
ከሰሞኑ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮችን የሚከለክል ሕግ ወጥቷል በሚል ብዙ አስተያየቶችን አያለሁ። አፈጻጸሙን ገና የምናየው ቢሆንም፤ የሕጉን መውጣት አስፈላጊነት ለረዥም ጊዜ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን የፕላስቲክን ጎጂነት ለማሳየት እየሠራን ለማስተማር ጥረት ስናደርግ ቆይተናልና በበጎ ዓይን ነው የማየው። ከሚሰጡት አስተያየቶች ውስጥ አሉታዊ የሆኑት የእዚህ አጭር አስተያየት መነሻ ሆነውኛል። በእርግጥ ለውጥ ሁልጊዜም አንዳች የሚጎራብጥ ነገር አያጣውምና አሉታዊ አስተያየቶችንና ስላቆችን በእዚያ ዓይን ማየት የሚገባ ይመስለኛል።
ሰፊ መሠረት ያለው ለውጥ፣ የባህሪና ተግባር መሻሻልን ግድ የሚል ለውጥ ቀላል የማይሆንበት ምክንያት የቆዩና መሠረታቸውን ያሰፉ ልምዶች በቀላሉ በአንድ ጀንበር ስለማይለወጡ፤ በእነዚህ ነባር የሆኑ ልምዶች ዙሪያ የተስፋፉ የኢኮኖሚ ፍላጎቶች መኖር፣ እና አኗኗራችንን ከሚያቀሉ ሁነቶች ጋር የሚያያዙ ብዙ ጉዳዮች በመኖራቸው ነው። ሰዎች ለውጥን ይሁን ብለው እንዳይቀበሉ ከሚያደርጓቸው ምክንያቶች ውስጥ የግንዛቤ እጥረት፣ ያሉበት ሁኔታ የተመቸ መምሰል፣ የአማራጮች ማነስ ወይም ግልፅ ሆነው አለመገኘት፣ ወይም በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው ላይ ኑሮን ማመቻቸት ሊሆኑ ይችላሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ሕጉ መውጣትና ተግባራዊ መሆን ከነበረበት ጊዜ የዘገየ ቢሆንም፤ ማንኛውም ለራሱ ጤና የሚያስብ፣ የልጆቹ ነገ የሚያሳስበው ሰው ይህንን ሕግ ሊደግፈው ይገባል። ለውጥ ሁልጊዜም ቢሆን አንዳች የማይመች ነገር እንዳለው የታወቀ ነውና እኒህን አሉታዊ አስተያየቶች በእዚያ አውድ ማየት እፈልጋለሁ።
ሕዝብ ጎጂነቱን ተገንዝቦና አምኖ ካልተቀበለው ሕግ ማውጣት ብቻውን የፕላስቲክ ብክለትን ሊገታው አይችልም። በመሆኑም ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ማስተማር፣ የሕጉን አፈጻጸም በጥብቅ መከታተል እንዲሁም አማራጮች በስፋት ተደራሽ የሚሆኑበትን መንገድ ማመቻቸት ያስፈልጋል።
ፕላስቲክን በሕግ ማገድ በአምራች ተቋማት ላይ ወዲያው የሚያስከትለው የኢኮኖሚ መታወክ ከጥቅሙ ጋር ሲነጻጸር፤ ጥቅሙ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚታይ ከመሆኑ አንፃር ፈጥኖ ሊታይ ስለማይችል ሳያቋርጡ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራትና በሚመለከታቸው አካላት መካከል መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል።
ፕላስቲክን በሕግ ለማገድ ስትነሳ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሀገር አይደለችም። እኤአ እስከ 2024 ባሉት ዓመታት ወደ 127 የሚሆኑ የዓለም ሀገሮችና ግዛቶች ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮችን፣ ማለትም እንደስስ ፌስታል ያሉትን የፕላስቲክ የዕቃ መያዣ ከረጢቶችን፣ የመጠጥ መምጠጫ የፕላስቲክ ቀሰሞችን (straws)፥ በፕላስቲክ የተሠሩ ሹካ፣ ማንኪያና ቢላዋ እና የምግብ መያዣ (ማስቀመጫ) ፕላስቲኮችን አግደዋል።
ከእነዚህ ሀገሮች ውስጥ በአፍሪካ ውስጥ ውጤታማ የሆነ ሥራ በመሥራታቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ኬንያ፣ ሩዋንዳና ደቡብ አፍሪካ ይገኙባቸዋል። ከሦስቱ ኬንያ እና ሩዋንዳ በሕጎቻቸው ጥብቅነት ይታወቃሉ።
ሩዋንዳ ባወጣችው የአካባቢ ጥበቃ ሕግ አማካኝነት ፕላስቲክ ማምረትን፣ ጥቅም ላይ ማዋልን፣ ከውጭ ማስገባትንና ሽያጭን የሚያግደውን ሕግ ያወጣቸው የዛሬ 17 ዓመት ነው። ዛሬ ዋና ከተማዋ ኪጋሊ ከአፍሪካ ከተሞች በንጽሕናዋ ቀዳሚ ስትሆን፤ የሀገሪቱ ነዋሪዎች ፕላስቲክን በተኩት የወረቀትና የጨርቅ አማራጮችን በመጠቀም ይታወቃሉ። አንድ ሩዋንዳዊ የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) ይዞ ከተገኘ ወደ $40 (50000 የሩዋንዳ ፍራንክ) ይቀጣል። የንግድ ድርጅቶች የሆኑ እንደሆነ መቀጫው ወደ $80 ከፍ ይልና መወረስ እንዲሁ የሥራ ቦታ መታሸግን ያስከትላል። በተደጋጋሚ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ እስር ወይም የማኅበራዊ አገልግሎት ግዴታ ይጣልባቸዋል።
ኬንያ ፌስታልን የሚከለክል ሕግ ካወጣች ስምንት ዓመት ይሆናታል። በእዚህም ሊታይ በሚችል ደረጃ በሀገሪቱ የፕላስቲክ ቆሻሻ መጠን ቀንሷል። ይህን ሕግ ተላልፈው የተገኙ እስከ $35000 ዶላር የሚደርስ የገንዘብ፣ወይም እስከ 4 ዓመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይጠብቃቸዋል። በዓለም ካሉ ሀገሮች ሁሉ ከባድ ቅጣት በመጣል የምትታወቀው ኬንያ ናት።
ደቡብ አፍሪካ ሌላኛዋ ውጤታማ ሥራ የሠራች ሀገር ናት። የመጀመሪያውን ሕግ የዛሬ 21 ዓመት አውጥታ ከ17 ዓመታት በኋላ አሻሽላዋለች። በእዚህም የፕላስቲክ ከረጢት (ፌስታል) ታክስ አውጥታ ተግባራዊ ስታደርግ የቆየች ሲሆን፤ በ2027 ደግሞ ሁሉም (100%) ፕላስቲክ ከረጢቶች ከፕላስቲክ እንደገና ተመልሰው የሚሰሩ (recycled) እንዲሆኑ አቅዳለች። በእዚህ ሕግ የታዩት ለውጦች ሕዝቡ ቀስ በቀስ የባህሪ ለውጥ እያመጣ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ፕላስቲክን መልሰው በመጠቀም ምርት የሚያመርቱትን እያበረታታ መጥቷል። ሀገሪቱ ያወጣችውን ይህንን የፕላስቲክ አጠቃቀምን የተመለከት ሕግ ተላልፈው የተገኙ አምራቾች እስክ $550000 ዶላር ወይም የ10 ዓመት እስር ይጠብቃቸዋል።
የፕላስቲክ ብክለትን ለመከላከል ሕግ ለምን ያስፈልጋል?
ይህንን ጥይቄ ከሳይንስ እና ሞራላዊ መሠረተ ሃሳቦች አንስቶ ማየት ይጠቅማል።
በሳይንስ ዓይን ካየነው
- ፕላስቲክ መርዛማ የሆኑ ንጥረ ነገሮችን (እንደ BPA, phthalates, and microplastics) ወደ አፈር፣ አየርና ውሃ በመልቀቅና በመበከል የሰውን ልጅ የሚኖርበትን አካባቢ ጤና አደጋ ላይ ይጥላል። ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ ፕላስቲክ ሕይወት ባላቸው ሕዋሶች ውስጥ በመጠራቀም የሰውነት አሠራርን ያውካሉ፤ መሐንነትን ያመጣሉ፤ እንዲሁም በሽታ የመቋቋም አቅማችንን ያዳክማሉ።
- ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የባሕርና የየብስ እንስሳት ፕላስቲክ በመብላት ወይም በፕላስቲክ በመተብተብ ሕይወታቸውን ያጣሉ። ከላይ እንደተገለጸው፤ ፕላስቲክ ወደ ደቃቅነት ይለወጥና በትንሽና ሕይወት ካለው የባሕር ፍጥረት ከመበላት ጀምሮ እስከ እኛ የሰው ልጆች የአመጋገብ ሰንሰለት ውስጥ ይገባል።
- የኅብረተሰብ ጤና ምርምር እንደሚያሳየው፤ የፕላስቲክ ብናኞች (ደቃቃዎች) በሰው ልጅ ደም፣ ሳንባ፣ እና ማህጸን ውስጥ ተገኝተዋል። ፕላስቲክን ለማስወገድ ወይም ለሌላ ጉዳይ የሚያቃጥሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ ሰዎች በጢሱ የተነሳ እንደ ዳዮክሲን ላሉ የካንሰር ሕመም አምጪዎች ተጋላጭ ሲሆኑ፤ የመተንፈሻ የሰውነት ክፍሎቻቸውንም አደጋ ላይ ይጥላቸዋል።
- ፕላስቲክን የማምረት ሂደቶችና የሚወገድባቸው መንገዶች ለዓለም የሙቀት መጠን መጨመር ምክንያት የሆኑ ትነቶችን ያመነጫል። በመሆኑም የፕላስቲክ ብክለትን ለመቀነስ የሚወጡ ሕጎች የአየር ንብረት መቃወስ እንዳይፈጠር የሚወሰዱ ርምጃዎች አካል ናቸው።
ሞራላዊ ወይም የፍልስፍና መሠረቶችን ስናይ ደግሞ፦
- የጥንቃቄ መርህ አንድ ድርጊት (ለምሳሌ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፕላስቲኮች ብክለትን የሚያመጡ የሆነ እንደሆነ) በኅብረተሰቡ ወይም በአካባቢው ላይ አደጋ ያስከትላል የሚል ጥርጣሬና እምነት ካለ፣ ሳይንሳዊ የሆነ ማስረጃ የግድ ማቅረብ ሳያስፈልግ የመከላከል ሥራ መሠራት ይኖርበታል።
- የሥነ ምህዳር ፍትሕ፣ ለፕላስቲክ ብክለት ይበልጥ ተጋላጭ የሆኑት በኑሯቸው ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉት ናቸው። ሕግ ሲወጣ ለሁሉም ሆኖ በተለይ ተጋላጭ የሆኑትን ከከፋ አደጋ ለመከላከልም ነው።
- ለትውልዶች የሚተርፍ ፍትሐዊነት፣ መጪዎች ትውልዶችም በጤናማና ንጹህ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው። ፕላስቲክን የተመለከቱ ሕግጋት የነገዋ ዓለም ለመኖር የተመቸች እንድትሆን አድርጎ የመተው ሞራላዊ ግዴታ እንዳለብን ያሳያሉ።
- የጋራ ሥነ ምግባር፣ አየር፣ ውሃ፣ እና መሬት የጋራ ሀብቶች ናቸው። ቁጥጥር ያልተደረገበት የፕላስቲክ አጠቃቀም የማህበረሰቡን መብቶች ይጥሳል፤ ስለዚህ ሕጎች እነዚህን የጋራ ሀብቶች ለመጠበቅ ይፈጸማሉ።
በመሠረቱ፣ የፕላስቲክ እገዳዎች በሳይንሳዊ ማስረጃ እና በሥነ ምግባራዊ አስተሳሰብ ላይ የተመሠረቱ ሲሆኑ፤ ጠንካራ ሳይንስን ከምድር ጠባቂዎች ኃላፊነታችን ጋር ያገናኛሉ።
ከላይ የተጠቀሰውን መሠረት አድርገን ስናየው እንግዲህ
- የቆሻሻን አወጋገድ ሥርዓት መዘርጋትና ማስተዳደር በጣም ውድና አድካሚ ሥራ ነው። ለአንድ ጊዜ ብቻ የምንጠቀምባቸው ፕላስቲኮች የውሃ መውረጃ ቦዮችን ይዘጋሉ፣ አካባቢንም በጣም ያቆሽሻሉ። የእኛ ሀገር የቆሻሻ ማስወገጃ አውታር በቆሻሻ ለመበላሸት የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ፤ የፕላስቲክ ቆሻሻ ለብዙ መቶ ዓመታት ካለመስበሱ ጋር ተያይዞ ይህንን ችግራችንን ያባብሰዋል። ለምሳሌ ክረምት በመጣ ቁጥር የቆሻሻ መውረጃ ቦዮችን ለማጽዳት እንኳ (ወንዞችንና ሐይቆችን ሳንጨምር) የምናፈስሰው የበዛ ወጪ በጣም ለሌላ አንገብጋቢ ጉዳይ ልናውለው የምንችለው በሆነ ነበር።
- የፕላስቲክ ብክለት ድህነት ይበልጥ ሥር እንዲሰድ ያደርጋል። በአብዛኛው በፕላስቲክ ተበክለው የምናያቸው በኑሮ ደረጃቸው ዝቅተኛ በሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች መኖሪያዎች አካባቢ ሆነው ነዋሪዎችን ለከፋ የጤና ችግር የሚያጋልጥ ነው። ለምሳሌ፦
- በተበላሹ የቆሻሻ ማስወገጃ መስመሮች የተነሳ ውሃ ይበከላል። ይህ ብክለት በምንጠጣው ውሃና በምንበላው ምግብ ውስጥ ሠርጎ ወደ ሰውነታችን ስለሚገባ ለብዙ በሽታዎች ያጋልጠናል። በቅርብ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ የፕላስቲክ ብናኞች በሰውነታችን ውስጥ በስፋት ከመገኘታቸው በተጨማሪ ለመሐንነት፣ ለልብ ሕመምና ለሰውነት ብግነት ምክንያት እንደሆኑ እየተገለጸ ነው። ቀደም ካሉትና ፕላስቲክ እንዲህ በስፋት ካልነበረባቸው ጊዜያት ጋር ሲነጻጸር በአሁኑ ጊዜ በወንዶች የዘር ፈሳሽ ውስጥ የፕላስቲክ ብናኞች በስፋት መገኘት የማስጸነስ አቅማቸው ላይ አስጊ የሆነ ማሽቆልቆል እያሳየ ነው።
- ቆሻሻ ሲቃጠል ፕላስቲክም አብሮ እየተቃጠለ አየሩ ይመረዛል፣ ነዋሪዎችም የፊት ተጋላጭ በመሆን ለበሽታ ይዳረጋሉ። እንደ ካንሰርና የመተንፈሻ አካላት ሕመም እንዲሁም የልጆች የዕድገት መስተጓጎል የመሳሰሉት ፕላስቲክ ሲቃጠል የተመረዘውን አየር ወደ ውስጥ ስንተነፍስ ከሚከሰቱ የጤና ችግሮች ውስጥ በዋነኛነት ተጠቃሽ ናቸው።
- ፕላስቲክ መውረጃቸውን በደፈናቸው አካባቢዎች አስፈላጊ ያልሆን የቆሻሻ ውሃ ክምችት ይፈጠርና የወባ ትንኝ መራቢያ ስለሚሆን በእዚህም በሽታ በቀላሉ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ነዋሪዎች በእንደዚህ ዓይነቱ ችግር ቀድመው ይጠቃሉ፤ የመከላከል አቅማቸውም ዝቅተኛ ነው።
- መከልከሉ አማራጭ የሥራ ፈጠራን ያበረታታል፣ የነበሩንንና እየከሰሙ የመጡትን የእቃ መያዣ፣ መጠቅለያ፣ የወረቀትና የእፅዋት ምርቶች፣ ወዘተ እንዲያንሠራሩ ያደርጋል፤ ለአካባቢ ስምም የሆኑ ሌሎች ሥራዎች እንዲፈጠሩም ያበረታታል። በእርግጥ ሕጉ ፕላስቲክ በማምረት ላይ ኑሮአቸውን የመሠረቱትን ሊያውካቸው እንደሚችል ይታመናል። ሆኖም ይህ መታወክ የበዛ ጉዳት እንዳያደርስና ወደ አማራጭ የምርት መስመር እንዲገባ ማገዝና ሁኔታዎችን ማመቻቸት ደግሞ ለውጡን ያፋጥነዋል።
- መከልከሉ በረዥም ጊዜ ውስጥ ሊፈጠር የሚችልን በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጠር የበረታ ጫና ይቀንሳል። አሁን ስናየው (እና ስለለመድነውም) ፕላስቲክ በቀላሉ የሚገኝና በአንጻራዊነት ርካሽ ቢሆንም፤ በረዥም ጊዜ ውስጥ አካባቢን ለማጽዳት የሚያስወጣን ወጪ፣ በጤና ላይ የሚፈጥረው ጉዳትና ቱሪዝምን በማስቀረት የሚፈጥረው ሳንካ ስናይ ጉዳቱ የከፋ ነው። ነቅተን ለአንድ ጊዜ ብቻ የምንጠቀምባቸውን ፕላስቲኮች በማስቀረት አሁን ልብ ያላልናቸው ተግዳሮቶች ጎልብተው ነገ የማንችለው የሀገር ዕዳ እንዳያመጡብን ያደርጋል።
- ግብርናንና የአኗኗራችንን ሁኔታ መጠበቅ።
- በፕላስቲክ የተሞሉ ማሳዎች የአፈር የጥራት ደረጃቸው የወረደ በመሆኑ እፅዋትና ተክሎች በጤናማ ሁኔታ እንዳያድጉ ይሆናሉ፤
- እንስሳት ፕላስቲክን በመመገብ ይራባሉ፣ የውስጥ አካላቸው ይጎዳል፣ ይታመማሉ፣ ይሞታሉ፤ እናም ምርታማነትም ይቀንሳል።
- መስኖ በሚጠቀሙ አካባቢዎች ውሃው በፕላስቲክ የተበከለ እንደሆነ በፕላስቲክ ውስጥ የሚገኙ መርዛማ ቅንጣቶች በውሃው አማካኝነት ወደ እፅዋትና አትክልቶች በመስረግ ወደ ምግብ ሥርዓቱ (ሰንሰለቱ) በመግባት የማንወጣው የጤና ችግር ውስጥ ይከቱናል።
- ለምርታማነት መሳለጥ ቁልፍ ሚና እንዳላቸው የሚነገርላቸውን ንቦችን በመጉዳት የቀሰማ ሥራቸውን (pollination) ያስተጓጉላል።
- እንደ ኢትዮጵያ ባለ በእርሻ ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ላይ ይህ በቀጥታ የምግብ ዋስትናንና የገበሬዎችን የነፍስ ወከፍ ገቢን ያቃውሳል። በተጨማሪም በፕላስቲክ የተበከለ መሬት እፅዋት ሥራቸውን በሚገባ እንዳይሰሩና በሚፈለገው መጠንም እንዳያድጉና ለፍሬ እንዳይበቁ ያግዳል፤ የእፅዋቱን ጤና ያቃውሳል።
- ሕጉ ሀገሪቱ ከምትከተለው አረንጓዴ መር የልማት መርሃ ግብር ጋር ስምም ነው። በእዚህ ረገድ ለአንድ ጊዜ ጥቅም ብቻ የሚውሉ ፕላስቲኮችን መከልከል ሀገሪቱ የጀመረችውን ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ የመገንባት ሥራና በእዚህም ረገድ በአፍሪካ መድረክ ያላትን የመሪነት ሚና የሚያጠናክር ርምጃ ነው።
ለማጠቃለል ክልከላው የቅንጦት ጉዳይ ሳይሆን ለሕልውናችንና ለሥነ ምህዳር ፍትሕ፣ ለኢኮኖሚ መረጋጋት እና ለኅብረተሰብ ጤና ወሳኝ ጉዳይ ነው። መጻኢው ጊዜ ንጹሕና ተስፋ የሚጣልበት ጊዜ እንዲመጣ መሠረት የሚጣልበት ጉዳይም ነው።
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
ተባባሪ የጥናት ፕሮፌሰር ፍሬው ከፍያለው
አዲስ ዘመን ዓርብ ሰኔ 13 ቀን 2017 ዓ.ም