የአምራቾች የማምረት አቅም ልኬት ሀገራዊ የማምረት አቅምን የሚያሳድግ ነው

አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት እያከናወነ ያለው በጥናት ላይ የተመሠረተ የአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬት ሀገራዊ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምን እንደሚያሳድግ ተገለጸ።

በልማት መሥሪያ ቤቱ የጨርቃጨርቅና ቆዳ ውጤቶች መሪ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አብርሃም ደስታ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ተቋሙ ለኢንተርፕራይዞች አስፈላጊውን ድጋፍ ለማቅረብ በጥናት ላይ የተመሠረተ የአምራች ኢንተርፕራይዞች የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬት ከግንቦት 18/2017 ዓ.ም ጀምሮ ለአንድ ወር የሚቆይ የመጀመሪያ ዙር ልኬት በተወሰኑ ክልሎች ላይ እያካሄደ ይገኛል።

የልኬት ሥራው የአምራቾች የማምረት አቅም በትክክል ምን ያህል ነው? የሚለውን በክልል ብሎም በሀገር አቀፍ ደረጃ ከማወቅ ባለፈ የሚያስፈልጋቸውን ድጋፍ ለይቶ በማቅረብ ሀገራዊ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅምን እንደሚያሳድግ አመልክተዋል ።

አሁን ላይ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው ዙር ልኬት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሚገኙ 100 አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ይለካሉ ያሉት አቶ አብርሃም፤ በቀጣይ በሚካሄደው በሁለተኛ ዙር ልኬት ደግሞ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ አምራች ኢንተርፕራይዞች እንደሚለኩ አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ከዝቅተኛ እስከ መካከለኛ ድረስ ያለው ሀገራዊ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 61 በመቶ ገደማ መሆኑን መረጃዎች እንደሚያመለክቱ ገልጸው፤ ይህንን ሀገራዊ የማምረት አቅም በአምስት ዓመት ውስጥ ወደ 85 በመቶ ከፍ የማድረግ እቅድ ተይዞ በትኩረት እየተሠራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል ።

የልኬቱ ግብ አምራች ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ችግሮቻቸውን የሚፈቱ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በመስጠት ወይም በማቅረብ ሀገራዊ የማምረት አቅምን ማሳደግ ነው ያሉት አቶ አብርሃም፤ ከዚህ አኳያ ተቋሙ እያከናወነ ያለው በጥናት ላይ የተመሠረተና ወጥነት ያለው የአቅም አጠቃቀም ልኬት በአምስት ዓመቱ የተቀመጠውን የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም 85 በመቶ የማድረስ ውጥን ለማሳካት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት አስታውቀዋል።

አቶ አብርሃም እንዳመለከቱት ፤ የማምረት አቅም ሲያድግ ደግሞ በዛው ልክ ከውጭ የሚገባ ምርትን በሀገር ውስጥ በስፋት በመተካት የውጭ ምንዛሪ ወጪን በእጅጉ ይቀንሳል። በምርትና ፍላጎት አለመጣጣም ሳቢያ የሚከሰትን የዋጋ ንረት ያስቀራል። ለዜጎች በዘርፉ ከፍተኛ የሥራ ዕድል ይፈጠራል። ሀገሪቱ ወደ ውጭ የምትልከውን ምርት በከፍተኛ ሁኔታ በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ገቢ እንድታገኝ ይረዳታል። ልኬቱ በሂደት እነዚህን ድምር ውጤቶች ያስገኛል።

ከዚህ ባሻገር ልኬቱ ክልሎች እንዲሁም ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች እንዲያዩና የመፍትሄ ርምጃ እንዲወስዱ ያግዛቸዋል። እንዲሁም የምርታማነት ደረጃቸውን እንዲያውቁ፣ ለሀገር ኢኮኖሚ እያበረከቱት ያለውን አስተዋጽኦ ጠንቅቀው እንዲረዱ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ተረድተው ተገቢ የሆኑ ርምጃዎችን በመውሰድ ተወዳዳሪና ትርፋማ ሆነው እንዲወጡ … ወዘተ ያስችላቸዋል ብለዋል።

በማንዋሉ መሠረት የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬቱን የልማት መሥሪያቤቱ ባለሙያዎች ከየክልሉ ባለሙያዎች ጋር በመቀናጀት እያከናወኑ እንደሚገኙ አቶ አብርሃም ገልጸው፤ በጥናት ላይ የተመሠረተ የአቅም አጠቃቀም ልኬቱን ከየክልሉ የዘርፍ ቢሮዎች ጋር ተቀናጅቶ መሠራቱ በአነስተኛና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ደረጃ ያለውን የማምረት አቅም አጠቃቀም የአለካክ ሥርዓት በሀገር አቀፍ ደረጃ ወጥ ለማድረግ እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ስለዚህ ሁሉም ኢንተርፕራይዞች ራሳቸውን በማንዋሉ መሠረት ለክተው፤ ወደ ሙሉ የማምረት አቅም ደረጃ ላይ ለመድረስ እቅድ አውጥተው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸው፤ ክልሎች ደግሞ የማምረት አቅም አጠቃቀም ልኬቱን ከልማት መሥሪያቤቱ ጋር ተቀናጅተው ማከናወንና በቀጣይም ልኬቱን አጠናክረው ማስቀጠል እንዳለባቸው አቶ አብርሃም አሳስበዋል።

ሶሎሞን በየነ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You