በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው መመሪያ ቀላል የጭነት ተሽከርካሪዎች ከጠዋቱ 12፡30 እስከ 4፡00 ሰዓት፣እንዲሁም ከቀትር በኋላ ከቀኑ 10፡00 እስከ ምሽት 2፡00 ሰዓት፤ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች ከማለዳው 12፡30 እስከ ምሽቱ 2፡00 ሰዓት ወደ ከተማ እንዳይገቡ፤ እንዳይንቀሳቀሱ ያዛል። እንዲሁም የሞተር ሳይክሎችንም እንቅስቃሴ ይገድባል። የኮንስትራክሽን ተሽከርካሪዎችም ከተማ መግባት፣ጭነትማራገፍና መጫን የሚችሉት ከምሽት 2፡00 ሰዓት እስከ ንጋቱ 12፡30 ሰዓት እንደሚሆን መመርያው ያስገድዳል።
ይህ መመሪያ ለከተማዋ ብሎም ለሀገሪቱ አኮኖሚ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚያስገኝ መንግሥት ቢያሳውቅም የተለያዩ ቅሬታዎች እየቀረቡበት ነው። በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ የመመሪያው ዓላማ፣ አተገባበር፣ ከተተገበረ በኋላ የተገኙ ስኬቶች፣ እቀረቡ ያሉ ቅሬታዎችና የማስተካከያ ዕርምጃዎች ዙሪያ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ አድርገዋል። ሙሉ ቃለ ምልልሱን እንደሚከተለው አቅርበናል።
አዲስ ዘመን፡– በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው መመሪያ ዋና ዓላማው ምንድን ነው?
ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፡– በከተማችን ያለው የትራንስፖርት ስርዓት ሲታይ በጣም ችግር ያለበት ነው። ብዙ ዓይነት ተሽከርካሪዎች በአንድ መንገድ ሲንቀሳቀሱ ነው የምናየው። የተለያዩ የተሽከርካሪ ዓይነቶች በአንድ መንገድ ላይ የሚንቀሳቀሱ ከሆነ ስርዓት ያለው ፍሰት ማረጋገጥ አይቻልም። እንደዚሁም የትራፊክ አደጋን መቆጣጠርና መቀነስ አይቻልም። ይህ ችግር ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት ይታያል። መመሪያውን ለማዘጋጀት አንዱና መሰረታዊ ምክንያት ይህ ነው። የትራፊክ ፍሰቱ እንዲሻሻልና የትራፊክ ደህንነቱን በተለይም የሞት አደጋን ለመቀነስ ነው መመሪያው እንዲወጣ የተደረገው።
ሁለተኛው አጠቃላይ በከተማው ያለው ፍሰት በጣም የተጨናነቀ ነው። ይህም ከመሆኑ የተነሣ ኢኮኖሚው ላይ በጣም ትልቅ ጫና እያደረሰ ነው። በአዲስ አበባ ከተማ በጥቂቱ 2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በቀን በትራንስፖርት ይንቀሳቀሳል። በቀን ይህን ያህል የሚንቀሳቀስ ብር በእያንዳንዷ ምርትና በእያንዳንዷ እንቅስቃሴ ትንጸባረቃለች። የትራንስፖርት እንቅስቃሴ በ10 በመቶ እንኳ ብናሻሽለው እስከ 230 ሚሊየን ብር በቀን ማዳን ይቻላል። ይህ ገንዘብ በተለያየ መልኩ ወደ ህብረተሰቡ ይሄዳል ማለት ነው። ቀስ በቀስ የአገልግሎትና የምርቶች ዋጋ ይቀንሳል። የዚያን ያህል ብር ማዳን ይቻላል።
ዕርምጃዎች ካልተወሰዱና የፍሰቱ ሁኔታ በዚህ ደረጃ ከሄደ ከተማችን ጭራሽ መንቀሳቀስ ወደማይቻልበት ሁኔታ ትሄዳለች። ሆኖም ግን ይህ ሁሉ እንቅስቃሴ የሚካሄደው በቀኑ ክፍለ ጊዜ ውስጥ ነው። የማታው ክፍለ ጊዜ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የሌለበት ከተማ ነች – ከተማችን። ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ስለማይደረጉ ውጤታማ የሆነች ከተማ አይደለችም።
ከተማችን ግን ቀን ብቻ አይደለም የሥራ ዕድል መፍጠር ያለባት። ቀን ብቻ አይደለም ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሊደረጉ የሚገቡት። ከተቻለ 24 ሰዓት መሠራት አለበት። ያ ማለት አንድ ሰው 24 ሰዓት ይሠራል ማለት አይደለም። አንዱ መሥራት ያለበትን ያህል ሲሠራ ሌላው ይቀጥላል ማለት ነው። አንዱ በሚተኛበት ሰዓት ሌላው ይሠራበታል። ሌላው በሚሠራበት ሰዓት ሌላው ይተኛል ማለት ነው። ስለዚህ የከተማው ኢኮኖሚ ብዙ ሰው መሸከም የሚችል ኢኮኖሚ ይሆናል ማለት ነው። ከተማችን ግን የሌሊት እንቅስቃሴ ስለሌላት ለሥራ ብቻ ሳይሆን ለደህንነት አስጊ የምትሆንባቸው ሁኔታዎች አሉ።
ስለዚህ የሌሊቱ ክፍለ ኢኮኖሚ መጠቀም ከተቻለ የሌሊት ክፍለ ጊዜን ማነቃቃት ይቻላል። ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ሲኖሩ ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ይፈጠራሉ። የጸጥታ ስጋቶችም ይቀንሳሉ። ምክንያቱም ተንቀሳቅሶ የሚሠራ ሰው ካለ ስጋት አይኖርም። የሰዎች እንቅስቃሴ መኖር ለሰዎች መልካም የደህንነት ስሜት እንዲሰማቸው የራሱ የሆነ ዋጋ አለው። ከዚህ አንጻር ከተማችን በጣም ወደ ኋላ የቀረች ነች። ሌሊት ትተኛለች። መተኛት ግን የለባትም። ስለዚህ ይህን መመሪያ ማዘጋጀት ያስፈለገበት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው።
በተለይ የሎጂስቲክስ ትራንስፖርት በጣም ተጎድቷል። የጭነት ትራንስፖርቶችን ሦስት ችግሮች እያጋጠሙት ነው። አንዱ ጊዜ ነው። የተሽከርካሪውም የሰውም ጊዜ በመንገድ ላይ እየጠፋ ነው። ተሽከርካሪው ልክ የአዲስ አበባ መንገድ ሲጀምር ብዙ ሰዓት እየፈጀበት ነው። በቀን ክፍለ ጊዜ በተጨናነቀ ትራፊክ ላይ መሄዱ ችግር አምጥቷል። አንዱ ችግር በተፈለገው ጊዜ መድረስ ወዳለበት ቦታ አይደርስም። ለጉዞም የሚፈጅበት ጊዜ ረጅም ስለሆነ የሎጂስቲክሱ ዋጋ ውድ እንዲሆን አድርጎታል። መጫኛና ማራገፊያ ቦታዎችም በጣም የተጨናነቁ ናቸው። መንገዶችም የተጨናነቁ ናቸው። ስለዚህ ከአዲስ አበባ ውጪ ያደረገውን ጉዞ ባይሆን እንኳ በመጣበት ፍጥነት መድረስ ወዳለበት ቦታ አይደርስም። ይህን ችግር መፍታት በጣም ወሳኝ ነው።
ያ ደግሞ የዕቃዎች ዋጋ እንዲጨምር ያደርገዋል። ምክንያቱም ጊዜ ካጠፋ በቂ ገቢ ስለማያገኝ መኪናውም ብዙ መሥራት ስለማይችል የዕቃዎች ዋጋ ይጨምራል ማለት ነው። ሁለተኛው ነዳጅ ወጪም ይጨምራል። ተሽከርካሪዎቹ እየቆሙ እየተነሱ ስለሚሄዱ ብዙነዳጅ ይፈጃል። የነዳጅ ወጪ መጨመሩ በራሱ የዕቃዎች ዋጋ እንዲጨምር ያደርጋል። ነዳጅ የሚመጣው በውጭ ምንዛሬ እንደመሆኑ የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታችን ከፍ እንዲል አድርጓል።
ሦስተኛ መለዋወጫ ዕቃ /ስፔር ፓርት/ ነው። በተለይ ፍሬን ሸራ፣ ዲ ኤል ዜድ፣ የመሳሰሉ በፍጥነት የሚያልቁ መለዋወጫ ዕቃዎች አሉ። ያ ደግሞ የመለዋወጫ ዕቃዎች ፍላጎቶችን ከፍ ያደርገዋል። የሎጂስቲክስ ዋጋም እንዲጨምር ያደርጋል። ለመለዋወጫ ዕቃዎች ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት ምንዛሬም በዚያው ልክ ይጨምራል ማለት ነው። በአጠቃላይ በማክሮ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጫና ያደርሳል። አዲስ አበባ ዋና የሎጂስቲክስ ማዕከል ሆና እያገለገለች ስለሆነ በአዲስ አበባ ደረጃ ይህን ችግር ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት በሀገር አቀፍ ደረጃም የራሱ ሆነ ፋይዳ አለው። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ነው መመሪያ ማውጣት አስፈላጊ የሆነው።
አዲስ ዘመን፡– መመሪያው ወደ ሥራ ከገባ ወር ሊሆነው ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ምን ውጤት ተገኘ?
ዶክተር ሰለሞን፡– ውጤቱን ለመለካት መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት የነበረው የከተማው የትራፊክ ፍሰት ፍጥነት ይታወቃል፤ ከዚህ በፊት የነበረው የአደጋ መጠን እናውቀዋለን፤ መረጃውም አለን። አሁን ያለው ነገር ለማወቅ ደግሞ መረጃ መሰብሰብ አለበት። በተለያዩ ባለሙያዎች መረጃው እየተሰበሰበ ነው ያለው። ያንን መረጃ መሰረት ተደርጎ የመጠው ውጤት የትንተና ሥራ ይሠራል። የህዝብ አስተያየትም እየተሰበሰበ ነው። የህዝብ አስተያየት ቁጥርን በትክክል አይገልጸም። ነገር ግን የሆነ ምስል ይሰጣል። እኛ በቁጥር የምንገልጻቸው ነገሮች በህብረተሰቡ ላይ የአስተያየት ለውጥ ካልፈጠረ ለውጥ ማለት አይቻልም። ስለዚህ ከዚህ አንጻር ሲታይ ብዙ ሰው ከፍሰት አንጻር የተሻለ ሆኗል የሚል ግብረ መልስ እየሰጠ ነው። የሰው አስተያየት ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ማለት ነው። ሰው ለውጥ እንዳለ ማየት ጀምሯል ማለት ነው።
ሁለተኛ የህዝብ አስተያየት ደግሞ ትንንሽ መኪናዎችና ትላልቅ መኪናዎች አንድ ላይ ስለማይነዱ፤ በአንድ መንገድ አንድ ዓይነት መኪኖች ስለሆኑ ያሉት በአሽከርካሪው ላይ የእፎይታ ስሜት እንዲፈጠር አድርጓል። ትናንሽ መኪኖችና ትላልቅ መኪኖች አንድ ላይ ሲነዳ በትናንሽ መኪኖች አሽከርካሪዎች ላይ የሆነ የሚፈጠር ስሜት አለ። አደጋ ሊከሰት ይችላል፤ ሊገጨኝ ይችላል የሚል ስሜት ውስጥ ይገባሉ። ያ ስሜት በጣም ቀንሷል። ይሄ ራሱ ትልቅ ውጤት ነው ብለን ነው የምናስበው። ስለዚህ የህዝብ አስተያየት ላይ ለውጥ እንዳለ ማየት ተችሏል።
አሉታዊ አንድምታውና ሊከሰት ይችላል ተብሎ የተገመተው የጭነት ዘርፍ ላይ የተሰማረው አካላት በተለያዩ መንገዶች ቅሬታ እያቀረቡ ነው። ማታ መሠራት አንችልም፤ የማታው ክፍለ ጊዜ መብራት የለም፤ እንዲሁም የደህንነት ጉዳይ ያሰጋናል የሚሉ ቅሬታዎች በተለያዩ መንገዶች እያቀረቡ ነው። ሌሎች ደግሞ የኛ ምርት የተለየ ምርት ነው፤ ይበላሻል፤ እኛ ላኪዎች ነን ስለዚህ መንቀሳቀስ የምንችለው በቀኑ ክፍለ ጊዜ ብቻ ነው፤ ኮንስትራክሽን ነን ዋጋው ይወደድብናል የሚል ብዙ ቅሬታዎች እየተነሱ ነው። እነዚህ አካላት ቅሬታ እያቀረቡ ያሉት በውጤቱ ላይ ሳይሆን በእነሱ ላይ በሚያሳድረው ኢኮኖሚያዊ ጫና ላይ ነው። እነዚህ ነገሮች ሊነሱ እንደሚችሉ መጀመሪያም የተገመተ ነበር።
አዲስ ዘመን፡– የጭነት መኪኖች ቀን ምርት ይዘው ከተማ ውስጥ መግባት ስላልቻሉ፤ ፊታቸውን ወደ ሌሎች ክልሎች እያዞሩ ስለሆነ በከተማዋ ውስጥ የሸቀጦች እጥረት እያጋጠመ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ይህን ችግር እንዴት ለመቅረፍ እየተሠራ ነው?
ዶክተር ሰለሞን፡– ሰው ወደ አዲስ አበባ ዕቃውን ጭኖ የሚመጣው ገበያ ስላለ ነው። ገበያውን ፍለጋ ነው። ስለዚህ ገበያው እስካለ ድረስ ከገበያው ሰው አይሸሽም፤ ገበያውን ይፈልገዋል። ቀን መሸጥ አልቻልንም የተባለውም አሳማኝ ምክንያት አይደለም፤ ማራገፍ መሸጥ አይደለም። አከፋፋዮች ዕቃ ከውጭ እንዳመጡ ወደ መጋዘን ነው የሚገባው። ከመጋዘን በኋላ ነው የሚሰራጨው። ስለዚህ ወደ መጋዘን የማስገባት ሥራ ማታ መሥራት ይቻላል። አንድ ኮንቴይነር ማታ መጥቶ መጋዘን ውስጥ ማራገፍ ይችላል። የጭነት ሠራተኞች ደግሞ ሥራ ነው የሚፈልጉት።
ማታ ሥራ ካለ ይሠራሉ። ማታ አልሠራም የሚል ካለ ሌላ አማራጭ ሥራ አለው ማለት ነው። ይህ በግልጽ ያለ ነገር ነው። አይሱዝና ትናንሽ መኪኖች ቀን ቀን ስለተፈቀዱ ከ4፡00 እስከ 10፡ 00 ማሰራጨት ያለበት ያሰራጫል። ምክንያቱ እየቀረበ ያለው መመሪያው አስቸጋሪ ሆኖ ሳይሆን ከተለመደው አሠራር ላለመውጣት የሚደረግ ጥረት ነው። ያ ጊዜ ይፈልጋል፤ ተቋማዊ ሆኖ፤ ባህል ሆኖ ሰው እስኪለምደው ድረስ ቢያንስ ሦስት ወር ተግባራዊ ማድረግ ይጠይቃል።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ቀደም እናንተ ጋር የመጡ ቅሬታዎች ካሉ በምን ዓይነት መልኩ መፍትሔ እንደተሰጠው ቢነግሩን?
ዶክተር ሰለሞን፡– እኛ ጋር በጣም ብዙ ቅሬታዎች እየመጡ ነው። ከመንግሥት መስሪያ ቤቶች ጀምሮ እስከ ግል ድርጅቶች ድረስ ይመጣል። ትላልቅ የጭነት መኪኖች በቀን ክፍለ ጊዜ በከተማዋ እንዳይንቀሳቀሱ መደረጉ መልካም ነገር ቢሆንም የኛ ተልዕኮ የተለየ ስለሆነ ሊፈቀድልን ይገባል፤ እያሉ የሚመጡ አሉ። ሁሉም የየራሱን ጉዳይ ልዩ አድርጎ ያቀርባል። ሁሉም የሚያቀርበውን ምክንያት ተቀብለን የምንፈቅደው ከሆነ ድሮ እንደነበረው ይሆናል ማለት ነው። እኛ ለኢኮኖሚው ያለውን ጥቅም ነው የምናየው። በቀን የማይቻል ነው ወይ? በቀን የማይቻል ከሆነና ውጫዊ ምክንያቶች ካሉ መፍትሔ እንዲሰጠው ይደረጋል።
ለምሳሌ አበባ ኤክስፖርት ይደረጋል። ኤክስፖርት የሚደረገው በአውሮፕላን ነው። ይህ ከኛ ቁጥጥር ውጪ ነው። የበረራ ክፍለ ጊዜያችሁን አስተካክሉ ማለት ስለማይቻል፤ ኤክስፖርት ደግሞ ወሳኝ ስለሆነ ለእነዚህ ምላሽ ይሰጣል። ሌላኛው ምሳሌ ቡና ኤክስፖርት እናደርጋለን። ቡና ኤክስፖርት የሚደረገው በባህር ነው። እነዚህ ሌሊትም እየወሰዱ ማድረስ ይችላሉ። ኤክስፖርት ነኝ ስላለ ብቻ በቀን የመንቀሳቀስ ፈቃድ አያገኝም። አሠራሩን ቀይሮ በማታ ክፍለ ጊዜ ብቻ መንቀሳቀስ የማይቻል ከሆነ ብቻ ነው ፈቃድ የሚሰጠው።
አዲስ ዘመን፡– እየተነሱ ካሉ ቅሬታዎች አንጻር መመሪያውን ሊያስቀይር የሚችል ነገር ያለ ይመስሎታል?
ዶክተር ሰለሞን፡- መመሪያውን ለማስቀየር ጫና ለመፍጠር የሚሞክሩ አሉ። አንዳንድ ከዚህ ቀደም የተቀየሩ መመሪያዎች ልምድም ስላለ ይቀየራል ብለው የሚያስቡ አሉ። ነገር ግን እስከአሁን ያለው ሁኔታ እንደሚያሳየው ምንም የሚቀየር ነገር የለም። መፍትሔው አሁን ሥራ ላይ መዋል የጀመረውን መመሪያውን ሥራ ላይ ማዋል ነው። ያ ሲደረግ የግል ዘርፉ ለራሱ ሲል መጋዘኑን ሌሊት ይከፍታል፤ ሌሊት ያራግፋል። መመሪያው ከወጣ በኋላ ሌሊት ማራገፍ የጀመሩ አሉ።
እኛ ይህን መመሪያ ከማጽደቃችን በፊት የጀመሩም ነበሩ። ለምሳሌ መንገድ ከዚህ ቀደምም ሌሊት ሌሊት ሲሠራ ነበር። የግንባታ ሥራ የሚሠሩ ኮንትራክተሮችም አሉ። ሌሊት ሌሊት ዕቃቸውን የሚያራግፉም ነበሩ ስለዚህ ምንም አዲስ ነገር አይደለም። ስለዚህ እያልን ያለነው አዲስ አበባ መዘመን አለባት፤ ከተማዋ ሌሊት መቆም የለባትም። የተጀመረው ነገር ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ነው እያልን ያለነው።
እንደዚህ ዓይነት ለውጦች ለመጀመሪያ ጊዜ ይጎረብጣሉ። ከቀጠሉ ግን በኢኮኖሚው ላይ ያለው ጠቃሜታ በጣም ከፍተኛ ነው። መንገዶቻችን አሁን ስታያቸው ለየት ይላሉ። አያስጨንቅህም። ይህ ትልቅ ነገር ነው። ህብረተሰቡ እየታየ ያለውን ነገር የሚፈልገው ከሆነ ይቀጥላል። ህብረተሰቡ ማይፈልገው ቢሆን እንተወው ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ሞተር ሳይክሎች እያቀረቡ ያለው ቅሬታ ምንድን ነው። በናንተ በኩልስ እየተሰጠ ያለው መፍትሔ ምንድን ነው ?
ዶክተር ሰለሞን፡– ሞተር ሳይክሎች አንዳንዶቹ የራሱ የሆነ የህግ ክፍተቶች ስላሉ በህግ ያልተፈቀዱ ሥራዎች ጭምር ነው ሲሠሩ የነበሩት። ህገ ወጥ ሥራ ሲሠሩ የነበሩትም ተላምደዋል። እኛም ያ እየተሠራ ዓይተን ዝም ማለታችን ተለምዶ እንደ ህግ ይወሰዳል። ያ በመሆኑ አሁን መመሪያ ሲወጣ ብዙ ቅሬታዎች እየቀረቡ ነው።
አዲስ ዘመን፡– የቅሬታዎቹ ጭብጦች ምንድን ናቸው ?
ዶክተር ሰለሞን፡– ጭብጡ ‹‹ለኛ የሥራ ዕድል ነው›› የሚል ነው። እንድንንቀሳቀስበት ይፈቀድልን ሳይሆን እንድንሠራበት ይፈቀድልን ነው እያሉ ያሉት። ሰው ማመላለሻ እንድንሠራበት ይፈቀድልን ነው። እያሉ ያሉት ይህ መብታችን ነው። የእንጀራችን ምንጭ ነው፤ የኑሯችን ምንጭ ነው የሚሉ ጥያቄዎች እያቀረቡ ነው። ከሥራ ዕድል ፈጠራ አንጻር ሲታየው እውነት ነው። በዚህ ሲተዳደር የነበረው ወጣት ከዚህ ሥራ ስታስወጣው በወጣቱ ላይ ቀላል ጫና አይፈጥርም። አጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ ችግር ይፈጥራል። መፍትሔ መስጠት ግድ ይላል።
አዲስ ዘመን፡– በናንተ በኩል የታሰቡ መፍትሔዎቹ ምንድን ናቸው?
ዶክተር ሰለሞን፡– መፍትሔው ጂፒ ኤስ ቴክኖሎጂ ትራክ እንዲደረጉ (ቁጥጥር እንዲደረግባቸው) ማድረግ ነው። መመሪያው ሲወጣም የተሰጣቸው አንድ መፍትሔ አለ። ፒ ኤል ሲ ወይም ሼር ካምፓኒ ሆነው ድርጅት ሆነው መምጣት አለባቸው። ህጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ይዘው ቢመጡ ሥራቸውን መቀጠልና መንቀሳቀስ ይችላሉ። ይህንን ማድረግ ግን አይፈልጉም። ዝም ብለው መንቀሳቀስ ነው የሚፈልጉት። ያ ደግሞ ለቁጥጥር አይመችም። 20 ሺ ሞተር ሳይክሎችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ተደራጅተው ሥራ የጀመሩ አሉ?
ዶክተር ሰለሞን፡– አዎ አሉ። ትንሽ አቅም ያላቸው ወደ ድርጅት ቀይረው መንቀሳቀስ የጀመሩ አሉ።
አዲስ ዘመን፡– የጀመሩት ምን ያህል ይሆናሉ?
ዶክተር ሰለሞን፡– ቁጥሩን በእርግጠኝነት አላውቀውም። መረጃው አሽከርካሪ ተሽከርካሪ ነው የሚገኘው። እንደነ ፖስታ ቤቶች ህጋዊ ፈቃድ አግኝተው ተመዝግበው ወደ ሥራ ገብተዋል። ሌሎቹም ወደዚሁ መንገድ እንዲገቡ ብዙ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው።
አዲስ ዘመን፡– በመጨረሻም መመሪያውን አስመልክተው ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ ዕድል ልስጥዎት ?
ዶክተር ሰለሞን፡– ትራንስፖርት ብዙ የሥራ ዕድል የሚፈጥር ዘርፍ ነው። ዋናው ግን መታየት ያለበት ትራንስፖርት የኢኮኖሚ ማቀጣጠያ መሳሪያ እንጂ ራሱ ኢኮኖሚ ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። መጀመሪያ መሥራት ያለብን እንዴት የሥራ ዕድል ይሁን ሳይሆን እንዴት ማቀጣጠያ ይሁን ነው። ሲያቀጣጥል ትራንስፖርት ይዞት ከሚመጣው የሥራ ዕድል በላይ ብዙ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ያደርጋል። ትልቅ ኢኮኖሚ እንዲፈጠር ማድረግ ይችላል። ስለዚህ እንዴት ነው ኢኮኖሚያችን መቀጣጠል የሚችለው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል።
ፍሰቱን ካሳለጥክ፤ በቀን አንድ ጊዜ ምልልስ ያደርግ የነበረው ተሳልጦ ሁሌ ምልልስ ማድረግ ከቻለ ሁለት ቦታዎች ስለሚሄድ ሁለት አገልግሎት ማግኘት ከቻለ ሁለት ሱቆችን ማንቀሳቀስ ይችላል። ሁለት ሱቆች ውስጥ የሥራ ዕድል ይፈጠራል ማለት ነው። ሌላ ኢኮኖሚ ተፈጠረ ማለት ነው። በዚያ ልክ ፍጆታ ይፈጠራል። በትርፍ ሰዓቱ ትምህርት መማር የሚፈልግ ይማራል። ህክምና መታከም የፈለገ መታከም ይችላል። ፈጣን ትራንስፖርት ካለ ምርታማ ያደርጋል። ብዙ የሥራ ዕድልም ይፈጠራል። ማየት ያለብን እሱ የሚፈጥረውን የሥራ ዕድል ሳይሆን ኢኮኖሚያችንን ማሻገር እንዲችል ነው ማሰብ ያለብን።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ቃለ ምልልስ አመሰግናለሁ።
ዶክተር ሰለሞን፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2011
መላኩ ኤሮሴ