
አዲስ አበባ፡- ምዕመናን የሃይማኖት አስተምሮን በመከተል ለሀገር ሰላም በጋራ ሊቆሙ እንደሚገባ በመዲናዋ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶች አመለከቱ ። ለሰላም ግንባታ የሃይማኖት ተቋማት እና መንግሥት በጋራ መሥራታቸው አስፈላጊ መሆኑ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ የመንግሥትና ሃይማኖት ተቋማት ግንኙነትና ትብብር በሚል መሪ ቃል ከሃይማኖት አባቶች ጋር ትናንት ውይይት አካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የመጡት የደብረ ቀራኒዮ መድኃኒዓለም እና የቅዱስ ገብርኤል አገልጋይ እና የደብሩ ምክትል ጸሐፊ ሊቀስዩማን ቀሲስ ካሳሁን ገመቹ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ የመንግሥት ተቋማት እና የሃይማኖት ተቋማት ተልዕኳቸው የተለያየ ቢሆንም የሀገር ሰላም ያገናኛቸዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች በእምነት መጻሕፍቶቻቸው የተጻፈውን ማስተማር እና ሕዝቡን ወደ ሰላም መምራት ቀዳሚ ሥራቸው መሆኑን በማንሳት፤ የሃይማኖት ተቋማት ይህን ኃላፊነታቸውን መወጣት ከቻሉ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችን ማስቆም ይቻላል ብለዋል ።
ሰላምን ከማጽናት አንጻር በየሃይማኖቱ ያሉ የበላይ አመራሮች ከስር ያለውን መዋቅር ለሰላም ማዘጋጀት ይጠበቅባቸዋል ያሉት ቀሲስ ካሳሁን፤ ልዩነቶች ተፈጥሯዊ ናቸው፤ የግጭት መንስኤ ሊሆኑ እንደማይገባ ገልጸዋል።
ሁሉም ሃይማኖቶች የተለያየ አስተምሮት አላቸው ነገር ግን የሀገር ሰላም ማስጠበቅ የጋራ ጉዳያቸው ነው። ለእዚህም ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ሰላምን በተግባር ሊሰብኩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ልዩነቶችን ተጠቅመው በሚዲያዎች አማካኝነት ግጭት ለመቀስቀስ የሚንቀሳቀሱ አካላትን እንደ መንግሥት እና እንደ ሃይማኖት መምከር ተገቢ ነው።
ነገሮች የሚስተካከሉ ካልሆነ እንደ መንግሥት የሕግ ማስከበር ሥራ መሥራት ተገቢ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ቀሲስ ካሳሁን እንደተናገሩት፤ ምዕመናንም የሀገር ሰላምን በማስጠበቅ ረገድ መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን እና የሃይማኖት አባቶች የሚያስተምሩትን ትምህርት መከተል፤ ለሰላምም ዋና ተጠሪ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ከልደታ ክፍለ ከተማ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ወክለው የተገኙት አቶ አብዱል ሰይድ መሀመድ በበኩላቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት እና መንግሥት በጋራ ተመካክረው መሥራታቸው የሀገርን ሰላም ለማጽናት ሚናው የጎላ መሆኑን አመልክተዋል።
መግባባት የሚመጣው መሪዎች ከሃይማኖት ተቋማት እና ከዜጎች ጋር ተመካክረው ሲሠሩ በመሆኑ ውይይቱ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አስታውቀዋል ።
የሃይማኖት ተቋማት ትልቁ ሥራቸው መሆን ያለበት ግጭቶች እንዳይከሰቱ ማድረግ፤ ከተከሰቱም የማርገበ ሥራ መሥራት ነው ያሉት አቶ አብዱል፤ በየትኛውም መልኩ የግጭት ተሳታፊ መሆን እንደሌለባቸው አመልክተዋል፤ የሃይማኖት አባቶች ስለሰላም ብቻ በመስበክ ኢትዮጵያ ሰላም ሆና እንድትቀጥል ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል።
ምዕመናን ሰላምን ከማስጠበቅ አንጻር የሃይማኖት አባቶችን ትምህርት መከተል እና ቴክኖሎጂዎችን ለጥሩ ተግባር ሊጠቀሙ ይገባል ያሉት አቶ አብዱል፤ የእስልምና ሃይማኖት ሰዎችን መንከባከብ እና ማክበር ያስተምራል። ይህን ደግሞ የሃይማኖት አባቶች ለተከታዮቻቸው በደንብ ሊያስተምሩ ይገባል ብለዋል ።
የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን የመካነ ኢየሱስ ተወካይ ቄስ ከበደ አበባው በበኩላቸው፤ ሀገር የጋራ እንደመሆኗ የሃይማኖት ተቋማት እና መንግሥት ለሰላም ግንባታ በጋራ መሥራታቸው አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በራሳችን ሊደረግ የማንወደውን ነገር ሌሎች ላይ ማድረግ እንደማይገባ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል ያሉት ቄስ ከበደ፤ሃይማኖት የሰላም መሠረት እንደመሆኗ ፤ ሰላምን ልትሰብክ እና ልትጸልይ ይገባል። ሰላም ከሌለ ተሰብስቦ እንኳን ለመጸለይ አይቻልም ብለዋል።
የእምነት አባቶች ምዕመናን ለሰላም እንዲቆሙ ተግተው ማስተማር አለባቸው። ምዕመናንም በበኩላቸው እንደየ ሃይማኖታቸው አስተምህሮ በጋራ ለሀገር ሰላም ሊቆሙ እንደሚገባም አስታውቀዋል ።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም