
አዲስአበባ፡– መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን ጥያቄዎች በአንድ ጊዜ ሳይሆን በሂደት ለመመለስ እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማ አቀፍ የጤና ባለሙያዎች የማጠቃለያ ውይይት መድረክ ትናንት ሲካሄድ እንደገለጹት፤ የጤና ባለሙያዎች ሙያ እጅግ የተከበረና የትኛውም ክፍያ የሚመጥነው አይደለም፤ ባለሙያዎቹም በቂ ደመወዝ እንደሌላቸው እንረዳለን። ችግሩንም በዘላቂነት ለመፍታት ጤና ሚኒስቴር ጥናት እያጠና ነው ብለዋል፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙ ባለሙያዎች የጤና ባለሙያ ዋናው ክፍያ እርካታ መሆኑን ገልጸው፤ የጤና ባለሙያዎች ደመወዝ ለመኖር በቂ የሆነ ክፍያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ ከደመወዝ ጋር ተያይዞም አንድ የጤና ባለሙያ የተወሰነ ደረጃ ካደገ በኋላ በዘርፉ ውስጥ እየቆየ ቢሄድም ተጨማሪ ክፍያ አያገኝም ብለዋል፡፡
ሰብስፔሻሊስት ለመሆን አምስት ዓመታትን ብንማርም ቀድሞ ሲከፈለን ከነበረው ክፍያ የአንድ ሺህ 500 ብር ጭማሪ ብቻ ነው የሚደረግልን፡፡ ከነማ የሚሠሩ ፋርማሲስቶችም በየጊዜው ከደመወዝ ጋር ተያይዞ ይለቃሉ፡ ከትርፍ ሰዓት (ከዲውቲ) ክፍያ ጋር ተያይዞ በበዓላት እና በአዘቦት ቀን የሚሰላው የክፍያ ስሌት ተመሳሳይ ነው፡፡ ይህ ሊሻሻል ይገባል ሲሉም የጤና ባለሙያዎቹ ጠይቀዋል፡፡
የትራንስፖርት እና የቤት አቅርቦት ለጤና ባለሙያዎቹ በልዩነት ሊሰጥ እንደሚገባም የውይይቱ ተሳታፊዎች አንስተዋል፡፡ የሕክምና ባለሙያዎች ለተለያዩ ተላላፊ በሽታዎች ተጋላጭ ናቸው፤ ነገር ግን መታከም የሚችሉት በሚሠሩበት ተቋም ብቻ ነው። ወደ ሌላ ቦታ ሪፈር ሲደረጉ በክፍያ ነው የሚታከሙት፤ ይኼ ሊስተካከል ይገባል፡፡ የሕይወት ኢንሹራንስም ልናገኝ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
አንዳንድ የጤና ተቋሞችም የመድኃኒት፣ የላብራቶሪ እና የቢሮ መገልገያ እቃዎች እጥረት እንዳሉባቸውም ተነስቷል፡፡ በፊልሞች እና በኪነጥበብ ሥራዎች የሚሰጠን ውክልና የሙያ ክብራችንን የሚነካ እና እኛንም የማይወክል ነው ሲሉም የጤና ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ከንቲባዋ በበኩላቸው፤ የተሳታፊዎችን ጥያቄዎች አዳምጠው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ሊፈቱ የሚችሉ የትራንስፖርት ጥያቄዎች ውሳኔ እንደተሰጠባቸው እና የጤና ባለሙያው የፐብሊክ ሰርቪስ አገልግሎት በማንኛውም ሰዓት እንዲያገኝ መወሰኑን አሳውቀዋል፡፡
የመኖሪያ ቤት ጥያቄን ለመፍታት የከተማ አስተዳደሩ ከንግድ ባንክ ጋር በትብብር ለመሥራት መፈራረሙን ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ የጤና ባለሙያዎቹ እንዲደራጁ እና ከሚያገኙት ገቢ ላይ ቁጠባ እንዲጀምሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከንቲባዋ እንደተናገሩት፤ በከተማዋ ከ200ሺህ በላይ የመንግሥት ሠራተኛ አለ፡፡ ሁሉም የቤት፣ የደመወዝ እና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች ጥያቄን ያነሳል። ሁሉንም በአንድ ጊዜ መፍታት ብንችል ደስተኞች ነን፡፡ ነገር ግን ጥያቄዎቹ ለዘመናት የተጠራቀሙ እና ምንም መፍትሔ ሳይሰጣቸው የቆዩ በመሆናቸው ለመፍታት በአጭር፣ በመካከለኛ እና በረጅም ጊዜ እቅድ መሥራት የሚያስፈልግ በመሆኑ መንግሥት ያንን እያደረገ ነው፡፡
የደመወዝ ጥያቄውንም ለመፍታት ጤና ሚኒስቴር ጥናት እያጠና መሆኑን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ለሠራተኛው ደመወዝ መጨመር ብቻ ሳይሆን፤ የኢኮኖሚ አሻጥር በማድረግ ዋጋ የሚጨምሩ ነጋዴዎችን መቆጣጠር እና የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም የባለሙያዎቹን ጥያቄ በመረዳት ከእዚህ ቀደም ለአንዳንድ ስፔሻሊስቶች ቤት እንደተሰጠ፤ በሁሉም ተቋማት ላይ የካፍቴሪያ እና የሸማቾች ማዕከልን በማቋቋም እየሠራ እንዳለም አስታውሰዋል፡፡ ዘርፉንም ለማሻሻል ጤና ጣቢያዎች ግንባታ፣ የሆስፒታል ማስፋፊያዎች እየተከናወኑ መሆኑና በአጠቃላይ ከተማዋን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሠራ ስላለው ሥራ አብራርተዋል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም