
አዲስ አበባ፡– ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ የሳይበር ጥቃትን በብቃት መከላከል እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ የመረጃ መረብ ደህንነት አስተዳደር አስታወቀ፡፡ ላለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት 500 የሚሆኑ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸዉን ታዳጊዎች ማሰልጠኑን ገለጸ።
የአስተዳደሩ የሳይበር ልህቀት ማእከል ዳይሬክተር ቢሻዉ በየነ ፤የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ ፕሮግራምን አስመልክቶ ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳመለከቱት ፤ በአለም ደረጃ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን የሳይበር ደህንነት ባለሙያዎች እጥረት አለ፡፡
ይሄንንም የሰው ሀይል እጥረት ለመቅረፍ መደበኛውን የትምህርት ስርአት ተከትለው ከሚሄዱ ባለሙያዎች ጋር ተሰጥኦ ያላቸውን ወጣቶች ማብቃት እንደሚያፈልግ አመልክተዋል ፡፡
ተቋሙ ላለፉት ሦስት ተከታታይ አመታት 500 የሚሆኑ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸዉን ታዳጊዎች ማሰልጠኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በዘንድሮዉ አመትም አራተኛዉ ዙር ስልጠና ለመስጠትም ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ምዝገባዉ እስከ ግንቦት 24 ይቆያልም ብለዋል።
ከዚህ ቀደም በሰመር ካምፕ ስልጠናው ተሳታፊ ከሆኑ ወጣቶች መካከል 70 የሚሆኑት በተቋሙ ውስጥ እየሰሩ የሚገኙ መሆናቸውን አመልክተው ፤ በርካቶችም በግላቸው ስራ መጀመራቸውን እና በግል መስሪያ ቤቶችም የተቀጠሩ እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ስልጠናው በከፍተኛ ዲሲፕሊን የሚመራ መሆኑን የገለጹት ዳይሬክተሩ ፤ የስልጠናው መርሃግብር ከንጋቱ 11 ሰአት ጀምሮ እስከ ለሊት 6 ሰአት ድረስ በሰአታት የተከፋፈለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በስልጠናው ተሳታፊ የሚሆኑ ወጣቶች ስልጠናዉን ወስደው ሲጨርሱ እንደ ሀገር ብሎም እንደ አለም ያለዉን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ እና የሀገሪቷን የሳይበር ሉአላዊነት ለማስከበር ጉልህ ሚና እንደሚኖራቸው አብራርተዋል።
ስልጠናዉ ከ11 አመት ታዳጊዎች እስከ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚያካትት እ ንደሆነ ጠቁመው ፤ የአምስት ሚሊዮን ኮደር ስልጠና ለወሰዱ ቅድሚያ ይሰጣል ብለዋል።ስልጠናውን በቀጣይ በክልሎች ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል ፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 20 ቀን 2017 ዓ.ም