
በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ አትሌቲክስና እግር ኳስ ከሌሎቹ የተሻለ እንቅስቃሴ አላቸው። አትሌቲክስ ከእግር ኳሱ በተለየ በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ ስኬታማ የሆነችበት ጭምር ነው። በአንፃሩ ኢትዮጵያ በእግር ኳሱ ኋላ የቀረች ሀገር ብትሆንም ስፖርቱ በሕዝብ ዘንድ ቁጥር አንድ ተወዳጅና ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግበት ነው። የስፖርት ቤተሰቡም በዓለም አቀፍ ደረጃ ይበልጥ ውጤት የሚጠብቀው በሁለቱ ስፖርቶች ነው ቢባል አልተጋነነም።
ውጤታማውን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ በተመለከተ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በውጤታማነቱ እንዳይዘልቅ በርካታ ፈተናዎች እንደተጋረጡበት እሙን ነው። እነዚህ ፈተናዎች ከውስጥ አሠራር ጀምሮ ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያላቸው ሲሆኑ አንድና ሁለት ብቻ አይደሉም። ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ባለፉት በርካታ ዓመታት ትልቅ ችግር ሆኖ የቆየውና አሁንም ድረስ መፍትሄ ያላገኘው የተተኪ አትሌቶች ጉዳይ ነው።
የተተኪ አትሌቶች ጉዳይ ሲነሳ ለዓመታት ፈተና ሆኖ የዘለቀው የአትሌቶች እድሜ ማጭበርበር የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ይህ የእድሜ ማጭበርበር ጉዳይ እንደ አፍሪካም ፈተና ነው። በኢትዮጵያ ግን አሳሳቢ መሆኑን በቅርቡ በድሬዳዋ በተካሄደው ከ18 እና 20 ዓመት በታች ቻምፒዮና ላይ ታይቷል።
ባለፉት በርካታ ዓመታትም በእድሜ ገደብ በሚካሄዱ መሰል ውድድሮች በተገቢው እድሜ የሚወዳደሩ ታዳጊና ወጣት አትሌቶች እድሜ ቀንሰው (“አጭበርብረው”) በሚወዳደሩ ታላላቆቻቸው እየተዋጡ እንደሀገር ተተኪ ለማጣታችን ትልቅ ምክንያት መሆናቸውን ብዙዎች ይስማማሉ። ይህ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብቻ ሳይሆን የዓለም አትሌቲክስም ከአበረታች ንጥረ ነገር ተጠቃሚነት (ዶፒንግ) ቀጥሎ በስፖርቱ የተደቀነ ትልቅ አደጋ ሆኖ የተቀመጠ ነው።
የእድሜ ጉዳይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገራት ያን ያህል አሳሳቢ ቢሆንም አንድ ሁነኛ መፍትሄ ግን አላጣም። ይህም በህፃናት አትሌቲክስ (kids atheletics) ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት ነው። የሀገራችንን ስፖርት በተለይም አትሌቲክስን ከፍ ለማድረግ፣ በጨቅላ እድሜ ያሉ ባለተሰጥኦ አትሌቶችን በትክክለኛው ሳይንሳዊ መንገድ ማሰልጠን ነው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያጋጠማትን የተተኪ አትሌቶች ችግር ለመፍታት እና ዘላቂ ስኬትን ለማረጋገጥ የተቀናጀና ሳይንሳዊ አቀራረብ ያስፈልጋል።
በአትሌቲክሱ በተለይም በመካከለኛ፣ ረጅም ርቀትና ማራቶን የኢትዮጵያ ተቀናቃኝ የሆነችው ኬንያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት በዚህ በህፃናት አትሌቲክስ ላይ መሥራት ከጀመሩ ቆይተዋል። ውጤቱንም እያዩ ይገኛሉ። ለዚህ አንዱ ማሳያ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች የተለያዩ አትሌቶችን ሲያሰልፉ መታየታቸው ነው።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በዚህ ረገድ ዘግይቶም ቢሆን በህፃናት አትሌቲክስ ላይ መሥራት ጀምሯል። ፌዴሬሽኑ ካለፈው አራት ዓመት ወዲህ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በትግራይ ክልል በሚገኙ አንደኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሚገኙ ህፃናት ላይ እየሠራ ይገኛል። በቅርቡ ወደ ሌሎች ክልሎችም የማስፋፋት ሃሳብ አለው። ቢዘገይም አልረፈደምና ሊበረታታና ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው ነው። የፌዴሬሽኑ ጥረት ብቻ ግን የሚፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አይችልምና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሊሠሩበት ይገባል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አንዱ ባለድርሻ አካል መሆኑ ይታወቃል። አካዳሚው ከተቋቋመበት ዓላማ አንዱ በተለያዩ ስፖርቶች ተተኪዎችን በብዛትና በጥራት ማፍራት ነው። በዚህ ረገድ በተለያዩ ስፖርቶች ባለፉት በርካታ ዓመታት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ መድረኮች የወከሉ አትሌቶችን ማፍራት ችሏል። ይሁን እንጂ ከአትሌቲክስ ስፖርት ጋር በተያያዘ ከሚነሳው የእድሜ ተገቢነት ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ነፃ ነው ማለት አይቻልም።
አካዳሚው ከተለያዩ አካባቢዎች ታዳጊና ወጣቶችን ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት በራሱ ባለሙያዎች መልምሎ እንደሚያሰለጥን ይታወቃል። የህፃናት አትሌቲክስ ላይ ግን አይሠራም። ይህ ደግሞ ከእድሜ አንፃር የተደራጀና ወጥ የመረጃ ሥርዓት በሌለበት ሀገር ሁሌም ትክክል እንደማይሆን ግልፅ ነው። ከእድሜ ባሻገር ሌላው በህፃናት አትሌቲክስ ላይ መሥራት ከታለንት/ ተሰጥኦን ከመለየት ጋር ያለው ጥቅም ነው።
አካዳሚው ወጣቶችን ለማሰልጠን የሚከተለው መንገድ በዋናነት ውድድር ተኮር ሲሆን በባለሙያዎችና ሳይንሳዊ መንገድም እንደሚከተል ነው በተለያዩ አጋጣሚዎች የሚጠቁመው። ይህ ትክክል ነው አይደለም የሚለው ሰፊ ጊዜ ስለሚጠይቅ ወደ ጎን ትተን ከወጣት ይልቅ ከህፃናት ጀምሮ መሥራት ያለው ፋይዳ ላይ እናተኩር።
በሌሎች ሀገራት የአንድን ሰው ተሰጥኦ/ታለንት ለይተው አትሌት ይሆናል አይሆንም ብለው ባለሙያዎች የሚወስኑት ገና በህፃናት እድሜ ላይ እያለ ነው። ይህም ተሰጥኦው በጊዜ ተለይቶ በየደረጃው አስፈላጊውን ስልጠና ከወሰደ በኋላ ወደ ወጣትነት እድሜ ሲሸጋገር ጀምሮ በትልቅ ደረጃ ተፎካካሪ እንዲሆን ያስችለዋል ተብሎ ይታመናል።
ብዙ ማለሙያዎችም በዚህ ይስማማሉ። እንደ ኢትዮጵያ አካዳሚውን ምሳሌ አድርገን ብንመለከት አትሌቱ ለስልጠና የሚመለመለው በታዳጊ ወይም ወጣት እድሜ ላይ እያለ ነው። ከዚያ በኋላ ገና ተሰጥኦው ተለይቶ አስፈላጊውን ስልጠና ወስዶ በትልቅ ደረጃ ተፎካካሪ እስኪሆን የሚፈጀውን ጊዜ መገመት ይቻላል። በዚህ ሁኔታ ከሌላው ዓለም ጋር እኩል መራመድ አይቻልም።
አካዳሚው በህፃናት ላይ ለመሥራት ብዙ እንቅፋቶች አሉበት። ለዚህ ቤተሰብ ልጆቹን ገና በለጋ እድሜያቸው ለአካዳሚው አሳልፎ ለመስጠት ፍቃደኛ ካለመሆን ጀምሮ ብዙ ፈተናዎች እንዳሉ ይታወቃል። ይህን ፈተና ግን መጋፈጥ ያስፈልጋል። ለዚህም መፍትሄ አይጠፋም።
አካዳሚው ባለፈው ሳምንት በሃዋሳ አስረኛውን የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባዔ ባደረገበት ወቅት ሰባት የተለያዩ ጥናቶች ቀርበው ጥልቅ ሙያዊ ውይይት ተደርጎባቸው ነበር። በጉባዔው ከተነሱ ሃሳቦች መካከል አንዱ አካዳሚው ለምን በህፃናት አትሌቲክስ ላይ አይሠራም? የሚል ነው። ይህ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የወደፊት እጣ ፋንታ ወሳኝ ሚና ያለው ጉዳይ በጉባዔው ላይ መነሳቱ በራሱ አንድ ጅምር ነው። በቀጣይ አካዳሚው በሚገባ አስቦበት ወደ ተግባር እንዲገባም የማንቂያ ደወል ነውና ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ሰኔ 14 ቀን 2017 ዓ.ም