
የነጻ አውጪነት እሳቤ የ1960 ዎቹ የወጣቶችን የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ወደ አደባባይ የመጣ ነው። በተለይም የብሄር ጥያቄ አለን የሚሉ ኃይሎች በወቅቱ የነበረውን የፖለቲካ መነቃቃት እንደ አንድ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ዜጎችን በየጎጡ በማደራጀት አለን ለሚሉት ጥያቄ ጠብመንጃ አንግበው ወደ ጫካ ፈልሰዋል።
ይህንን ተከትሎም ሀገሪቱ ከሦስት አስርት ዓመታት ለቀጠለ የእርስ በርስ ጦርነት ተዳርጋለች ፤ ሀገር እና ሕዝብም በእዚህ ጦርነት ከፍተኛ ለሆነ ሠብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ፤ ለከፋ የሥነ ልቦና ስብራት ተዳርገዋል። ብዙ የተዘመረለት እና ተስፋ የተደረገበት የወቅቱ ለውጥም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ አልፎ የተጠበቀውን ውጤት ሳያመጣ እንደ ሀገር ተጨማሪ ጥቁር የታሪክ ምንጭ ሆኖ አልፏል።
የስመ ነጻ አውጪነት እሳቤ ከዚያን ዘመን ጀምሮ የሀገርን ብሔራዊ አንድነት ከመፍታት አልፎ ፤ እንደ ሀገር ለዘመናት የቆየውን የሕዝባችንን አብሮ የመኖር ባህል በመሸራረፍ ያለመተማመንን እና የጥርጣሬ ምንጭ ሆኗል። ከፍ ያለ ማኅበራዊ ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ስብራት በመሆንም አሁን ያለውን ትውልድ ሳይቀር ያልተገባ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል።
ገና ከጅምሩ ባልጠራ ፖለቲካ ፤ መርሕ አልባ በሆነ ግንኙነት፣ በተዛቡ ትርክቶች እና ጥላቻ ላይ የሚገባው ይህ የነጻ አውጪነት እንቅስቃሴ ፤ ነጻነት የሚለውን ቃል ከማሳነስ ባለፈ ፤ ዜጎች ስለነጻነት በዘመናት መካከል የገነቧቸውን የጋራ እሴቶች ጭምር ሸርሽሮታል። በነጻነት ስም ያልተገባ ዋጋ እንዲከፍሉ ፤ በሚከፍሉትም ዋጋ ለከፋ ባርነት እንዲዳረጉ አድርጓቸዋል።
ራሳቸውን ነጻ አውጪ አድርገው በዘመኑ የተነሱ ቡድኖች፣ ከብዙ ደም መፋሰስ /እልቂት በኋላ ወደተመኙት ሥልጣን ሲመጡ፤ ለሕዝባችን የነጻነት ምንጭ ከመሆን ይልቅ፤ በሕዝቡ ላይ የጫኑት የአገዛዝ ቀንበር የቱን ያህል ከባድ / መራራ እንደነበር ፤ ቀንበሩን ለመስበር ሌላ ሕዝባዊ ትግል / መሥዋዕትነት እንደጠየቀ የአደባባይ ሚስጥር ነው።
አሳዛኙ እውነት እነዚህ ቡድኖች የሀገርን ህልውና፤ የሕዝባችንን አብሮ የመኖር ዘመን የተሻገረ ማኅበረሰባዊ ማንነት ሳይቀር የነጻ አውጪነት ቁማር መቆመሪያ ካርድ አድርገው የመጡበት መንገድ ፤ እንወክለዋለን ብለው ብዙ ያልተገባ የመሥዋዕትነት ዋጋ ላስከፈሉት ሕዝብ ሳይቀር ያመጣለት አንዳች ነገር አልነበረም ። ብዙ የተደሰኮረለት ነጻነት እንኳን እንደ ቀለብ በራሽን እየተሰፈረላቸው የነጻነት ናፋቂ እንደሆኑ እስከ ዛሬ አሉ።
ይህ ተጨባጭ የሆነ የትናንት ትርክት ከጓዳዎቻችን ወጥቶ፤ አደባባዮቻችንን በሞላበት በዚህ ዘመን፤ በተመሳሳይ ቁማር ውስጥ የሚገኙ ቡድኖችን የመመልከታችን እውነታ ፤ የቱን ያህል ከትናንት ስህተቶቻቸው መማር ያቃታቸው ኃይሎች እንዳሉ የሚያሳብቅ ነው። ከሁሉም በላይ ፖለቲከኞቻችን የቱንም ያህል ቆሞ ቀር ብቻ ሳይሆን የመቆመሪያ ካርዳቸው ዛሬም የንጹሃን ዜጎች ደም መሆኑን አመላካች ነው።
ፖለቲካ ከጅማሬው በመርህ የሚገዛ፤ የሕዝብን ተጠቃሚነት መሠረት ያደረገ ነው። በየትኛውም መመዘኛ ባልጠራ የፖለቲካ እሳቤ፤ መርህ አልባ በሆነ ግንኑነት ፣ በተዛቡ ትርክቶች እና ጥላቻ ፤ ጽንፍ በረገጠ እሳቤ ላይ የሚመሠረት ፖለቲካ ማንም የሚያተርፍ አይደለም። እርግማን ሆኖ የትውልዶችን ሆኖ የመገኘት መሻት/ ተስፋ ከማምከን፤ ማህበራዊ ግራ መጋባት እና ውድቀት ከማምጣት ያለፈ ፋይዳም አይኖረውም።
ይህ እንደሀገር ባለፉት ስድስት አስርት ዓመታት በተጨባጭ ያየነው፤ ብዙ የለውጥ ተስፈኛ ወንድም እና እህቶችን ባጭር ያስቀረ ፤ እባት እናቶቻችንን ያሳጣን፤ የትውልዶችን ተስፋ ያከሰመ ፤ እንደ ሀገር ለከፋ ድህነት እና ኋላ ቀርነት የዳረገን ፤ ይህንንም ዕጣ ፈንታችን አድርገን እንድንወስድ ከፍ ያለ ማኅበራዊ ድባቴ ውስጥ የጨመረን የፖለቲካ ውድቀታችን ነው።
ከዚህ የፖለቲካ ውድቀት ለመውጣት እንደ ሕዝብ ከነጻ አውጪነት ግጥም እና ዜማ በስተጀርባ ያሉ ተጨባጭ እውነታዎችን ዓይናችንን ከፍተን ልናይ፤ ከትናንት የነጻነት ክሽፈት ታሪካችን ልንማር ይገባል። ከሁሉም በላይ የነጻነታችን ባለቤቶች እኛ መሆናችንን ፤ ይህንን ማስተዋል የምንችል ትውልድ መሆናችንን በተግባር ማሳየት፤ ለዚህ የሚሆን ቁርጠኝነት መፍጠር ይጠበቅብናል!
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም