
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሀገራቸው ከኢራን ጋር በምታደርገው የኑክሌር ድርድር ከእስራኤል ጋር ጠንካራ የሆነ የጋራ አቋም እንዲኖራቸው እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትሯ ክሪስቲ ኖም ከፕሬዚዳንት ትራምፕ የተላከና ከኢራን ጋር በሚደረገው ድርድር እስራኤልና አሜሪካ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለባቸው የሚገልፅ መልዕክት ለእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ማድረሳቸውን ለ“ፎክስ ኒውስ” (Fox News) የቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል፡፡
አሜሪካና ኢራን አምስተኛውን ዙር የኑክሌር ውይይት በሮም ከተማ ካደረጉ ከቀናት በኋላ ወደ እስራኤል የተጓዙት ኖም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር ግልጽና ቀጥተኛ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸዋል። ሚኒስትሯ ቴል-አቪቭ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ ወደእዚህ የላኩኝ ድርድሮቹ በምን ደረጃ ላይ እንዳሉ እና ሁለታችንም በአንድነት መቆማችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ጋር ለመነጋገር ነው” ብለዋል፡፡
እስራኤል በኢራን የኑክሌር ድርድር ላይ በሚደረጉ ድርድሮች እምነት የላትም፡፡ ኢራን የኑክሌር ቦምብ ልትታጠቅ ጫፍ ላይ እንደደረሰች ደጋግማ በመግለጽ ወታደራዊ ርምጃ እንደምትወስድ ትዝታለች፡፡ የእስራኤል ባለሥልጣናት በቀጣናው እስራኤልን የሚወጉ ታጣቂ ቡድኖችን ትደግፋለች ብለው የሚከሷትን ኢራንን እንደዋና አደጋ ይመለከቷታል፡፡
ኔታንያሁ ኢራንን እንደማያምኑ አሜሪካ እንደምትገነዘብ የተናገሩት ክሪስቲ ኖም፤ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰላምን የሚሹ መሪ እንደሆኑና ኑክሌር ታጣቂ የምትሆን ኢራንን ግን እንደማይታገሱ ተናግረዋል፡፡ “ሰላምን የሚፈልጉ ፕሬዚዳንት እንዳሉንና ፕሬዚዳንቱ ኢራን ኑክሌር መታጠቅ የምትችልበትን አቅም እንደማይታገሱ ለአሜሪካ ሕዝብ መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡ ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ይህ እንዲሆን አይፈቅዱም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁም ከእርሳቸው ጋር የጋራ አቋም እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ” ብለዋል፡፡
ትራምፕ ከቀናት በፊት ሲናገሩ፣ ከኢራን ጋር የሚደረጉት ንግግሮች በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ “ከኢራን ጋር በጣም ጥሩ ውይይት ነበረን። በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት የምነግራችሁ ነገር ጥሩ ይሁን መጥፎ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ግን ጥሩውን እንደምነግራችሁ ይሰማኛል” ማለታቸው ይታወሳል፡፡
“ሲኤንኤን›› (CNN) ባለፈው ሳምንት ባሰራጨው ዘገባ ደግሞ፣ እስራኤል በኢራን የኑክሌር መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ለመፈጸም እየተዘጋጀች እንደነበር ገልጿል፡፡ ጣቢያው ስማቸው ካልተገለጸ የአሜሪካ ባለሥልጣናት አገኘሁት ባለው መረጃ መሠረት፣ እስራኤል በመካሄድ ላይ ያለውን የአሜሪካንና የኢራንን ድርድር ወደ ጎን በማለት በራሷ እቅድና ፍላጎት ኢራንን ለማጥቃት እየተዘጋጀች ነበር፡፡ ኔታንያሁ የአሜሪካን ዲፕሎማሲ ጥረት እያበላሹ መሆኑን የገለጸችው ቴህራንም. ከእስራኤል ለሚሰነዘርባት ማንኛውም ዓይነት ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደምትሰጥ አስታውቃለች፡፡
የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ “የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አሜሪካ ምን ማድረግ እንዳለባትና እንደሌለባት ለማዘዝ ይቃጣቸዋል” ብለዋል።
የፕሬዚዳንት ትራምፕ አስተዳደር ኢራን ዩራኒም ማበልፀጓን ሙሉ በሙሉ እንድታቆም ይፈልጋሉ። ኑክሌሩን የምጠቀመው ለሰላማዊ ግልጋሎት ነው የምትለው ኢራን ደግሞ ዩራኒምን ለኃይል ማመንጫ ማበልጸግ ሉዓላዊ መብቷ እና በዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ያልተከለከለ ተግባር እንደሆነ ትገልጻለች። ከአሜሪካ ጋር በምታደርገው ድርድር ዩራኒየም የማበልጸግ ተግባሯን ለሦስት ዓመታት ያህል ልታቆም ትችላለች ተብሎ የተነገረውን መረጃም “ፍፁም ውሸት” ብላዋለች፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በድጋሚ ወደ ዋይት ሃውስ ከተመለሱ ወዲህ አሜሪካና ኢራን በኦማን አደራዳሪነት አምስት ዙር ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡ ውይይቶቹ እስካሁን ድረስ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ውጤት ባያስገኙም፣ ሁለቱ አካላት ለኢራን ጉዳይ ሰላማዊ አማራጭን በተግባር ያሳዩባቸው ርምጃዎች እንደሆኑ ተቆጥረው ተወድሰዋል፡፡ የአሜሪካ ዩራኒየም የማበልጸግ ሂደቱን የማቋረጥ ጥያቄና የኢራን ያለማቋረጥ አቋም የሁለቱ አካላት የክርክር ነጥብ ሆኖ ዘልቋል፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትራቸውን ክሪስቲ ኖምን ወደ ቴል አቪቭ ልከው በኢራን የኑክሌር ድርድር ጉዳይ ሀገራቸውና እስራኤል የጋራ አቋም እንዲይዙ እንደሚፈልጉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ መግለጻቸው ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በውሳኔዎቻቸው እስራኤልን እያገለሉ እንደሆነ ለቀረበባቸው ወቀሳ ማስተንፈሻ ሊሆን እንደሚችል እየተገለጸ ነው፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የወሰዷቸው ርምጃዎች የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ሁነኛ አጋር የሆነችውን እስራኤልን ያገለሉ እንደሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ከየመን ሁቲ ታጣቂዎች ጋር የደረሱት የተኩስ ማቆም ስምምነት፣ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝታቸው እስራኤልን አለማካተቱ እንዲሁም በሶሪያ ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦችን ለማንሳት እና ከሀገሪቱ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር መወሰናቸው የቴል አቪቭ ባለሥልጣናትን አስደንግጧል፡፡
እስራኤል ከሁቲዎች ጋር የምታደርገውን ጦርነት አፋፍማ በቀጠለችበት ሁኔታ፣ ዋና አጋሯ አሜሪካ ግን ከሁቲዎች ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት መፈራረሟ በብዙ ወገኖች ዘንድ ጥያቄዎችን ያስነሳ ጉዳይ ሆኖ ነበር፡፡ ሁቲዎች በአሜሪካ መርከቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት በማርገብ ከአሜሪካ ጋር እንዲስማሙ የመከረቻቸው ደግሞ እስራኤል ዋና ጠላቴ የምትላት ኢራን መሆኗ ሲሰማ አሜሪካ አጋርነቷ ለእስራኤል ወይንስ ለኢራን?” እስከማለት የደረሱት ጥቂቶች አልነበሩም፡፡
ይባስ ብሎም በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሁካቢ፣ “አሜሪካ ከሁቲዎች ጋር ለመደራደር የእስራኤልን ፈቃድ መጠየቅ አይገባትም፡፡ አሜሪካ ሁቲዎች በእስራኤል ላይ ለሚሰነዝሩት ጥቃት ምላሽ የምትሰጠው እስራኤል ውስጥ የሚኖሩ አሜሪካውያን ዜጎች ከተጎዱ ብቻ ነው” ማለታቸው አሜሪካ በቀጣናው እስራኤልን በቀጥታ በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ የምትወስነው አይሁዳዊቷን አጋሯን አማክራ ነው የሚል እምነት ላላቸው ሰዎች የሚዋጥ አልነበረም፡፡
ትራምፕ እስራኤልን ባላካተተው የመካከለኛው ምሥራቅ ጉብኝታቸው ይፋ ካደረጓቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ሀገራቸው ቀደም ሲል በሶሪያ ላይ ጥላቸው የነበሩ ማዕቀቦችን እንደምታነሳ ማሳወቃቸው ነው፡፡ እስራኤል ያለማንም ከልካይ ቦምብ የምታዘንብባትንና “አሸባሪ” ብላ በፈረጀችው ቡድን የምትመራውን ሶሪያን የሚጠቅም ውሳኔ ይፋ ማድረጋቸው በዋሺንግተንና በቴል አቪቭ መካከል ስንጥቅ ተፈጥሯል የሚሉ ወገኖች ሁኔታውን በማስረጃነት አቅርበውታል።
ታዲያ ከእነዚህ ሁሉ ጥርጣሬዎችና የሴራ ትንተናዎች በኋላ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሀገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትራቸውን ክሪስቲ ኖምን ወደ ቴል አቪቭ ልከው በኢራን የኑክሌር ድርድር ጉዳይ ሀገራቸውና እስራኤል የጋራ አቋም እንዲይዙ እንደሚፈልጉ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ መግለጻቸው፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በውሳኔዎቻቸው እስራኤል እያገለሉ እንደሆነ የቀረበባቸውን ወቀሳ የሚያቀዘቅዝና የአሜሪካ እስራኤል ወዳጅነት በቀላሉ ነፋስ የሚገባበት እንዳልሆነ ማሳያ ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው፡፡
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም