
ዜና ሐተታ
‹‹ማስታወቂያ አውጥተን የምናገኛቸው ተመራቂ ተማሪዎች የክህሎት ክፍተት ያለባቸው በመሆኑ የምንተማመንባቸውን ለመቅጠር በጣም እንቸገራለን። ይህ በመሆኑም የሥራ ልምድ ያላቸውን ለማፈላለግ ተገደናል›› በማለት አስተያየታቸውን የሰጡት የላየንስ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ተወካይ አቶ ውብሽት ዓለሙ ናቸው።
አቶ ውብሽት ሀሳባቸውን የሰጡት፤ ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የ2017 ዓ.ም ዕጩ ምሩቃን ከቀጣሪ መሥሪያ ቤቶች (አምራች ኢንዱስትሪዎች) ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን ዕድል ለማመቻቸት ሰሞኑን በዩኒቨርሲቲው በተካሄደው የሥራና ሙያ ዓውደ ርዕይ ላይ ነው። ተቋማቸው በተለይ በግብርናው ዘርፍ ለመሥራት ቁርጠኛ የሆነ ጀማሪ ባለሙያ ማግኘት እየተቸገረ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ ቀደም የግብርና ባለሙያዎችን እያሠለጠነ ያወጣ እንደነበረው ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ዓይነት የትምህርት ተቋም መፈጠር እንዳለበትም ገልፀዋል።
በአፍሪካ ጆብስ ኔት ወርክ የደረጃ ፕሮጀክት አስተባባሪ ወይዘሪት ጵንኤል ኃይሉ በበኩላቸው፤ ድርጅታቸው የቀጣሪ መሥሪያ ቤቶችን ማስታወቂያ በማውጣት ሥራ አመልካቾች በድረ ገጽ (ኦንላይን) ተጠቅመው ሥራ እንዲያመለክቱ፣ ድርጅታቸው ከስምንት ዓመት በፊት ዕድሉን ባመቻቸበት ወቅት ነበር ቀጣሪ ድርጅቶች አዲስ ተመራቂ ተማሪዎችን መቅጠር እንደማይፈልጉ መገንዘቡን ያስታወቁት። እርሳቸው እንዳሉት ሥራ ፈላጊዎቹ እራስን መግለጽ፣ ያላቸውን የትምህርት ውጤት አደራጅቶ (ሲቪ አዘጋጅቶ) ማቅረብ፣ በድረ ገጽ መረጃን መስጠትና ደብዳቤ መፃፍ ጥቂቶቹ የክህሎት ክፍተቶቻቸው ሆኖ ተገኝቷል። በዚህና በተያያዥ ምክንያቶች ቀጣሪዎቹ የሥራ ልምድ ያለውን መቅጠር ይመርጣሉ ይላሉ።
ዩኒቨርሲቲዎችና ቀጣሪ ተቋማት ተቀራርበው ቢሠሩ ክፍተቱ እንደሚፈታም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል። ክፍተቱን ለመሙላት ወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚ ሆኖ በመንቀሳቀስ ከተለያዩ ተቋማት ጋር ለመምከር፣ ተማሪዎችም ልምድ እንዲያገኙ፣ ቀጣሪ ተቋማትም በቦታው ተገኝተው ዕጩ ተመራቂዎችን ለመመልመል እንዲችሉ ዕድሉን ማመቻቸቱ ይበል የሚያስብል ሆኖ እንዳገኙት አስረድተዋል።
የትምህርት ማስረጃቸውን ለቀጣሪ ተቋማት ለማስገባት ዕድሉን ካገኙት የ2017ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ዕጩ ተመራቂዎች መካከል ኮሌጅ ኦፍ ኢንጂነሪንግ ሜካኒካል ትምህርት ክፍል ዕጩ ተመራቂ ኤሊያስ እጅጉ፤ ትምህርቱን ለአምስት ዓመት መከታተሉንና በዩኒቨርሲቲው የነበረው ቆይታም ጥሩ እንደነበር ነው የነገረን። ተመራቂዎች ግቢውን ለቀው ሳይወጡ ከቀጣሪ ተቋማት ጋር የሚገናኙበት ዕድል መመቻቸቱ ደግሞ በጣም እንዳስደሰተው ገልጿል። እርሱም የትምህርት ማስረጃውን (ሲቪ) ለአራት ድርጅቶች ማስገባቱንም ነው የነገረን።
የኢንፎርሜሽን ሲስተም (አይ ኤስ) ትምህርት ክፍል ተማሪ ዕጩ ተመራቂ የሆነችው፤ ሣሕለማርያም መኮንን፤ ለአራት ዓመታት ትምህርቷን መከታተሏንና በአጠቃላይ ውጤት ወደ ሦስት ነጥብ በማግኘት ለምረቃ መዘጋጀቷን ገልፃለች። ዩኒቨርሲቲው ያመቻቸውን ዕድል በመጠቀምም የትምህርት ማስረጃዋን(ሲቪ) ለሁለት ተቋማት ማስገባቷንና ቅጥሩ እንደሚሳካላትም ተስፋ አድርጋለች።
የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፋሪስ ደሊል (ዶ/ር)፤ ለ2017 ዓ.ም ዕጩ ተመራቂዎች የሥራ ዕድል ለማመቻቸት የተካሄደው የሥራና ሙያ ዓውደ ርዕይ በዩኒቨርስቲው ታሪክ የመጀመሪያ እንደሆነ ገልፀው፤ የተመቻቸው ዕድል ተማሪዎች ተቀጣሪ ብቻ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪ ለመሆንም መልካም ተሞክሮ ይፈጥርላቸዋል ብለዋል። ዩኒቨርሲቲው ከቀጣሪ ተቋማት ጋር ተቀራርቦ መሥራቱ የሚስተዋለውን የተማሪዎች የክህሎት ክፍተት በተሻለ ለመሥራት እንደሚያስችልም ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የትምህርት ጥራት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ፋንታዬ ጨምር፤ አምራች ኢንዱስትሪዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተቀራርበው መሥራታቸው ፋይዳው ከፍ ያለ እንደሆነ በመጥቀስ፤ ሁለቱ ተቋማት በጋራ እንዲሠሩ አዋጅና መመሪያ መኖሩንም ገልጸዋል።
እርሳቸው እንዳሉት፤ በ2011ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት አዋጅ መውጣቱንና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በመተማመን ላይ የተመሠረተ ለጋራ ዓላማ ተናብበውና ተግባብተው መሥራት እንዳለባቸው ግዴታ መቀመጡን አስረድተዋል። አዋጁ በአምራች ኢንዱስትሪው በኩል የሚስተዋለውን ክፍተት የሚደግፍ ባለመሆኑ፤ በ2015ዓ.ም የከፍተኛ ትምህርት፣ የቴክኒክና ሙያ፣ የምርምር ተቋማት ከአምራች ኢንዱስትሪዎች ጋር በትስስር መሥራት የሚያስችላቸው አዋጅ መውጣቱንና አዋጁም ከእያንዳንዱ ባለድርሻ የሚጠበቀውን በዝርዝር ማስፈሩን አስረድተዋል።
በለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም