
ሰመራ፦ በአፋር ክልል የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማደጉን የአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ ያሲን በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የክልሉ ሴቶች ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነት አድጓል። በክልል እና በሀገር አቀፍ ደረጃ የአመራርነት ተሳትፎአቸው ጨምሯል፡፡
ቢሮው የክልሉ ሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ በሰባት ዓመቱ ሰፊ ሥራዎችን ሠርቷል። ውሳኔ ሰጪ እንዲሆኑ በተከናወኑ ተግባሮች ካቢኔ ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ ከለውጡ በፊት ከነበረው ጋር ሲታያይ ዕድገት ማሳየቱን አመልክተዋል።
ሀገራዊ ለውጡ እንደመጣ የክልሉ የሴቶች የአመራርነት (የፖለቲካ ተሳትፎ ውስን እንደነበር አስታውሰው ፤ አሁን ግን እስከ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደረጃ ሃላፊነት ተሰጥቷቸው እያገለገሉ መሆናቸውን አስታውቀዋል። ይህም በፖለቲካ አኳያ የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ዕድገት እያሳየ ለመምጣቱ በእብነት እንደሚታይ ገልጸዋል።
ቢሮው የሴቶችን የህፃናትን፣ የአረጋውያንን፣ የአካል ጉዳተኞችን ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት ፣ መብትና ደህንነታቸውን ከማረጋገጥ አኳያ ሰፊ ሥራዎች መሥራቱን አመልክተዋል።
በተለያየ መንገድ ጥቃት የሚደርስባት ሴት በተቀናጀ አሠራር ፍትህ የምታገኝበት አደረጃጀት መፈጠሩን አመልክተው፣ በጉዳዩ ላይ የሚመለከታቸው አካላት በጋራ ሆነው የተሟላ አገልግሎት መስጠት የሚችሉበት ሰባተኛው የአንድ ማዕከል አገልግሎት በቅርቡ በወረር ከተማ ተመርቆ ወደ ሥራ መግባቱን ጠቁመዋል።
በዚህ ማዕከል የፍትህ ፣ የፖሊስ፣ የጤና እና ማህበራዊ አገልግሎት ሰጪዎች ተቀናጅተው የሚሠሩበት ተጠቂዎች ተገቢውን አገልግሎት በ72 ሰዓት የሚያገኙበት እንደሆነም አመልክተዋል።
ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች በሀገር ደረጃ በተዘጋጁ የማገገሚያ ማዕከላት የሚቆዩ መሆኑን ጠቁመው ፤ ለዚህም በሀገር ደረጃ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ መንግሥት በጀት አውጥቶ በድሬዳዋ ከተማ መስተዳድር እና በአፋር ክልል ሁለት ማገገሚያ ማዕከላት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
በማእከላቱ ጥቃቱ የሚያመጣውን ጉዳት የሚያስቀሩ የሥነልቦና ሥልጠናዎች በተጨማሪ ተጠቂዎች ገቢ በሚያገኙባቸው ዘርፎች ላይ የሕይወት ክህሎት ሥልጠና እና ድጋፍ የሚያገኙባቸው መሆናቸውን አመልክተዋል። ተቋማቱ የለውጡ ትሩፋት መሆናቸውን ጠቁመዋል። በክልሉ ዞን አምስት ማዕከሉን ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
ከትምህርት አንፃር ራቅ ብለው የሚማሩ ሴቶች የሚደርስባቸው ችግሮች እና የተለያዩ ጥቃቶች የሚያስቀር የመጀመሪያው የሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ከለውጡ በኋላ በሰመራ መከፈቱን ጠቁመዋል። ማዕከሉ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ለሴቶች የትምህርት አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ከዚህ የወጡ ሴት ተማሪዎች በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች አመራር የሆኑበት ሁኔታ መኖሩን አመልክተዋል ።
ከሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግብረ ሰናይ ድርጅት ድጋፍ ይጠየቅ ከነበረበት ሁኔታ በመውጣት ሴቶች ተደራጅተው መሥራት አለባቸው በሚል የክልሉ መንግሥት በራሱ ኃላፊነቱን ወስዶ ካፒታል በጀት ይዞ መሥራት መጀመሩን ጠቁመዋል።
ክልሉ ላለፉት ሰባት ዓመታት በሰው ሠራሽ እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ጉዳት እንደደረሰበት ፤ ከዚህ ውስጥ የሰሜኑ ጦርነት፣ አንበጣ ፣ ጎርፍ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ተጠቃሽ መሆናቸውን አመልክተዋል።
ከጦርነቱ በኋላ ቢሮው፣ ከመንግሥት እና አጋር አካላት ጋር በመሆን ሴቶችን በኢኮኖሚ ለማብቃት የሚያስችሉ አበረታች ሥራዎች መጀመራቸውን አስታውቀዋል።
በ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን እንዲችሉ ለማድረግ ተደራጅተው እንዲሠሩ እየተደረገ ነው፤ ለእዚህም ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቧል ብለዋል።
ሴቶች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በቅድሚያ ግንዛቤ ላይ መሥራት እንደሚያስፈልግ ታምኖበታል ያሉት ሃላፊዋ፣ ለዚህም እንዲረዳ በ14 ወረዳዎች ላይ ጥናት ተደርጓል ብለዋል። ጥናቱ እኔ አውቅላታለሁ የሚለው ቀርቶ ሴቶቹ በምን ላይ መሠማራት ይፈልጋሉ የሚለውን ለመለየት እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡
በእነሱ ፍላጎት ላይ በመመስረትም ከሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመሆን ሴቶቹን ማደራጀት መቻሉን ገልጸዋል። በሚሠማሩባቸው የሥራ ዘርፎች የንግድ ዕቅድ መዘጋጀቱንም አመልክተዋል።
የሕይወት ክህሎት ሥልጠና ተሰጥቷቸው የስታርት አፕ ካፒታ ወደ አካውንታቸው የማስገባት ሥራ መሠራቱንም ወይዘሮ ፋጡማ መሐመድ አስታውቀዋል።
በበኃይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም