አገልግሎት ፈልገው የተገኙ፤ ነገር ግን አገልግሎቱ ርቆባቸው ማግኘት የሚገባቸውን በማጣት የተከፉ ፊቶች፤ በለውጥ ጎዳና ላይ ተሰልፎ በትኩስ ጉልበቱ አገር ለመለወጥ አገር ለመገንባት በሚችሉ እግሮቹ አገልግሎት ተጓትቶበት ደጅ የሚጠና ወጣት ኩርፊያ፤ ባልተገባ መልኩ የተጠየቁትን “አይ! መብቴን አላስነጥቅም!” የሚሉ ጉርምርምታዎች እዚህ በርክተው አሉ፤ ይሰማሉ፡፡
ታግሎ መጣል፣ ሮጦ ማሸነፍ፣ ሠርቶ መለወጥ የሚቻልበት፤ በሰው ልጅ ህይወት ምርጥና ወሳኙ የዕድሜ ክልል ወጣትነት ነው፡፡ የወጣትን ጉልበት እንደ አገር ታስቦና መልክ ባለው መልኩ ከተጠቀሙበት ሀገርን በመለወጥ ሂደት ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት የሚቻልበትና ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረ ቀጣይነት ያለው ለውጥ ማስመዝገብ የሚያስችል ነው፡፡
የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ በመንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶበት እየተሠራ ቢሆንም፤ በአፈፃፀሙ ላይ ችግሮች መታየታቸው አልቀረም፡፡ ወጣቶች በሀገር ግንባታ ተሳታፊና ምርታማ እንዲሆኑ ሥራን በመፍጠር የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት እንዲቀይሩ አላማ አድረጎ የተነሳው የወጣቶች ሥራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት እንደሚያሻው ለመጠቆም አመላካች ነጥቦችን ማሳየት ፈለግን፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጽህፈት ቤት ባለጉዳዮችን ማስተናገድ ተለምዷዊ ተግባር ቢሆንም፤ በተለየ መልኩ ግቢውን በወረፋ የሞላው የመታወቂያ ጠያቂዎችና በመደራጀት ራሳቸውን ለመለወጥ ፍላጎት ኖሯቸው ለዚያ የሚያስፈልገው ሂደት በማስኬድ ላይ ያሉ ወጣቶችና ባለጉዳዮች በርክተዋል፡፡ በጽህፈት ቤቱ አገልግሎት አሰጣጥ ሳይረኩ ቀርተው ቅሬታ ሲያቀርቡ የነበሩ ወጣቶች ቁጥራቸው ከፍ ይላል፡፡
በአዲስ አበባ አስተዳደር ለበጀት ዓመቱ በልዩ ሁኔታ ለሥራ አጥ የከተማዋ ኗሪዎች፤ በተለይም ለወጣቶች ሥራ መፍጠር ያስችላል የተባለለትን ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ በጀት ያላግባብ የግል ጥቅማቸውን ለሚያሳድዱና ለማይገባቸው ሰዎች እየዋለ መሆኑ በመደራጀት ሂደት ላይ ያሉ ወጣቶች ይናገራሉ፡፡ ወጣቶቹ ከእነሱ በተሻለ ኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና የራሳቸው ሥራና ጥሩ ገቢ ያላቸው ግለሰቦች የሥራ አጥ መታወቂያ በማውጣት ቅድሚያ እየተስተናገዱ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በወረዳው ቅጥር ግቢ ውስጥ አግኝቼ ስለ አገልግሎቱ የጠየቅነው በመደራጀት ሂደት ላይ ያለና ስሙን መግለፅ ያልፈለገ ወጣት በአደረጃጀት ሂደቱ እየተፈፀሙ ናቸው ያላቸው ስህተቶች ይዘረዝራል፡፡ በወረዳው ውስጥ የሚገኙ ፈፃሚዎች ሥራቸውን በአግባቡ እየሠሩ አይደለም። በአደረጃጀት ሂደቱ ጉዳዮችን በማጓተት ብዙ ጊዜ ይፈጃሉ፤ ብድር ቅድሚያ ለማግኘት ብር ክፈሉ ይባላል በማለት ሐሳቡን ይገልፃል፡፡
ወጣት ዝናሽ ደሳለኝ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ኗሪ ስትሆን መንግሥት ባቀረበው ዕድል ተጠቃሚ ለመሆን ከጓደኞቿ ጋር ለመደራጀት የሚያበቃትን ሂደት ከጨረሰች ከሁለት ወር በላይ ቢሆናትም የብድር አገልግሎቱ የተቀላጠፈ ባለመሆኑ ችግር ላይ መሆንዋን ትናገራለች፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለመደራጀት መስፈርቱን ያሟሉ ወጣቶች የብድር ሂደቱ ጊዜ የሚፈጅ በመሆኑ መቸገራቸውንም አመልክተዋል፡፡ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የወረዳ 13 ነዋሪ ነው ሰለሞን በላይ ይባላል። ለመደራጀትና ወደ ሥራ ለመግባት አራት ወር የፈጀ ጊዜና ተደጋጋሚ ጥረት እንደወሰደበት ይናገራል፡፡ በወረዳው ውስጥ በማደራጀት ሂደት ላይ ያሉ ፈፃሚዎች ለመደራጀት ወደ ጽህፈት ቤቱ የሚመጡ ወጣቶችን በቀናነት ተቀብሎ የማስተናገድ ልምድ የላቸውም በማለት በማደራጀት ሂደት ላይ ያለውን ችግር ይገልፃል፡፡
በአደረጃጀት ሂደቱ ላይ ትልቅ ቅሬታ ፈጥሮብኛል ያለው ሌላኛው ጉዳይ የብድር አሰጣጡ መሆኑን የገለጸው ሰለሞን፤ የአደረጃጀት ሂደቱን ተከትሎ የጨረሰና ወደብድር ወይም የገንዘብ ሂደት ውስጥ የገባ ተደራጅ ትዕግስት የሚጠይቅ ማመላለስና የብድር ሂደቱን ማዘግየት ችግር እንዳለ ይገልፃል፡፡ ብድር ለማግኘትም ፈፃሚዎቹ ገንዘብ እንደሚጠይቁም ይናገራል፡፡
በወጣቶቹ በሚነሱ አጠቃላይ ቅሬታዎች ላይ ምላሽ የሰጡት አቶ አማረ መርሻ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ጽህፈት ቤት የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ሃላፊ ናቸው፡፡ ሃላፊው የአገልግሎቱ መዘግየት እና እንደቀድሞው ቀልጣፋ አለመሆኑ ምክንያት በመንግሥት የተመደበውን በጀት ተከትሎ ወደ ጽህፈት ቤቱ የሚመጣ ተገልጋይ ቁጥር መጨመር መሆኑን ይገልፃሉ፡፡
ሥራ አስፈፃሚው በፈፃሚዎች ለሥራው መቀላጠፍ ተብሎ ያላግባብ ገንዘብ ይጠይቃል መባሉን እስካሁን በጽህፈት ቤት ደረጃ ጥቆማ አለመቅረቡን ገልፀው ተገልጋዮች መብታቸው በሕግ አግባብ ማስከበር እንጂ፤ ባልተገባ መንገድ የሚጠየቁትን ገንዘብ ከመስጠት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡ በጽህፈት ቤት ደረጃም ጉዳዩን በተመለከተ የማጣራትና ችግሩ ካለ እርምጃ የመውሰድ ሥራ እንደሚሠራም አመልክተዋል፡፡
በዚህ ዓመት በመዲናዋ ለሥራ አጥ ወጣቶች የተበጀተውን ሁለት ቢሊዮን ብር የተመለከተ ጉዳይ ለማሳያነት አነሳን እንጂ፤ በሀገር ደረጃ ከሁለት ዓመት በፊት የወጣቶችን ሥራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ታስቦ በ2009 የተበጀተው 10 ቢሊዮን ብር የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ በአስፈፃሚ አካላት የቅንጅት ሥራ አለመኖር የታለመለትን ውጤት አለማስመዝገቡን ተጠቃሚ ወጣቶችና ክልሎች ማመላከታቸውን የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነበር፡፡
በዚህ ዘርፍ ግምባር ቀደም ተዋናዩ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር ከተመደበው ገንዘብ 91.3 በመቶ ወይም ዘጠኝ ቢሊዮን 125 ሚሊዮን 757 ሺህ 385.24 ብር ለክልሎች መልቀቁን ገልፆ፤ አፈፃፀሙን መከታተልና ቁጥጥር ማድረግ የራሳቸው የክልሎቹ ድርሻ መሆኑን ቢገልጽም ሃላፊነቱ ታዲያ የማን ነው የሚያስብል ጥያቄን በሰሚው ዘንድ ፈጥሯል፡፡ ይህ ግዙፍ በጀት የተያዘለት የወጣቶች ፈንድ ተዘዋዋሪና ቀጣይ እንደመሆኑ መጠን ተገቢ ክትትልና ድጋፍ የሚያስፈልገው ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ተዘዋዋሪ ፈንዱ በዋናነት በፌደራል መንግሥት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደረጃ እንዲመራና ክልሎች ደግሞ በክልል ፕሬዚዳንቶች እንዲመሩ የተደረገው ለጉዳዩ ትልቅነት ዋጋ ተሰጥቶት መሆኑን ለጉዳዩ መንግሥት የሰጠው ልዩ ትኩረት ቢያመለክትም፤ ክትትልና ቁጥጥሩ ላይ ግን ውስንነት እንዳለ በአፈፃፀም ላይ የታዩ ችግሮች አመላካች ናቸው፡፡
ክልሎች ተዘዋዋሪ ፈንዱ ለወጣቶች ስኬት ላይ መድረስ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸው የሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሐጂ ኢብሳ ይናገራሉ፡፡ መሥሪያ ቤታቸው ለክልሎች የተበጀተላቸውን ገንዘብ ወቅቱን ጠብቆ ከመሥራት ባለፈ የሚያደርገው ክትትልና ቁጥጥር አለመኖሩን፤ ይህም የመሥሪያ ቤታቸው ሃላፊነትና ተግባር ባለመሆኑ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የተያዘውን ይህንን ከፍተኛ በጀት የተያዘለትና ሲሠራበት የቆየው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ሥራውን በመቆጣጠርና በመምራት ላይ ያለው የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር ሥራውን ክልሎች በተገቢው መልኩ እየመሩት አለመሆኑ መግለፁም ይታወሳል፡፡
አቶ ብርሃኑ ፋንታዬ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስቴር የወጣቶች ማሳተፍና የሥራ ዕድል ፈጠራ ባለሙያ ሲሆኑ፤ ተዘዋዋሪ ፈንዱ የተፈለገውን አላማ እናዳያሳካ የቅንጅት አለመኖር፤ ወጣቶቹን ውጤታማ በሆኑ የሥራ መስኮች አለማሰማራትና የክልሎች አፈፃፀም አነስተኛ መሆን ዋንኛ ችግሮች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ክትትል በማድረግ ላይ በባለሙያነት የሚሠሩት አቶ ብርሃኑ፤ ክልሎች ተዘዋዋሪ ፈንዱ ስኬታማ እንዲሆን ትኩረት ሰጥተው አለመሥራታቸውን አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ በጥናት ላይ የተመሰረት የወጣቶች ፍላጎት ዳሰሳ ማድረግና አዋጭ የሥራ መስክ መርጦ መተግበር ሲገባው በተቋማት መካከል ተናብቦ ያለመሥራት የሚፈለገውን ውጤት ማግኘት እንዳላስቻለ ይገልፃሉ፡፡
አካባቢን መሰረት ያረጉና አዋጭ የሥራ መስኮች በመለየትና ስልጠና በመስጠት ወደ ሥራ አለማስገባት፤ ምቹ የብድር አገልግሎት አለማመቻቸታቸውና ወደ ሥራው የገቡትን ወጣቶች በቂ ክትትልና ድጋፍ ያለማድረግ በባለሙያ የተነሱ የክልሎቹ ዋነኛ ችግሮችና ነጥቦች ናቸው፡፡
ሥራ-አጥ ወጣቶች ያለባቸውን ዘርፈ ብዙ ችግር ለመቅረፍ የተበጀተው ተዘዋዋሪ ፈንድ እንዲያዳርሱና ሥራ ፈጥረው ወደተግባር የተሰማሩ ወጣቶችን ድጋፍ በማድረግ ውጤታማ እንዲሆኑ የማስቻል የተጣለባቸው ክልሎች ሥራቸውን በአገባቡ መወጣት ሲጠበቅባቸው የተሰጣቸውን ሃላፊነት በመዘንጋት ተዘዋዋሪ ፈንዱ ለታለመለት ዓላማ ሳይውልና ዕቅዱም ግቡን ሳይመታ ቀርቷል፡፡
በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል የሥራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕርይዞች ልማት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ተሰማ በበኩላቸው፤ ለወጣቶች የተመደበው ተዘዋዋሪ ፈንድ የተፈለገውን ያህል ስኬታማ እንዳልሆነ ያስረዳሉ፡፡ ይህም የሆነው በክልሎችና በፌደራል ደራጃ ባለው የአሠራር ጉድለትና የቅንጅት ችግር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በተጨማሪም፤ ለክልሎች በጀት በአስፈላጊና በተገቢው ሰዓት አለመለቀቁ፤ ወጣቶችን ለማደራጀት የወጡ መስፈርቶች ለወጣቶቹ አስቸጋሪ መሆናቸውና ወጣቶቹ ሥራ ከመጀመራቸው በፊት ተገቢውን ስልጠና ያለማግኘታቸው ዋንኛ ችግር ናቸው ብለው ይገልፃሉ፡፡
በአጠቃላይ በዘርፉ የሚታዩትን ችግሮች ለይቶ በመቅረፍ ወጣቶች በተመቻቸው ዕድል ተጠቅመው በሀገር ግንባታው የራሳቸውን ጉልህ ሚና መጫወት እንዲችሉ ለሥራ ዕድል ፈጠራው ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠውና አፈፃፀሙም ክትትል ያስፈልገዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2011
ተገኝ ብሩ