ቱርክዬ አውሮፕላን ከመቆሙ በፊት የሚነሱ ተሳፋሪዎችን ልትቀጣ ነው

ወደ ቱርክዬ የሚጓዙ መንገደኞች የአውሮፕላኑ የመቀመጫ ቀበቶ ምልክት ከመጥፋቱ በፊት ከተነሱ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው ተቆጣጣሪዎች ገለጹ። የቱርክዬ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ትዕዛዙን ያስተላለፈው ከተሳፋሪዎች ቅሬታ ከደረሰው በኋላ መሆኑን አስታውቋል።

ሕጎቹ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ተግባራዊ ሆነዋል። ባለሥልጣኑ ሕጎቹን የተላለፉ ቅጣቱ ምን እንደሆነ በመመሪያው ውስጥ ባይጠቅስም፣ 70 ዶላር ገደማ እንደሆነ የቱርክዬ ሚዲያዎች ዘግበዋል። እንዲህ አይነት ክስተቶች “በከፍተኛ ሁኔታ” መጨመራቸውን ያስጠነቀቀው ባለሥልጣኑ አውሮፕላኑ ከማረፉ በፊት ከመቀመጫዎች በላይ ያለውን የሻንጣ ማስቀመጫ በርካታ መንገደኞች እየከፈቱ ነው የሚል በርካታ ቅሬታዎች ደርሶኛል ብሏል።

ቱርክዬ በዓመት በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቱሪስቶችን ታስተናግዳለች። አየር መንገዶች በበራዎች የውስጥ ማስታወቂያዎች ትዕዛዙን ማስተላለፍ እንደሚገባቸውና ይህንን ተላልፈው የሚገኙትን ማሳወቅ እንደሚገባቸው የአቪዬሽን ባለሥልጣኑ ተናግሯል። ተሳፋሪዎች የመቀመጫ ቀበቷቸውን ምልክቱ እስኪጠፋ ድረስ እንዳይፈቱ እንዲነገራቸው እና በመቀመጫቸው በላይ ያለውን የሻንጣዎች ማስቀመጫ ከመክፈት ይታቀቡ ተብለዋል።

እነዚህን ሕጎች የማይከተሉ መንገደኞች ለባለሥልጣኑ ሪፖርት ሊደረጉ ይገባል ብሏል። ብሔራዊው የቱርክዬ አየር መንገድ የበረራዎች ማስታወቂያውን እንዳሻሻለ ዩሮ ኒውስ ዘግቧል። “በሕ ጎቹ የማይመሩ መንገደኞች ረብሻ በመፍጠር ለሲቪል አቪዬሽን ዳይሬክቶሬት ሪፖርት ይደረጋሉ በሕጉ መሠረትም አስተዳደራዊ ቅጣት ይጠብቃቸዋል” የሚል ማስጠንቀቂያ በበራራ አስተናጋጆች መነገሩን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You