
-የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳቸውን ለምክክር ኮሚሽኑ አስረከቡ
አዲስ አበባ፡- የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ማስረከባቸውን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ገለጹ። የፌዴራል ተቋማትና ማህበራት የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በስኬት መጠናቀቁንም አመልክተዋል
ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ የምክክሩን መጠናቀቅ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ በምክክር ምዕራፉ ከ38 በላይ ተቋማት መሳተፋቸውን ጠቁመው፣ እስካሁን የተሰበሰቡ ሁሉም አጀንዳዎች ወደ ኮሚሽኑ ቋት ገብተዋል። በቀጣይ በሚካሄደው ዋና የምክክር ጉባዔ አጀንዳዎቹ መግባባት ላይ ይደረስባቸዋል ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በ11 ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ማካሄዱን አውስተው፤ 14ኛውን የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በፌዴራል ተቋማትና በማህበራት ደረጃ መካሄዱንና ይህም ስኬታማ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሦስት ቀናት በቆየው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ላይ የነበሩት የፌዴራል ተቋማት እና ማኅበራት አጀንዳቸውን ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ አስረክበዋል።
በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት አጀንዳ የማሰባሰብ መርሃ ግብርም በቀጣይ የሚከወን ቀሪ ሥራ መሆኑን አመልክተው፤ እስካሁን በሂደቱ ያልተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ወገኖች አጀንዳዎቻቸውን ወደ ምክክር ቋቱ እንዲያስገቡ ጥሪ አቅርበዋል
በቀጣይ የትግራይ ክልልን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠራ ጠቁመው፣ ምክክሩ አካታች እንደመሆኑ መጠን የትግራይ ክልልን ሳንይዝ የምክክሩ ስኬት የሚታሰብ አይደለም ብለዋል
የተጠናቀቀው የፌዴራል ተቋማት እና ማህበራት አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አጀንዳ ርክክብ፤ ተቋማቱ የተዋሃደ አጀንዳዎችን ማቅረብ የቻሉበት መሆኑንም ተናግረዋል
ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ በበኩላቸው የተቋማቱ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት የነቃ ተሳትፎ ተደርጎበታል የምክክር ሂደቱ በማያግባቡን ጉዳዮች ላይ መነጋገር እና ለጋራ ችግሮቻችን በአንድነት መፍትሄ መፈለግ እንደምንችል በተጨባጭ ያሳየ ነው ብለዋል።
በየደረጃው የተካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ስኬታማ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሯ፣ እስካሁን ባለን ግንዛቤ ባሳታፊነት፣ በአካታችነቱ እና በስፋቱ በዓለማችን ከተካሄዱ ሀገራዊ ምክክሮች ሁሉ የኢትዮጵያ ትልቁ ይሆናል የሚል እምነት ይዘናል ብለዋል።
ማንኛውም ጉዳይ በአንድ ጀንበር ተጀምሮ እንደማይጠናቀቅ የገለፁት ምክትል ዋና ከሚሽነሯ፤ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክርም በአጀንዳዎቹ ላይ ከታች ጀምሮ መግባባት እየተፈጠረበት የመጣ ስለሆነ መጨረሻው ያማረ ይሆናል ብለው እንደሚያምኑ ገልፀዋል።
ተስፋ ፈሩ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም