
ዜና ትንታኔ
ከግንቦት 1985 ዓ.ም ጀምሮ ኤርትራ አዲስ ሀገር በመሆኗ፤ ኢትዮጵያ የራሷን የባሕር በር ሙሉ ለሙሉ አጣች ይህን ተከትሎ ከሌሎች ወደቦች ጋር ሲነፃፀር እጅግ የተጋነነ ዋጋን ለወደብ ኪራይ እየከፈለች ለ30 ዓመታት ያለባሕር በር ቆየች ኢትዮጵያ 95 በመቶ የሚሆነውን የውጪ ምርት የምታስገባው በጅቡቲ በኩል ብቻ ነበር ይህ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ከሚፈጥረው ተፅዕኖ ባሻገር፤ ደህንነቷንም ስጋት ላይ የሚጥል በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከአንድ ዓመት በፊት የባሕር በር የኢትዮጵያ አገብጋቢ ጥያቄ መሆኑን ይፋ አደረጉ፡፡
ኢትዮጵያ ሃሳቡን በማቅረቧ ብዙዎች በቅራኔ የተሞሉ አስተያየቶችን መሰንዘር ጀመሩ የሌሎች ሉዓላዊ ሀገሮችን ከመውረር ጋር አያያዙት ይሁንና ሃሳቡ ከቀረበ በኋላ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሰከነ መልኩ ጥያቄው መቅረቡ ተገቢ መሆኑን እና ዓለም አቀፍ ሕግን ተከትሎ ጥረት ሊደረግ እንደሚገባ የተለያዩ ባለሙያዎች ሃሳብ በመስጠት ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ የባሕር በር ፍለጋ ጉዞን በተመለከተ ጥናት ያደረጉት የአውሮፓ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሚኒስቴር፤ የሕግ አማካሪ እና የአውሮፓ እና ዓለም አቀፍ ሕግ የክብር ፕሮፌሰር አምባሳደር ግሬጎር ሹስተርቺትስ እንደተናገሩት፤ ዓለም አቀፍ ሕጉ በፍትሃዊ መንገድ ወደብ የሌላቸው ሀገራት ወደ ባሕር የመግባት መብት ይሰጣል
የተባበሩት መንግሥታት የባሕር ሕግ ኮንቬንሽን (UNCLOS) አንቀጽ 25 ወደብ የሌላቸው ሀገሮች ወደ ባሕር የመግባት መብት አላቸው ይላል። ይህ ማለት ወደብ የሌላቸው ሀገሮች ወደ ባሕር የመግባት እና የመውጣት እንዲሁም የመተላለፊያ ሀገሮችን የመጠቀም መብት አላቸው ሲሉ አምባሳደሩ ይናገራሉ። ይህ የሚፈፀምበት ሁኔታን በተመለከተ እንደገለፁት፤ ወደብ በሌላቸው ሀገሮች እና የባሕር ዳርቻዎች ባሏቸው ሀገራት መካከል መስማማት መኖር አለበት ይላሉ።
በዋናነት የባሕር በር የሌላቸው ሀገሮች ወደቦችን ማግኘት እና ያለ ገደብ ወደ ባሕሩ የመግባት ዋስትና ሊኖራቸው እንደሚገባ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያ በአንድ ሀገር ላይ ጥገኛ መሆኗ፤ አስተማማኝ እና ቀጣይነት ያለው የባሕር ዳርቻ አገልግሎት እንዳታገኝ ያደርጋታል ሲሉ ተናግረዋል ሌሎች አማራጭ ሀገሮችን ማየት እንዳለባት አመላክተዋል።
በዋናነት የባሕር ተደራሽነት የፍትሃዊነት መርሆዎች የተከተለ ሁሉንም ሀገራት ያገናዘበ መፍትሄዎችን የሚፈልግ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ መግባት እንዳለበት አመልክተው፤ የተለያዩ አማራጮች ከመውሰድ ጋር ተያይዞም በሚኖረው ሂደት፤ የደህንነት ጉዳይ ዋነኛ መሠረቱ ሊሆን እንደሚገባ አብራርተዋል
ይሁንና ብዙዎች ባሕሩን ለማግኘት ኢትዮጵያ ለጅቡቲ እየከፈለች ያለውን ዋጋ ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ዶላር ያላነሰ መሆኑን በማስታወስ፤ ፍትሃዊነት የጎደለው ስለመሆኑ ይናገራሉ
በሌላ በኩል አምባሳደር ግሬጎር፤ የባሕር ዳርቻ ሀገሮች የባሕርን ሀብቶች ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ ለማካሄድ ዕድል እንዳላቸው ያመለክታሉ ይሁንና ይህን ችግር ለማቃለል ስምምነቶችን እና የፍትሃዊነት መርሆዎችን መሠረት በማድረግ በድርድር፣ በቀጣናዊ ትብብር ወይም በሕጋዊ መንገድ የባሕር ላይ ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ አማራጮችን ማሰስ ተገቢ መሆኑን አክለዋል።
‹‹ኢትዮጵያ የባሕር ዳርቻን ለመጠቀም በአንድ ሀገር ላይ ብቻ መተማመን የለባትም። ከብዙ ሀገራት ጋር የተለያዩ አማራጮች አሏት ነገር ግን መንገዶችን ለመፈለግ ጥሩ አካሄድን መከተል እና የባሕር ዳርቻ ተጠቃሚነቷን ለማስቀጠል አስተማማኝ ሁኔታ የሚፈጠርበትን መንገድ በተመለከተ በጥንቃቄ መሥራት አለባት። በጣም ጥሩ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባታል።” ሲሉ ተናግረዋል
‹‹ዓለም አቀፍ ሕግ በሀገራት መካከል በፍትሃዊነት አቀራረብ መርሆዎች ላይ መግባባት ለመፍጠር የሚያደርግ ነው›› ያሉት አምባሳደር ግሬጎር፤ ሕጉ ላይ ተመሥርተው የባሕር ጠረፍ ሀገር ለኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻን ሲሰጡ ከኢኮኖሚ አንፃር ከፍተኛ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አብራርተዋል ምክንያታቸውን ሲገልፁ፤ በሀገራቸው የንግድ ልውውጥ ከማሳደግ በተጨማሪ ሰፊ የሥራ እድል እንደሚፈጠር እና ከሆቴል አገልግሎት ሰጪዎች ጀምሮ ብዙዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል ይፈጠራል ብለዋል
በአውሮፓ ትልቅ ወደብ ያላትን ኦስትሪያን ጠቅሰው፤ ወደብ የሌላት ክሩሺያን እና ከወደብ ጋር ተያይዞ የባለብዙ ወደብ ባለቤት የሆነችዋን በጋራ በፍትሃዊነት በመኖር የምትታወቀዋን ስሎቬንያን ተሞክሮ ማየት ይገባል ብለዋል ፍትሃዊነት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን አስገንዝበዋል
በሲቪል ሠርቪስ ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ ሔኖክ ስዩም (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከወደብ አንፃር ታሪካዊ እና ሕጋዊ መብት ያላት መሆኑን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ ወደብ ያጣችበት ምክንያት እና ጉዳዩ የሚታይበት መንገድ የተለየ ነው ብለዋል
የባሕር በር የሌላቸው 44 ሀገራት ሲሆኑ፤ 16ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው ከአፍሪካ አንፃር ሀገራቱ የሚገናኙት በመሬት ነው ስለዚህ ባሕሩን ማግኘት የሚቻለው መሬትን በመጠቀም ነው ሲሉ ገልፀው፤ በአፍሪካ የተለያዩ መሬት የማግኛ መንገዶች እንዳሉ አስታውሰዋል
የዓለም አቀፍ ሕግም ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት መብት እንዳላት ያስቀምጣል ያሉት ሔኖክ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የምትታወቀው በዓለም ደረጃ የሀገራትን ሉዓላዊነት በማክበር ነው መብቷን ለማስከበር እንደሀገር እና እንደሕዝብ ለሰው ልጆች ሠላም ሲባል ሰላማዊ አማራጮችን ትጠቀማለች ብለዋል ይሁንና የባሕር በርን ከመጠቀም አንፃር መታየት ያለበት፤ የፖለቲካ ፈቃደኝነት ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት ያለው መግባባትን ይፈልጋል ሲሉ አመልክተዋል
በመሠረታዊነት የባሕር በር ማግኘት ጉዳዩ የተነሳው ከጋራ ተጠቃሚነት አንፃር መሆኑን የተናገሩት ሔኖክ (ዶ/ር)፤ የጋራ ገበያን ለማቀላጠፍ ወደብ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አብራርተዋል
እንደ ሔኖክ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ የነፃ ንግድ ግንኙነትን ትፈልጋለች፤ ቀጣይነት ባለው መልኩ ከቀጣናው ጋር እንድትገበያይ የባሕር በር የማግኘት መብቷ መረጋገጥ አለበት ብለዋል
አክለውም የዓለም የባሕር በር ሕግም ሆነ የዓለም ሕዝብ ከኢትዮጵያ 100 ኪሎ ሜትር የማይሞላ ርቀት ላይ ብቻ የሚገኘውን ባሕር ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም ለመከልከል እና 130 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ በር ለመዝጋት ይደፍራሉ ብለው እንደማያስቡ እና ኢትዮጵያም ጥያቄውን ያነሳችው በዚህ የፍትሃዊነት መሠረት ላይ መሆኑን ተናግረዋል
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 25 ቀን 2017 ዓ.ም