ቀጣዩን ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፦ ሰባተኛውን ሀገር አቀፍ ምርጫ በተቀመጠለት ጊዜ ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በቀጣይ ዓመት የሚደረገው ምርጫ በዲጂታል እንዲካሄድ ማሕቀፍ መዘጋጀቱንም አመለከተ።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ቅድመ ዝግጅትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት ፤ በ2018 ዓ.ም ለሚካሄደው ሀገራዊ ምርጫቦርዱ አስፈላጊውን ዝግጅት እያደረገ ነው።

የምርጫ ማካሄድ ሥነ-ሥርዓት ቅድመ ምርጫ ፣ የምርጫ ወቅት እና ድህረ ምርጫ ምዕራፎች አሉ ያሉት የቦርድ ሰብሳቢዋ ፤ ከስድስተኛው ሀገርአቀፍ ምርጫ የተገኙ ልምዶችን በመገምገም እና ጥናት በማድረግ ቦርዱ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በ2013 ዓ.ም በተካሄደው ምርጫ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላትና ሲቪክ ማህበራት ጋር ውይይት ከተደረገ በኋላ ቦርዱ የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ እንደሚያስፈልገው ከድምዳሜ ተደርሶ ወደ ሥራ መግባቱን አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ እስካሁን የሚደረጉ ምርጫዎች በማኑዋል መካሄዳቸውን አንስተው በቀጣይ ዓመት የሚደረገው ምርጫ በዲጂታል እንዲካሄድ ማሕቀፍ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል። የምርጫ አስፈፃሚዎች ምልመላን በተመለከተ ከዚህ ቀደም በኦንላይን ተመዝግበው ወደ ሥራ የሚገቡበት ሂደት እንደነበር ገልጸው ፤ በቀጣዩ ምርጫ የምርጫ አስፈፃሚዎች የራሱ የሆኑ መገምገሚያ ጥያቄዎችን በማዘጋጀት በኦንላይን ፈተና ወስደው ብቃታቸው ተረጋግጦ ወደ ሥራ የሚገቡ ይሆናል ብለዋል።

የ2018 ምርጫ በዲጂታል ሥርዓት ማከናወን ከዚህ ቀደም መራጮችን ለመመዝገብም ሆነ የአስመራጭ ኮሚቴዎችን ለመመዝገብ ይወጣ የነበረውን ከፍተኛ ወጪ የሚቀንስ መሆኑን አመልክተው ፤ የፖሊቲካ ፓርቲዎች እንዲሁ አባሎቻቸውን የሚመዘግቡበትና ለቦርዱ የሚያስረክቡበት ሥርትዓት መዘርጋቱንም በመግለጫው አመልክተዋል።

ቦርዱ በ2018 ዓ.ም የሚካሄደው ምርጫ በሕገ-መንግሥቱ በተቀመጠለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማካሄድ የምርጫ ጣቢያዎች አደረጃጀት ፣ ገለልተኛ መሆን ፣ ለሴቶች ፣ ለአረጋውያን እና ለአካል ጉዳተኞች ያለውን ምቹነት የመገምገም ሥራዎችን እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በዚህም በሀገርአቀፍ ደረጃ ከሚገኙ 50 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች እስካሁን 12 ሺህ የምርጫ ጣቢያዎች ምልከታ ተደርጎባቸዋል ብለዋል፡፡

ምርጫውን በተሳካ ሁኔታ ለማስኬድ ከሚሠሩ ሥራዎች እያንዳንዱ የምርጫ ተሳታፊ እና አስፈጻሚዎች የሥራ ክፍላቸውን አውቀው እንዲሠሩ የሚያስችል ማኑዋል መዘጋጀቱ ያመለከቱት ሰብሳቢዋ ፤ እያንዳንዱ የሥራ ክፍል በዚህ መመርያ መሠረት የሚሠራ ይሆናል ፤ ማንዋሉ እርስበእርስ መናበብ የሚያስችል መሆኑም ገልጸዋል።

መራጮች ወደ ምርጫ ሲሄዱ የፋይዳ መታወቂያን ቢይዙ ተመራጭ ነው ያሉት ሰብሳቢዋ ፤ይህም ውጤታማ ምርጫ እንዲካሄድ ይረዳል። ይህ ማለት የፋይዳ መታወቂያ የሌለው ሰው ከመራጭነት ይታገዳል ማለት እንዳልሆነ አስታውቀዋል።

ምርጫው ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው አስቻይ ሁኔታዎች ባሉባቸው የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚካሄድ ገልጸው። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ የምርጫ ጣቢያዎችን በማቋቋም በመጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዜጎች መራጭ ብቻ ሳይሆን እጩ እንዲሆኑም ፤ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች የሚሄዱ የምርጫ ቁሳቁሶች በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆኑም የሎጀስቲክ ዘርፉ ላይ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል ።

በሰሚራ በርሀ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You