
አዲስ አበባ፡- በአማራ ክልል አንድ ሚሊዮን 432 ሺህ 642 ቶን ተኪ ምርት በማምረት 113 ሚሊዮን 117 ሺህ 736 ዶላር ማዳን መቻሉንም ተገለጸ።
የቢሮው የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዝናው አበበ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ከውጭ የሚገቡ ማዕድናት በሀገር ውስጥ ማዕድናት ለመተካት በተያዘው ግብ በ10 ወራት 268 ሺህ 717 ነጥብ 5 ቶን የኢንዱስትሪ ማዕድን ውጤቶችን በመተካት፣ 52 ሚሊዮን 692 ሺህ 150 ዶላር የውጭ ምንዛሬን ለማዳን ታቅዶ ፤ አንድ ሚሊዮን 432 ሺህ 642 ቶን ምርት በመተካት 113 ሚሊዮን 117 ሺህ 736 ዶላር ማዳን ተችሏል። አፈጻፀም ከዓመታዊ እቅዱም በላይ የተፈጸመ መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 60 ሺህ 955 ነጥብ 714 ብር ከሮያሊቲ፣ ከመሬት ኪራይ፣ እና ሌሎች ተዛማጅ አገልግሎት ክፍያዎች ለመሰብሰብ ዕቅድ ተይዞ 68 ሚሊዮን 833 ሺህ 944 ነጥብ 93 ብር ተሰብስቧል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አፈጻጸሙም ከ10 ወሩ እቅድ ከ 100 በመቶ በላይ ሲሆን፣ የዓመታዊ እቅዱን 84 ነጥብ 7 ይሸፍናል። ባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻፀር የ 34 ነጥብ 3 በመቶ ብልጫ እንዳለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የአማራ ክልል በበጀት ዓመቱም 10 ወራት ከማዕድን 9 ሚሊዮን 034 ሺህ 539 ነጥብ 18 ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን አመልክተው፤ 8 ሺህ 768 ነጥብ 98 ኪ.ግ ምርት ወደ ውጭ መላክ ተችሏል። በዚህም 9 ሚሊዮን 034 ሺህ 539 ነጥብ 18 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል። አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ44 ነጥብ 5 በመቶ ብልጫ ማሳየቱንም አመልክተዋል።
በበጀት ዓመቱ 10 ወራት 18 ሺህ 779 ነጥብ 5 ኪ.ግ የጌጣጌጥ ማዕድናት ለማምረት ታቅዶ 23 ሺህ 558 ነጥብ 8 ኪ.ግ ማምረት ተችሏል ያሉት አቶ ዝናቡ፤ ከዚህ ውስጥ 8 ሺህ 768 ነጥብ 98 ኪ.ግ ምርት ወደ ውጭ በመላክ 9 ሚሊዮን 034 ሺህ 539 ነጥብ 18 ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱን ጠቁመዋል።
ከገቢው 64 ነጥብ 7 በመቶ ከወርቅ የተገኘ ምንዛሬ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ10 ወራት 45 ኪ.ግ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ 3 ሚሊዮን 587 ሺህ 742 ነጥብ 3 ዶላር ለማስገኘት ዕቅድ ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል። ከእቅድ በላይ 75 ነጥብ 9 ኪ.ግ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ በማስገባት 5 ሚሊዮን 842 ሺህ 817 ነጥብ 96 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ተገኝቷል ብለዋል።
እንደ አቶ ዝናው አበበ ገለጻ፤ የቢሮው አጠቃላይ የ10 ወራት አፈጻጸም በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ ላይ ይገኛል።
ለውጤቱ መገኘትም አደረጃጀቶችን በጥብቅ ዲስፕሊን እየገመገሙ መምራት፣ ከታችኛው መዋቅር ጋር የሚኖርን ግንኙነትና መረጃ ሰንሰለት መጠናከር፣ በየደረጃው ተግባራትን የመገምገሚያ ጊዜ ሰሌዳ በማስቀመጥ እየገመገሙ መምራት መቻሉን በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም