አዲስ አበባ፡- በኦሮሚያ ክልል 40 ከመቶ የሚሆነው መሬት በአሲዳማነት በመጠቃቱ ከወዲሁ እልባት ካልተበጀለት በቀጣይ በምርትና ምርታማነት መቀነስ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ተገለፀ፡፡
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈቶ ኢስሞ እንደገለፁት፣ ከክልሉ መሬት 40 ከመቶ የሚሆነው በአሲዳማነት የተጠቃ ሲሆን፣ በምርታማነት ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአፈር አሲዳማነት የተጠቃው መሬት እንዲያገግም ካልተደረገና ችግሩ በዚሁ ሁኔታ የሚቀጥል ከሆነ ምርታማነትን መቶ በመቶ ሊቀንስ ይችላል፡፡ ከ10 እስከ 15 ዓመታት ውስጥ 78 ከመቶ የሚሆነው መሬት በአሲዳማነት ሊጠቃ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
አሲዳማነት በክልሉ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ቢሆንም በጥናትና ምርምር በመታገዝ መፍትሄ ለማስቀመጥ ጥረቶች መጀመራቸውን የተናገሩት አቶ ፈቶ በአሲዳማነት የተጠቃው መሬት ባለበት ሁኔታ ላይም ነፃ ለማውጣት ትኩረት መደረጉን ገልጸዋል። ሌላው መሬትም በአሲዳማነት እንዳይጠቃ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በተፈለገው መጠን ባይሆንም ድንጋይ ሰባብሮ አሲዳማነትን የሚከላከል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በአሲዳማነት የተጠቃው መሬት ኖራ በመጨመር አሁን ባለው ምርታማነት ላይ በአንድ ሄክታር መሬት ላይ አስር ኩንታል ምርት መጨመር እንደሚቻል ገልፀዋል፡፡ ይሁንና በሳይንስ ሳይረጋገጥ አፈር አሲዳማነት ተጠቅቷል በሚል እሳቤ ብቻ ኖራ መጨመር እንደማይገባ አሳስበዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ የባለሙያዎች ምክር ያልታከለበትን አሰራር መተግበርም አስፈላጊ እንዳልሆነና በአሲዳማነት የተጠቃን መሬት ኖራ መጨመር ካስፈለገም ሳይንስን መሠረት ያደረገ መሆን አለበት፡፡ ኖራ ከመጨመሩ በፊትም አፈሩ መጠናት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡ የሚጨመረው የኖራ ዓይነት፣ አፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች ግብዓቶችን መጠቀም አስፈላጊነት በሳይንስ ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በአገሪቱ 40 ከመቶ የነበረው የአሲዳማነት ሽፋን ወደ 43 ከመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ስርጭቱ በአገሪቱ ምዕራባዊ ክልል ተወስኖ የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ወደ ሰሜናዊ እና ደቡባዊ የአገሪቱ ክፍሎችም እየተስፋፋ ነው፡፡ በአሲዳማናት የተነሳም አገሪቱ በየዓመቱ ከስንዴ እና ገብስ ምርት ማግኘት የሚገባትን 18 ቢሊዮን ብር ታጣለች፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 6/2011
ክፍለዮሐንስ አንበርብር