክፍሎች መካከል ልዩነት እና አለመግባባቶች ኖረዋል። እነዚህን አለመግባባቶች በየዘመኑ እየፈታን የመጣንበት መንገድ ዘላቂ ትምምን በሚፈጥር መልኩ ስላልነበረ ከጦርነት እና ግጭት አዙሪት በዘላቂነት መንጭቀን እንዳንወጣ እንዳደረገን እሙን ነው።

እነዚህ የግጭት መንገዶች እጅግ በርካታ ውድመት አስከትለዋል። ለረጅም ጊዜ ይዘን የመጣነው ልምምድ እና ዝንባሌ ታላላቅ ሕልሞቻችንን በጋራ እንዳናሳካ እንቅፋት ሆኖብን ቆይቷል። እነዚህ መንገዶች አንዱ የጀመረው ላይ እየገነባን የምንሄድ ሳይሆን ሁሌም ከዜሮ ጀማሪዎች እንድንሆን፣ በተቋማት እና በመሠረታዊ የሀገር ምሰሶዎች ላይ እምነት፣ የጋራ የሆነ ሀገራዊ የተስፋ ዕይታ እንዳይኖረን አድርገውን ቆይተዋል። እኛ ኢትዮጵያውያን በጋራ ባለመምከራችን ያያያዙን፣ ያጋመዱን የተለያዩ ጥብቅ እሴቶቻችንን ለሚሸረሽሩ አካላት ምቹ ሁኔታ ስንፈጥር ኖረናል።

ይህን አዙሪት በዘላቂነት ለመፍታት ልዩነቶቻችንን እና አለመግባባቶችን ላይ ሰፋፊ ሀገራዊ የሕዝብ ምክክሮችን አካታች በሆነ መንገድ በማካሄድ ሀገራዊ መግባባት መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ፤ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ በርካታ ሥራዎችን አከናውኗል። ኮሚሽኑ እጅግ መሠረታዊ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታች ሀገራዊ ምክክሮችን በማካሄድ የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመገንባት፤ በሂደትም መተማመን ለማጎልበት ያለውን የማይተካ ፋይዳ በመገንዘብ ነጻ፣ ገለልተኛ እና አካታች እንዲሆን መንግሥት አስፈላጊውን ሕጋዊና መዋቅራዊ ድጋፍ አድርጓል።

በተስፋ ፈሩ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You