የዓባይ ግድብን ከደለል ለመከላከል የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት መሥራት ያስፈልጋል

አዲስ አበባ፡- የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች የዓባይ ግድብን በዘላቂነት ከደለል ለመከላከል የተቀናጀ የተፋሰስ ልማት ሥራ ሊሠሩ እንደሚገባ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ገለፀ።

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አረጋዊ በርሄ (ዶ/ር) “አንድ ዕቅድ፤ አንድ ሪፖርት ለተቀናጀ የዓባይ ተፋሰስ ልማት የሲቪክ ማህበራት ሚና” በሚል መሪ ሃሳብ ከሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር ትናንት ውይይት ሲካሄድ እንደተናገሩት፤ የዓባይ ግድብ በደለል ሳይሞላ ዘላቂ አገልግሎት እንዲሰጥ የተፋሰስ ልማት ሥራ በቅንጅት መሥራት ቁልፍ ጉዳይ ነው።

የዓባይ ግድብ ላለፉት 14 ዓመታት ሁሉም ኢትዮጵያውያን በጋራ ስሜት በመሳተፍ እና የተለያዩ ጫናዎችን በመቋቋም የመጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ እንዲደርስ አድርገዋል ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዓባይ ግድብ መጠናቀቁ በሁሉም ዜጋ ላይ የይቻላል መንፈስ እንዲፈጠር እና ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን ሥራ ከዳር ሳያደርሱ የማያቋርጡ መሆናቸውን አሳይቷል ብለዋል፡፡

የዓባይ ግድብን ከማጠናቅ በዘለለ ዘላቂነት እና ቀጣይነት እንዲኖረው የተፋስሰ ልማት ሥራ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ መሆኑን አመልክተው፤ የዓባይ ግድቡ በደለል ሳይሞላ ውሃ የመያዝ አቅሙ ከፍተኛ ሆኖ ለቀጣይ ትውልድ እንዲሻገር የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያም የሲቪክ ማህበራት የአካባቢ ጥበቃና ልማት ሥራን በተናጠል ከመሥራት ይልቅ ፎረም በማቋቋም በጋራ መሥራታቸው ለሥራው ውጤታማነት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

አረጋዊ (ዶ/ር) የቴክኒክ ሥራዎች ተጠናቀው በቅርብ ጊዜ የዓባይ ግድብ ተፋሰስ ልማት ፎረም እንደሚመሠረት ጠቁመው፤ የፎረሙ መቋቋም የተፋሰስ ሥራዎችን በቅንጅት ለመሥራት እና ለመቆጣጠር ያስችላል ብለዋል።

የውሃና መሬት ሀብት ልማት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ጌቱ ዘለቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ወደ ሃይቆች እና ወንዞች የሚገቡ ውሃዎች ብዙ ጊዜ የሚመጡት ከተፋሰስ ልማት ሥራዎች ቢሆንም የሚሰጠው ትኩረት ዝቅተኛ ነው፡፡ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችና ውሃ አስተዳደር ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡

ቅንጅታዊ አሠራሩን ውጤታማ ለማድረግ ፎረም መመሥረት ተገቢ መሆኑን በመጠቆም፤ ፎረሙ ከተመሠረተ በኋላ የተፋሰስ ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ላይ አርአያ የሚሆን ሥራ መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ስኬትም ሁሉም የሲቪክ ማህበራት ባለሙያ አዋጥተው ሊያሠለጥኑ ይገባል፡፡ በተጨማሪም መሪ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ይህን ሥራ ሊያሳልጥ እንደሚገባ ምክረ ሃሳብ ሰጥተዋል፡፡

የ 10 ዓመቱ የአረንጓዴ ልማት እቅድ ተግባራዊነት ላይ የተወሰነ ክፍተቶች ቢኖሩትም በመርህ ደረጃ ቅንጅታዊ አሠራርን የሚያበረታታ መሆኑን በመግለጽ፤ የዓባይ ግደብን የተፋሰስ ልማት ቅንጅታዊ ከማድረግ አንጻር እቅዱን መነሻ አድርጎ መሥራት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

ማህበራቱ የገንዘብ ፈንድ ከማግኘት አንጻር፤ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን በተወሰነ አካባቢ በመጀመር ውጤቱን እያዩ ሊያሳድጉ እንደሚገባ ጠቁመው፤ የሚሠሩ የተፋሰስ ልማት ሥራዎችን ውጤታማ ማድረግ ገንዘብ ፈንድ የሚያደርጉ አካላትን በዘላቂነት እንዲረዱ ለማድረግ እንደሚያግዝም አመልክተዋል፡፡

ዓመለወርቅ ከበደ

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You