
-ፕሮጀክቱ ከመጠናቀቂያ ጊዜው ሁለት ዓመት ዘግይቶም አፈጻጸሙ 23 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል
አዲስ አበባ፡– በኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ባለቤትነት፣ በኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን አማካሪነትና በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ተቋራጭነት እየተገነባ የሚገኘው የአላባ-አንገጫ-ዋቶ እና የደምቦያ አስፋልት መንገድ ፕሮጀክት መዘግየት በቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ ተነስቶበታል።ፕሮጀክቱ ከመጠናቀቂያ ጊዜው ሁለት ዓመት ዘግይቶም አፈጻጸሙ 23 በመቶ ላይ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በትናንትናው ዕለት ከሦስቱ ተቋማት አመራሮች ጋር በመሆን የፕሮጀክቱን አፈጻጸም ገምግሟል።ፕሮጀክቱን በአማካሪነት እየመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን የትራንስፖርት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር አበበልኝ መኩሪያ ባቀረቡት የሥራ ሪፖርት እንዳሉት፤ እ.ኤ.አ ሐምሌ 29 ቀን 2020 የግንባታ ሥራ ውል ተፈርሟል።የግንባታ ሥራ ውሉም አንድ ነጥብ 98 ቢሊዮን ብር ነበር።የግንባታ ሥራውንም በሦስት ዓመታት ማለትም ታሕሳስ 29 ቀን 2023 ለማጠናቅ ታቅዶ ነበር።
በሂደት በተደረገው ግምገማ የፕሮጀክት ክለሳ ተከናውኖ የተሻሻለው የፕሮጀክት ማጠናቀቂያ ጊዜ እ.ኤ.አ ሚያዝያ 26 ቀን 2025 እንደነበር ጠቅሰው፤ እስሁን ድረስ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም 23 በመቶ ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የወሰን ማስከበርና የፋይናንስ አቅርቦት ችግሮች ለፕሮጀክቱ መዘግየት በምክንያትነት የጠቀሱት ኢንጅነር አበበልኝ፤ ሥራዎችን በቅንጅት አለማስተዳደርና የባለድርሻዎች ተናቦ አለመሥራትም ተጨማሪ እክል መፍጠራቸውን አንስተዋል።
ፕሮጀክቱን በኮንትራክተርነት እየሠራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር በእምነት ጋሻው በሰጡት ምላሽ፤ የፕሮጀክቱን መዘግየትና በዚህም ሕዝቡን የደረሰበትን እንግልት እንደሚቀበሉት ገልጸዋል።
የወሰን ማስከበር ችግሮች ሥራውን በእጅጉ እንደተፈተነው አንስተው፤ እስካሁን ድረስ ከ65 ኪሎ ሜትሩ አጠቃላይ ፕሮጀክት 40 በመቶ የሚሆነው ፕሮጀክት አካል የወሰን ማስከበር አለመከናወኑን ጠቁመዋል። የፋይናንስ አቅርቦት ችግር፣ የዋጋ ንረት፣ የውጪ ምንዛሪና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪንም በምክ ንያትነት ጠቅሰዋል።
አሁን ላይ ሥራውን እየሠራን ያለነው በብድርና በኪሣራ ነው ያሉት ኢንጅነር በእምነት፤ ከዚህ ፕሮጀክት ትርፍ አንፈልግም፤ ሥራውን በፍጥነት አጠናቀን ሕዝቡን መካስ እንፈልጋለን፤ ለዚህ ደግሞ ወቅቱን የሚመጥን የዋጋ ማሻሻያ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር መልካሙ በቀለ በበኩላቸው፤ የሥራው መዘግት አካባቢው ሕዝብ ላይ ትልቅ ቅሬታ መፍጠሩን ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ አሁን ባለው ሂደት ከቀጠለ ተጨማሪ ስድስት ዓመታት እንደሚፈልግ አመልክተው፤ የወሰን ማስከበር ችግሮችን ለመቅረፍ ከክልሉ አመራሮች ጋር መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
ተቋራጩ በገባው ውል መሠረት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዳለበት አንስተው፤ የፕሮጀክት ውሉን ተከትሎ የዋጋ ንረት ማሻሻያ እንጂ የዋጋ ክለሳ ማካሄድ የሚቻልበት አሠራር እደሌለ አብራርተዋል።ኃላፊነትን በመገፋፋት ውጤት ሊመጣ እንደማይችል አመልክተው፤ ተቀራርቦ በመነጋር የሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለስ መና በሰጡት ማጠቃለያ፤ ሦስት ታላላቅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች የሚሳተፉበት ፕሮጀክት በዚህ ልክ መጓተቱ የሚጠበቅ እዳልሆነ አንስተዋል።
ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ሕዝቡ ለእንግልት መዳረጉን አመልክተው፤ ሥራው ያለፉትን ጊዜያት መዘግየት በሚያካክስ መልክ ሊሠራ ይገባል ብለዋል።የተቋማቱ የበላይ ኃላፊዎች በጋራ ተወያይተው የደረሱበትን ውጤት በአማካሪው በኩል ለቋሚ ኮሚቴው ሪፖርት እንዲቀርብ አቅጣጫ አስቀምጠዋል።
በተጨማሪም የወሰን ማስከበር ሥራዎች በፍጥነት እንዲከናወኑ፣ የዋጋ ክለሳን ጨምሮ ሌሎችም ተግዳሮቶች በተቋማቱ ኃላፊዎች ውይይት ተደርጎባቸው ባሉ የሕግ አማራጮች ሊፈጸሙ እንደሚገባ ጠቁመው፤ አማካሪ ድርጅቱም የሚጠበቅበትም ሚና እንዲወጣ አሳስበዋል።
በፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም