
አዲሱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ዕሳቤ ሀብት ፈጠራን መለኪያ ያደረገ ነው
አዲስ አበባ፡- አዲሱ የመንግሥት ምልከታ የሥራ ዕድል ፈጠራን ከዳቦ በላይ አድርጎ የሚመለከት፣ ሀብት ፈጠራንም መነሻም መለኪያም ያደረገ ነው ሲሉ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለጹ።
ወይዘሮ ሙፈሪሃት የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው ሁለተኛው ምዕራፍ አምስተኛ የስለኢትዮጵያ መድረክ ላይ በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት እንደተናገሩት፤ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከተቋቋመ በኋላ ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ በመመልከት የክህሎት ልማትን፣ የሥራ ዕድል ፈጠራንና የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነትን የተመለከቱ ዘርፎችን በማስተባበር አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው። ከዚህም ጎን ለጎን የተቋም ግንባታን በተመለከተ ሰፊ ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።
ከእነዚህ የለውጥ ዓምዶች ውስጥ አንዱ የሆነው የሥራ ዕድል ፈጠራ ወትሮ ከምናውቀው አስተሳሰብ የተለወጠ ነው ያሉት ወይዘሮ ሙፈሪሃት፤ ቀደም ሲል የነበረው አስተሳሰብ በአመዛኙ የእለትን ፍጆታ እና ጉርስ ማሟላትን ታሳቢ ያደረገ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ያለው አስተሳሰብ ከዚህ የተለየ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከዳቦ በላይ ሀብት ፈጠራን መነሻውም መድረሻውም ያደረገ አስተሳሰብ የተላበሰ እንደሆነ ተናግረዋል።
ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ሰፊ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ሀብቶች አሏት፣ እነዚህን ሀብቶች በመለየት በምን መልኩ ብንሠራ ነው የላቀ ውጤት የምናመጣው የሚለውን ሀገራዊ ትልም በማስቀመጥ በተለይ ሀገር በቀል ኢኮኖሚ ሪፎርም ተግባራዊ በማድረግ እየተሠራ ነው።
በ10 ዓመቱ ፍኖተ ብልፅግና እቅድም ያሉንን ዕድሎችም፣ ተግዳሮቶችም በመለየት እየተሠራ መሆኑን አመልክተው፤ ኢንተርፕራይዞቻችንም ለአጭር ጊዜ ብልጭ ብለው የሚጠፉ እንዳይሆኑ ጥራት ባለው መንገድ የሚቀረጹና ወደ ተግባር ሲገባም ሀብት የሚፈጥሩ እንዲሆኑ በመሠራቱ ዘለግ ያለ ጊዜ የመጓዝ ዕድላቸው ሰፊ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ኢንተርፕራይዞች ክህሎት መር እንዲሆኑ እየተሠራ መሆኑን ገልጸው፣ እያንዳንዱ የሥራ ሂደት የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል አሟጦ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
በኢንተርፕራይዞችም የሰው ሀብት ልማት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሠራል ያሉት ሚኒስትሯ፣ ለዚህም የሥልጠና፣ የቴክኖሎጂ፣ የፋይናንስና መሰል ጉዳዮች ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ለመፍታት እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
በመድረኩ የሚድሮክ ግሩፕ ዋና አስፈጻሚ አቶ ጀማል አሕመድ “በሥራ ዕድል ፈጠራ የግሉ ዘርፍ ሚና” በሚል ጽሑፍ ያቀረቡ ሲሆን በዚህም የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ ዩኒቨርሲቲዎች እና የግሉ ዘርፍ በጥምረት የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ተናበው ሊሠሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የሚድሮክ ግሩፕ ለ74 ሺህ ዜጎች የሥራ ዕድል የፈጠረ መሆኑን ተናግረው፤ ኢትዮጵያ ካላት የሥራ አጥ ቁጥር አንጻር የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
አሁን ላይ ሁሉም ነጋዴ መሆን ይፈልጋል። ነገር ግን አብዛኛው ሰው አምራች ቢሆን ለብዙኃኑ የሥራ ዕድል መፍጠር ይቻላል ያሉት አቶ ጀማል፤ መንግሥት ለአምራቾች የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ የሀገር ውስጥ ምርት የሚያድግበት ሁኔታን ማመቻቸት እንዳለበት አመልክተዋል።
በመንግሥት አቅም ብቻ የሥራ ዕድል ፈጠራን ተደራሽ ማድረግ ስለማይቻል ለሥራ ዕድል ፈጠራ ትልቁ ተዋናይ የግሉ ሴክተር ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።
በኢትዮጵያ የግል አልሚዎች በብዛት የአገልግሎት ዘርፉ ላይ ትኩረት እንደሚያደርጉ ገልጸው፤ በቀጣይ ማምረት ላይ ብዙ ሥራ በመሥራት አምራች ኃይል ማፍራት እንደሚገባ አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የሚገኙ ባለሀብቶች ከትርፍ የዘለለ ለትውልድ ተሻጋሪ ሥራ በትኩረት ሊሠሩ ይገባል። ባለሀብቶች ትርፋቸው ሊሆን የሚገባው ሥራዬ ለሀገርና ለሕዝብ ምን አስተዋፅዖ አበረከተ የሚለው ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ኮሪያ የተፈጥሮ ሀብት ውስንነት ቢኖርባትም በነፍስ ወከፍ ከዓለም ትልቅ ገቢ ያላት ናት። ኢትዮጵያ በርካታ የተፈጥሮ ሀብት ያላት ስትሆን ገቢዋ ግን ዝቅተኛ መሆኑን ማወቅና ማሻሻል ይገባል ያሉት አቶ ጀማል፤ ኢፕድ ለሀገር ወሳኝ የሆኑ አጀንዳዎች በውይይት ዳብረው ከነመፍትሔያቸው ለሕዝብ እንዲቀርቡ ማድረጉ ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ቀጣይነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የቲና ማርት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወጣት ኢዘዲን ካሚልም “ሥራ ፈጠራ በኢትዮጵያ” በሚል የውይይት መነሻ ጽሑፍ ያቀረበ ሲሆን በዚህም ወጣቶች በችግሮች ውስጥ መፍትሔና ዕድል ፈጣሪ ለመሆን ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል ብሏል።
በተለይ የዲጂታል ዘርፉ የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል አሟጦ መጠቀም እንደሚገባና የፋይናንስ ተቋማት ስታርት አፖችን በመመደብ ከዘርፉ የሚገኘውን ሀብት መጠቀም እንደሚገባ ተናግሯል።
ወጣቶች ሥራ የለም ከሚል እሳቤ በመውጣት ሥራ ፈጣሪ ሊሆኑ እንደሚገባ የገለፀው ወጣቱ፤ በኢትዮጵያ ለሥራ ዕድል ፈጠራ አስተዋፅዖ የሚያበረክቱ የኢንኩቬሽን ማዕከላትን እና መሰል ተቋማትን በርካታ ወጣቶች እንዲያውቁት ሊደረግ እንደሚገባ አመላክቷል።
በኢትዮጵያ ብዙ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶች ቢኖሩም ወደ ገበያው ለመግባት ትልቁ ማነቆ ፋይናንስ መሆኑን አንስቶ፤ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የሥራ ዕድል ፈጠራን ለማስፋፋት ሀሳብ ላይ ኢንቨስት ሊያደርጉ እንደሚገባ ገልጿል።
የልማት ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ዋቄ “የፋይናንስ ግብዓት ለሥራ ዕድል ፈጠራ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የውይይት መነሻ ሀሳብ አቅርበዋል።
ልማት ባንክ የፖሊሲ ባንክ እንደመሆኑ መጠን ለተመረጡ የኢኮኖሚ ዘርፎች ማለትም በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በታዳሽ ኃይል ዘርፍ ለተሰማሩ ብድር እንደሚሰጥ ተናግረው፤ በዚህም ምርትና ምርታማነት፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና የእውቀትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ታሳቢ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በሊዝ ፋይናንስ፣ በፕሮጀክት ፋይናንስ እና በተለያዩ አማራጮች ብድር እንደሚሰጥ ጠቁመው፤ ኢንተርፕራይዞችን ለማሳደግ ከባለድርሻ ተቋማት ጋር በቅንጅት የመሥራት እና አዳዲስ ፖሊሲና አሠራሮችን የመዘርጋት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ያሉትን ሥራ አጥ ወጣቶች ወደ ሥራ ማስገባት የባንኩ ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አንስተው፤ የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ኢኮኖሚ ለማስገባት ጥናት መካሄዱን እና አዋጅ ለማስፀደቅ እየተሠራ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን መነሻ በማድረግ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ የመነሻ ሃሳቦች እያቀረቡ የሚመለከታቸው አካላት እንዲወያዩባቸው በማመቻቸትና የፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ሃሳቦች እንዲንሸራሸሩ በማድረግ 19 መድረኮችን በማዘጋጀት በርካታ ጉዳዮች ላይ የሃሳብ ገበያ እንዲፈጠር ሲሠራ መቆየቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀውና በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚያተኩረው ሁለተኛው ምዕራፍ አምስተኛ ዙር የስለኢትዮጵያ የፓናል ውይይት መድረክ ትናንት በአዳማ ከተማ ኃይሌ ሪዞርት መካሄዱ ታውቋል።
በሳሙኤል ወንደሰን
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 4 ቀን 2017 ዓ.ም