
የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ጸጋዋ ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። በበረከት የተጎበኘችበት እድሏ ከብዙ ችግሮች ታድጓት ዛሬን እንድታይ አድርጓታል። እንደሌሎች ሀገራት በአውሎ ንፋስ፣ በሙቀትና በድንገተኛ ጎርፍ እንዳትጥለቀለቅና ዜጎቿን እንዳታጣም መከታ ሆኗታል። የተፈጥሮ ጸጋዋ ንጹህ አየር እንድትተነፍስ፣ ክረምት ከበጋ እምርታ የተሻለውን ከምድሪቱ እንድታፍስም እድል ሰጥቷታል። በአንዳንድ አካባቢዎች ድንገተኛ አደጋዎች ቢከሰቱ እንኳ ዜጎቿ መሸሸጊያ እንዳያጡ የሚያደርጋቸውን እድልም አጎናጽፏታል።
ሆኖም ይህ የተፈጥሮ ሀብት አለን ብሎ መቀመጥ ግን ተገቢነት የለውም። ምክንያቱም የተፈጥሮ ሀብትም ቢሆን አላቂ ነው። በጊዜ ሂደት ማለቁ፣ መበከሉና መለወጡ አይቀርም። ስለሆነም መተካትንና እንክብካቤን ይፈልጋል። እናም የተፈጥሮ ጸጋችን ዛሬን በብርሃን እንዲያመላልሰን፣ ነገን ደግሞ ድልድይ ሆኖ እንዲያሻግረን ከፈለግን ልንጠብቀውና ልንከባከበው ግድ ይለናል።
ተፈጥሮን ከምንከባከብበት መንገዶች አንዱ ደግሞ ችግኞችን መትከል ነው። ለዚህ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዓለምን ያስደነቁበት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብርን በማሳያነት መጥቀስ ይቻላል። ይህ መርሃግብር ሀገርን በመገንባት ሂደት ውስጥ በርካታ ለውጦችን ያመጣ ነው። ራስን ከመቻል ጀምሮ አንድነትን ከማጠናከር አኳያ ሚናው ተዘርዝሮ አያልቅም። የማኅበረሰብ ልዕልናን ያረጋገጠ፣ የሀገርን ኃያልነት በዓለም ላይ ያሳየ ዳግማዊ ዓድዋ ብንለው አያንሰውም።
ብዙ የተናቅንባቸው ተግባራት በዓድዋ ድል ድባቅ ተመትተዋል። ድሉ ኃያላኑ አቅማችንን እንዲረዱት አድርጓል። ‹‹ትንሽ ሀገር ናቸው፤ ይህንን ማድረግ አይችሉም›› ሲሉን ቢቆዩም በሕብረታችን የጥቁርና የነጭ አጥርን ገርስሰን ኃያል ሀገር እንደሆንን አረጋግጠናል። በቅኝ ግዛት ስር ያሉ ሀገራትን ጭምር ነጻ የመውጣትን ትግልና ውጤቱን አሳይተናል። ዛሬ ብዙ የአፍሪካ ሀገራት ከእኛ ተምረው ራሳቸውን የቻሉ እንዲሆኑ እድል አግኝተዋል።
በሀገር ደረጃ ስናየው በአረንጓዴ ዐሻራው ሥራም ይኸው ድል ነው የተደገመው። ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ስለ ሀገሩ መጻኢ ተስፋ እንዲነጋገር ሆኖበታል። ሕብረቱን አጠናክሮ ከልመና የሚወጣበትን መስመር ቀይሶበታል። በዓለም ደረጃ ያለውን ምልከታ ከመቀየር አንጻር ስናየው ደግሞ ብዙ ዘርዘር ያሉ ጉዳዮችን ማንሳት እንችላለን። አንዱና ዋነኛው ስምና ገጽታዋን ቀይረው በዓለም መድረክ ላይ ጭምር በድርቅ፣ በእርስ በርስ ጦርነት፣ በረሃብ … ወዘተ የሚያነሷት ሰዎችን ከማሳፈር አንጻር የሚነሳው ነው።
መርሃ ግብሩ በ2011 ዓ.ም በመደመር እሳቤ ይፋ ሲደረግ ዓለምን በሚያስደምም መልኩ ለመሥራት ታስቦ ነው። ሕዝቡም ሁሌ ድል ማድረግን ያነገበ ነውና ሕልሙን እውን አድርጎ በዓለም ደረጃ የሚያሳውቀውን ተግባር ከውኗል። የዓለም ክብረወሰንን የሰበረ ሥራ በመሥራትም አረንጓዴ አሻራን ዳግማዊ ዓድዋ ማድረግ ተችሏል። ይህ ዓለምን ያስደመመ ተግባር ‹እንችላለን›ን ያሳየንበት ሆኗል።
የአረንጓዴ ዐሻራው ሥራ ሌሎች ሀገራትን ጭምር ማስተማር የተቻለበት ሆኖም የቀጠለ ነው። በተለይም እንደእኛ በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት ብዙ ትምህርት ሰጥተን ያለፍንበት ነው። እነርሱን በማነቃቃት ወደ ሥራው እንዲገቡ ልምድ አካፍለናል። ነጋቸውን እያሰቡ እንዲሰሩም የይቻላል መንፈስን አጋርተናቸዋል። ግን ‹‹እንዴት ይብራራል? ለውጦቹ እንዴት ተለኩና ታዩ?›› የሚሉ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርምና ከኢትዮጵያ ደን ልማት የተገኙ መረጃዎችን አብነት አድርገን ጥቂት እናንሳ።
ሥራውን በ2011 ዓ.ም ስንጀምረው እሳቤው መደመርን ያነገበ ነው። በሕብረት ውስጥ መተሳሰር፣ አብሮ መለወጥ፣ ነገን አሻግሮ ማየትና የእርስ በርስ ትስስርን ማስፋት እንዳለ አምኖ የመጀመሪያ ሥራን አቅዶ ወደ መሬት ማውረድ ነው። ኢትዮጵያ በአራት ዓመታት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኞችን ለመትከል ማቀዷ የሚታወስ ነው። ከታቀደው ግብ አልፋ በመላ ሀገሪቱ 25 ቢልዮን ችግኞች በመትከል የአራት ዓመታት ዕቅዷን አሳክታለች። ይህ ሥራዋም በታሪክ መዝገብ ላይ እንድትሰፍር አድርጓታል።
በ2016 ዓ.ም ስድስት ቢሊዮን ችግኞችን መትከል ችለናል። በዘንድሮው፣ በ7ኛው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ደግሞ ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ለመትከል በሀገር አቀፍ ደረጃ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተሠሩ ይገኛሉ።
በአጠቃላይ እስካሁን ድረስ ከ40 ቢሊዮን በላይ ችግኞች ተተክለዋል። እንደ ሀገር የተተከሉ ችግኞች መጠነ ፅድቀታቸው ደግሞ ከ85 በመቶ በላይ ነው። ሆኖም እንደ ሀገር የተነሳንበት ዓላማ ችግኝ መትከል ብቻ አይደለም። ከዚያም ያለፈ ግብን ያነገበ ነው። ይህም ችግኞች ጸድቀው ሀገር ለምትፈልጋቸው ዓላማ እንዲውሉ ማድረግ፣ ዜጎችን ከችግሮቻቸው ማላቀቅ ነው። ከሀገር አልፎም ዓለምን ከአየር ንብረት ለውጥ ችግር ማውጣት ነው። በድርቅ የሚጎዱ፣ በአውሎ ንፋስ የሚናወጡ፣ በሙቀት ኃይል ጤናቸውን የሚያጡ ሰዎች እንዳይኖሩ ማገዝም ነው። ይህ ደግሞ በብዙ መልኩ እንደተሳካልን የሚያሳዩ ነገሮች አሉ።
ችግኞቹ በእኛ ሀገር ብቻ ቢተከሉም የአየር ብክለት ጉዳይ የእኛ ብቻ አይደለም። ዓለምን ሙሉ የሚመለከት ነው። እናም በእኛ ሥራ ዓለም ይድናል ማለት ነው። ግን ይህ የሚሆነው የተተከለው ምን ያህል እንክብካቤ አግኝቶ ጸድቆ ነው የሚለው ምላሽ ማግኘት አለበት። ከዚህ አንጻርም የኢትዮጵያ ደን ልማት በተለያዩ ጊዜያት ባወጣቸው መረጃዎች እንዳስቀመጠው፤ የችግኞች የጽድቀት መጠን ከዓመት ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ እየተሻሻለ መጥቷል።
መረጃው እንደሚሳየው ሥራው ሲጀምር አካባቢ የነበረው የችግኞች መጠነ ፅድቀት 79 በመቶ ብቻ ነበር። ሆኖም የችግኝ እንክብካቤ ሥራው በተቀናጀ መልኩ ተጠናክሮ መቀጠል ሲጀምር የችግኝ መጠነ ፅድቀቱ ከ80 በመቶ በላይ ከፍ ማለት ችሏል። ስለዚህም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የተተከሉ ችግኞች መጠነ ፅድቀታቸው ዝቅተኛው 79 በመቶ፣ ከፍተኛው ደግሞ 88 በመቶ እንደሆነም መረዳት ተችሏል። ከዚህ አንጻር ባለፉት ስድስት ተከታታይ ዓመታት በተከናወነው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ውስጥ ከተተከሉ ችግኞች ውስጥ በአማካኝ 81 በመቶዎቹ መፅደቅ ችለዋል።
ባለፈው ዓመት በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ሰባት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፤ በተሠራው የተቀናጀ የችግኝ የእንክብካቤ ሥራ በመጀመሪያው መጠነ ፅድቀት ልኬት ስድስት ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች ፀድቀዋል። በሁሉም ክልሎች በተሠራው የአንደኛ ዙር የችግኝ መጠነ ፅድቀት ልኬትም በአማካኝ 88 ነጥብ 6 በመቶ ፅድቀት ተመዝግቧል።
በ13 ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር በላይ የደን ሀብት ማጣቷን ከዚሁ መሥሪያቤት የወጣው መረጃ የሚያስረዳ ሲሆን፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እየተከናወነ ባለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ግን ይህ ነገር በብዙ መልኩ ተሻሽሏል። ለአብነትም እንደ ሀገር ይከሰት የነበረውን የደን ጭፍጨፋ ማሕበረሰቡ በአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ በስፋት በመሳተፉና በአቅራቢያው ለማገዶም ሆነ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውለውን ግብዓት በቅርቡ በማግኘቱ ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺህ ሄክታር ዝቅ ማለት ችሏል።
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ ውስጥ ሌላው ትኩረት አድርጋ የሰራችበት ጉዳይ የሚተከሉ ችግኞች ምን ምን አይነት መሬቶች ላይ ይረፉ፣ ምን አይነት ችግኝ የትኛው ላይ ቢተከል አዋጭነት አለው የሚለው ጉዳይ ነው። እናም በተራራማ፣ ሸለቋማ፣ ሞቃትና ቀዝቃዛ አካባቢዎች እንደየባህሪያቸው መቋቋም በሚችሉት ችግኝ እንዲሸፈኑ ተደርገዋል። በዚህም አሁን ላይ በኢትዮጵያ ካላት መሬት ውስጥ 26 ነጥብ 7 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በደን ተሸፍኗል። ለ2017 የአረንጓዴ ዐሻራ ልማትም 441 ሺህ ሄክታር መሬት የተከላ ቦታ ተለይቷል።
ይህ ልየታ ለምን ይጠቅማል ከተባለ ደግሞ እንደሚታወቀው ደን በሰው ልጆች ሕይወት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያለው ነው። ከሰው ጤና አልፎም የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው። ምክንያቱም ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ ምድርን ሚዛኗን ጠብቃ እንድትራመድ ያደርጋታል። በካይ ጋዝን አምቆ በመያዝ አካባቢን ይጠብቃል። የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል። ከዚህ አንጻር እንደ ሀገር ስናየው የተራቆተውን መሬታችንን ለመጠበቅ፣ የውሃ ሀብታችንን ለመታደግ፣ የደን ምርትና ምርታማነታችንን ለመጨመርና የፍራፍሬ ልማት ሥራዎቻችንን ለማስፋፋት እንዲሁም ለዜጎቻችን የሥራ እድልን ለመፍጠር ያግዘናል።
ከሁሉም በላይ ደግሞ እንደ ሀገር የምግብ ዋስትናችንን ለማረጋገጥ ሁነኛ መፍትሄ ይሆነናል። የተመጣጠነ ምግብ የሚባለውን እሳቤ እውን እንድናደርግም ያስችለናል። ጤናማ የሆነ አመጋገብንና ጤናማ አኗኗር እንዲኖረንም ይረዳናል። ከዚያም ባሻገር እንደ ዓለም ለሚጠበቅብን የአየር ንብረት ጥበቃ የራሳችንን ዐሻራ እንድናሳርፍም የሚረዳን ነው።
ለመሆኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ በሥራ እድል ፈጠራ እንደ ሀገር ምን ጠቀመን፣ ምን አይነት ለውጦችስ አሉት ከተባለ ደግሞ አሁንም የደን ልማት በተለያየ መልኩ ያወጣውን መረጃ አብነት አድርገን እናንሳ። የአረንጓዴ ዐሻራ ልማቱ በ2011 ዓ.ም ከተጀመረ ጀምሮ የዘንድሮን ሳይጨምር ባለፉት ስድስት ዓመታት (በችግኝ ማፍላት፣ ችግኝ አፍልቶ በመሸጥ፣ ዘር ሰብስቦ በመሸጥ፣ ችግኞችን በመንከባከብ፣ በለሙ ተፋሰሶች ላይ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በመሥራት ለአብነት ንብ በማነብ፣ በከብት ማድለብ … ወዘተ) አንድ ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል ተፈጥሮላቸዋል።
የአካባቢን መራቆት በመቀነስ የደን ሽፋን እንዲያድግ የሚያደርገው፣ የተስተካከለ አየርና የተሻለ የዝናብ ስርጭት እንዲኖር የሚያስችለው፣ ሀገር እየገነባች ላለው ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ሚናው የጎላ የሆነው፣ ድርቅን ለመከላከል ከማገዙም በላይ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችለውና ሀገር ከተረጂነት እንድትላቀቅ የሚያደርገው ይህ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃግብር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሉት መሆኑን ተገንዝበን ለነገ ኑሯችን ዛሬን እየሰራንበት እንሂድ። ዐሻራችን የነገ ተስፋችንና የልጆቻችን ሀብት በመሆኑም ዛሬን የሚያበራ፣ ነገን የሚያሻግር እናድርገው። ሰላም!
ክብረ መንግሥት
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም