ቢሮው በጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን መልሶ እያደራጀ መሆኑን ገለጸ

ሰመራ፦ በበጀት ዓመቱ 10 ወራት በክልሉ በተለይም በጦርነት ወቅት ጉዳት ደርሶባቸው የነበሩ የጤና ተቋማትን የማደስ፣ የሰው ኃይልና ግብዓትን የማሟላት ስራዎች መሰራታቸውን የአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ያሲን ሀቢብ አስታወቁ።

የጤና ቢሮ ኃላፊው ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ አሥር ወራት በጦርነት የተጎዱ የጤና ተቋማትን ከማደስና ግብዓቶችን ከማሟላትም በተጨማሪ ሌሎች የጤና አገልግሎቶችንም የማሻሻል ሥራዎች ተሠርተዋል። የእናቶችንና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ በተሠሩት ሥራዎች ፤ እናቶች ለወሊድ በሚመጡበት ወቅት የሚቆዩባቸው 24 ያህል ማቆያዎች መሠራታቸውን ገልጸዋል።

እንደ ቢሮ ኃላፊው ገለጻ፤ ቀደም ሲል አንድ አርብቶ አደር እናት እርጉዝ ሆና ወደ ጤና ተቋም ስትሄድ ጊዜዋ ገና ከሆነ ወደ መጣችበት እንደትመለስ ይደረግ ነበር፤ ምጥ ሲመጣባት ደግሞ እንደገና በሸክም ትወሰዳለች ፤ ካልሆነም እዚያው ትውልዳለች፤ ይህም በመሆኑ የሞት አደጋ ሊያጋጥማት ይችላል።

የተሠሩት 24 የእናቶች ማቆያዎች እንዲህ አይነቱን ችግር ለማስቀረት የሚረዱ መሆኑን ጠቁመው፤ መውለጃ ጊዜያቸው የተቃረበ ነፍሰ ጡሮች እስከሚወልዱ ድረስ በጤና ተቋማት እንዲቆዩ መደረጉ ትልቅ ለውጥ ነው ብለዋል።

በ2016 ዓ.ም የታደሱ 22 ጤና ጣቢያዎችም የሕክምና መሣሪያዎች ተሟልተውላቸው ወደ ስራ መግባታቸውን አቶ ያሲን አስታውሰዋል። በተመሳሳይ በ2017 በጀት ዓመት 10 ወራት በዞን ሁለት 22 ጤና ጣቢያዎች እድሳት ተደርጎላቸውና የሕክምና መሣሪያ ተሟልቶላቸው የሰው ሀብት በመዘጋጀት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል። በዚህ ሥራ ላይ የዓለም ባንክ እና በየደረጃው ያሉ የጤና ተቋማት እገዛ እያደረጉ ነው ብለዋል።

በክልሉ ሆስፒታሎችን በማጠናከር ረገድ ለመሀመድ አክሌ ሆስፒታል በቀን 200 ሲሊንደር የኦክሲጅን ፕላንት የሚያመርት እና 60 ሚሊዮን ብር ዋጋ የሚያወጣ ሲቲ ስካን ማስገባት እንደተቻለም ጠቅሰዋል። በጦርነት ወቅት ለወደመባቸውና ለሌላቸው ወረዳዎችና ጤና ተቋማት 26 አምቡላንሶች መሰራጨታቸውንም ተናግረዋል።

ቀደም ሲል አምቡላንሶቹን ለሌላ ዓላማ የማዋል ተግባር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን የክልሉ ፕሬዚዳንትን ጨምሮ ጥብቅ አቅጣጫ ተሰጥቶ አምቡላንሶች ለሌላ ሥራ እንዳይውሉ ተደርጓል ብለዋል።

በክልሉ በጤና ዘርፉ ሰፊ የሪፎርም ስራ መሰራቱን ተከትሎ ሞባይል የጤና ቡድንም በተመሳሳይ ሥራ እየሰራ እንደሚገኝ፤ ጤና ተቋማትን ዲጂታል ከማድረግ አኳያ የኮምፒውተሮች ስርጭት መደረጉንና ሥልጠናዎች መሰጠታቸውን ገልጸዋል። ሆስፒታሎች ከወረቀት ነፃ የሆኑ ሥራዎችን እንዲተገብሩ ከማድርግ አንጻር በዱብቲ ወረዳ ላይ አበረታች ውጤት መታየቱን አቶ ያሲን ተናግረዋል።

ከበጎ አድራጎት ሥራ ጋር ተያይዞ፤ ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት ቤት ሰርቶ ለመስጠት እንቅስቃሴ እየተደረገ እንደሚገኝ እና በየቦታው የስኳር፣ የደም ግፊት እንዲሁም የተለያዩ ምርመራዎች በነፃ መደረጋቸውን ጠቅሰው፤ በዚህም ከ20 ሺህ በላይ ሰዎች የነፃ የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት ማግኘታቸውን አቶ ያሲን አስረድተዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 18 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You