
አሰላ ፡- በክልሉ ቀደም ሲል የተጀመሩ 2 ሺህ 645 አነስተኛ እና ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች መጠናቀቃቸውን የኦሮሚያ ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) አስታወቁ::
የኦሮሚያ ክልል ውሃ እና ኢነርጂ ቢሮና የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ በምዕራብ አርሲ፣ በባሌና በአርሲ ዞኖች ለሚዲያ አመራሮችና ለጋዜጠኞች ያዘጋጁት የአምስት ቀናት ጉብኝት ከትናንት በስቲያ ተጠናቋል
የተጓተቱ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች የሥራ ሂደትና ውጤት ምን ይመስላል? ተጠናቀው ወደ ሥራ የገቡትስ እየሰጡ ያለው አገልግሎት እንዴት ይታያል? የሚሉት የጉብኝቱ ዋና ጉዳዮች መሆናቸውን ኢንጂነሯ አንስተዋል
በጉብኝቱ ማጠቃለያ ለጋዘጠኞች መግለጫ የሰጡት ኢንጂነሯ፤ በክልሉ መንግሥት፣ በዞኖች፣ በወረዳዎች፣ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማትና በህብረተሰቡ ተሳትፎና ትብብር ቀደም ሲል ተጀምረው የነበሩ ከ 3 ሺህ 600 በላይ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ ታስቦ 2 ሺህ 645 የውሃ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ተችሏል ብለዋል በዚህም ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የክልሉ ነዋሪዎች ንጹህ የመጠጥ ውሃ ማግኘታቸውን ገልጸዋል
ሙሉ ለሙሉ ካልተጠናቀቁት ውስጥ እንደ ሀሎ ጎባ ፣ ነጆ፣ ካለቻ አርበቴ፣ ቁኔ ፣ ደደር፣ ቆንዳላ ፣ ሀሮ ዋጮ፣ እና ሌሎችም በርከት ያሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ከ90 በመቶ በላይ እንደሆነ ገልጸው፤ እነዚህም በሚቀጥለው አንድ ወር ውስጥ የሚጠናቀቁ መሆናቸውን አመልክተዋል
ፕሮጀክቶቹ የተጓተቱት በግብዓት አቅርቦት ችግር እንደሆነ ተናግረው፤ አሁን ችግሩ መቀረፉን ተከትሎ ጠዋትና ማታ ተሠርተው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁ ናቸው ብለዋል የቢሮው ሙያተኞችና ኃላፊዎችም ከቢሮ ወጥተው ሥራው ቦታ ድረስ በመገኘት ክትትል እና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል
የሄበን- ነጌሌ- ሲራሮ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ የአሳሳ ዶዶላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ የባሌ ዞን ሮቤ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና የሚኦ- አጋርፋ -ጋሠራ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና የሉቁጬ- አሰላ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት እና የአሰላ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ፕሮጀክቶች አበረታች ውጤት የታየባቸው እንደሆኑና ለሌሎች የሚተርፍ መልካም ተሞክሮዎች ያላቸው መሆኑን በጉብኝቱ መረዳት እንደተቻለ ጠቅሰዋል
አንዳንድ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በሌሎች የሥራ ዘርፎች ኢንቨስት በማድረግ የገቢ ምንጫቸውን አሳድገው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እያደረጉ ያሉት ጥረት በመልካም ምሳሌነት የሚጠቀስ እንደሆነ አንስተዋል ለአብነትም በሆቴል ሥራ ፣ በንብ ማነብ ሥራና በሌሎችም ሥራዎች የተሠማሩ የመጠጥ ውሃ ተቋማትን በጉብኝቱ መመልክት እንደተቻለ ገልጸዋል
ህብረተሰቡ በአንዳንድ ቦታዎች የሚስተዋሉ የፕሮጀክቶች መጓተትን በትዕግስት መጠበቁ እና በልማቱ ላይ ተሳትፎ ማድረጉም የሚያስመሰግን እንደሆነ ጠቅሰዋል ለአብነትም የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት በውሃ ላይ ታሪፍ በመጨመር ባደረጉት የገንዘብ ድጋፍ ችግራቸውን መፍታታቸው ያስመሰግናቸዋል ብለዋል
የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት፣ የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ቢሮ እና የኦሮሚያ ገንዘብ ቢሮ ለነበራቸው ድጋፍና አጋርነት ሚሊዮን በቀለ (ኢ/ር) ምስጋና አቅርበዋል
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም