
ከሦስት ዓመታት በላይ ለዘለቀ ጊዜ ደም አፋሳሽ በሆነ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያና ዩክሬን ስለሰላም አማራጭ ለመነጋገር ተወካዮቻቸው ሁለተኛ ዙር የፊት ለፊት ውይይታቸውን በቱርኪዬ፤ ኢስታንቡል አካሂደዋል። ከአንድ ሰዓት ብዙም ባልበለጠው ውይይት፣ ሁለቱ ወገኖች እስረኞችን፣ የተፈናቀሉ ሕፃናትንና የሞቱ ወታደሮችን አስከሬን ለመለዋወጥ ከመስማማታቸው ባለፈ ስለተኩስ ማቆምም ሆነ ዘላቂ የሰላም ድርድር ይህ ነው የሚባል ውይይት አላደረጉም።
ዩክሬን አሁንም የ30 ቀናት ተኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቃለች። ሩሲያ ግን የምትፈልገው በውጊያ የሞቱ ወታደሮቿን አስከሬን ለማንሳት የሚያስችል የሁለት ወይም የሦስት ቀናት ተኩስ አቁም ነው። ሩሲያ ተኩስ ለማቆም ያስችላል ያለችውን ዝርዝር እቅድና ቅድመ ሁኔታ አቅርባለች። የፕሬዚዳንት ፑቲን አማካሪና የሩሲያ ተወካዮች መሪ ቭላድሚር ሜዲንስኪይ ሞስኮ ጥልቅ የሆነና በሚገባ የተደራጀ የስምምነት እቅድ ለኪዬቭ ማስረከባቸውን ተናግረዋል። የዩክሬን ተወካዮችም የሩሲያን እቅድ ሰነድ መረከባቸውንና በዝርዝር ተመልክተው ምላሻቸውን እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል።
የ30 ቀናት የተኩስ ማቆም እቅዱ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካና የዩክሬን ተወካዮች በሳዑዲ ዓረቢያ ካደረጉት ውይይት በኋላ በአሜሪካ ይፋ የተደረገ እቅድ ነበር። ይህ እቅድ በዩክሬን በኩል ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ሩሲያ እቅዱን ለመቀበል ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርባ ነበር። ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አሜሪካ ስላቀረበችው የተኩስ አቁም እቅድ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሀገራቸው ተኩስ የማቆምን ሃሳብ በአወንታዊነት እንደምትቀበለው ገልጸው፣ በወቅቱ ግልጽ ምላሽና ማብራሪያ የምትፈልግባቸው ጉዳዮች እንዳሉ አስረድተዋል።
‹‹ግጭትን ለማስቆም ተኩስ አቁም ማድረግ ትክክለኛ ሃሳብ ነው። ሩሲያም በመርሕ ደረጃ ተኩስ ማቆምን ትደግፋለች። ነገር ግን ከአሜሪካ ጋር ልንወያይባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ›› ያሉት ፑቲን፣ ሞስኮ የተኩስ አቁም ስምምነቱን እንድትተገብር መሟላት ስላለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች መዘርዘራቸው ይታወሳል። ዩክሬን የተኩስ አቁም ጊዜውን መሣሪያ ለመሰብሰብ እና ኃይል ለማደራጀት ልትጠቀምበት ትችላለች ብለውም ይሰጋሉ። ይህ እንዳይሆንም ዋስትናው ምን እንደሆነ ጠይቀዋል። ‹‹የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተቆጣጣሪ ማን ነው?›› የሚለው ጥያቄም ፑቲን በቅድመ ሁኔታነት ያነሱት ጉዳይ እንደነበር ይታወሳል።
የዩክሬን የመከላከያ ሚኒስትርና የሀገሪቱ ተወካዮች መሪ ሩስተም ኡሜሮቭ ሩሲያ የ30 ቀናት የተኩስ ማቆም እቅዱን አለመቀበሏ ጦርነቱን ለማቆም ፍላጎት እንደሌላት ማረጋገጫ እንደሆነ ተናግረዋል። ሀገራቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የሚተገበር የ30 ቀናት ተኩስ ማቆም እንዲደረግ በያዘችው አቋሟ እንደጸናችም ጠቁመዋል። የሩሲያው ሜዲንስኪይ ግን ሀገራቸው በጥቂት የጦር ግንባሮች ብቻ የሚተገበር አጭር የተኩስ አቁም አማራጭን ለመቀበል ዝግጁ እንደሆነች ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲንና ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ በዚህ ወር መገባደጃ ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲወያዩ ዩክሬን ፍላጎት እንዳላት ኡሜሮቭ ተናግረዋል። ‹‹ሁሉም ወሳኝ ጉዳዮች መፍትሔ የሚያገኙት በመሪዎች ደረጃ በሚደረግ ውይይት እንደሆነ በጽኑ እናምናለን›› በማለት ከሁለቱ መሪዎች በተጨማሪ ጦርነቱን ለማስቆም የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕም በውይይቱ ቢሳተፉ መልካም እንደሚሆን ኡሜሮቭ ጠቁመዋል።
ሩሲያ ተኩስ ለማቆም ያስችላል ያለችውና ለዩክሬን ተወካዮች ያቀረበችው ዝርዝር እቅድ ለዩክሬንና አጋሮቿ ፈፅሞ የሚዋጥ አይደለም። እቅዱ ዩክሬን ሩሲያ የግዛቴ አካል ናቸው ካለቻቸው አራቱ ግዛቶች (ዶኔትስክ፣ ሉሃንስክ፣ ዛፖሪዢያና ኬርሶን) ጦሯን እንድታስወጣና ግዛቶቹ የሩሲያ አካል እንደሆኑ እውቅና እንድትሰጥ፣ የጦር ዘመቻ ዝግጅቷንና ስምሪቷን እንዲሁም ከምዕራባውያን አጋሮቿ የጦር መሣሪያ መቀበሏን እንድታቆም፣ የሌሎች ሀገራት ሠራዊት ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ፣ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን የመቀላቀል ሃሳቧን እንድትተው፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንድታነሳና ፕሬዚዳንታዊና የፓርላማ ምርጫ እንድታካሂድ እና ከዩክሬን ቋንቋ በተጓዳኝ ሩሲያኛን መንግሥታዊ የሥራ ቋንቋዋ እንድታደርግ ይጠይቃል። ዩክሬንና ምዕራባውያን አጋሮቿ ግን ከዚህ ቀደምም እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችን ውድቅ አድርገዋል።
ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ እንደተመለደው ሩሲያ ጦርነቱን የማቆም ፍላጎትና ዝግጁነት እንደሌላት ጠቁመው፣ ጠንካራ ማዕቀቦች ሊጣሉባት እንደሚገባ በድጋሚ አሳስበዋል። ፕሬዚዳንቱ በሊቱዌኒያ በተካሄደ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባላት የፀጥታ ጉባዔ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ‹‹ውይይቱ ምንም ለውጥ ካላመጣ ሩሲያ አዳዲስ ማዕቀቦች በአስቸኳይ ሊጣሉባት ይገባል›› ብለዋል።
የቱርኪዬ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን የሩሲያና ዩክሬን ተወካዮችን ውይይት ‹‹አስደናቂ›› ሲሉ ገልጸውታል። ‹‹ትልቁ ምኞቴ ፑቲንና ዘለንስኪ እንዲሁም ትራምፕ ወደ ኢስታንቡል ወይም አንካራ እንዲመጡና በጋራ እንዲነጋገሩ ነው›› ብለዋል።
ሁለተኛው ዙር ውይይት ዩክሬን በሩሲያ የአየር ኃይል ማዘዣ ጣቢያዎች ላይ ያልተጠበቀና መጠነ ሰፊ የሆነ ጥቃት በፈፀመች ማግሥት መካሄዱ ብዙዎች ከውይይቱ አዎንታዊ ውጤት እንዳይጠብቁ አድርጓቸዋል። ዩክሬን አንድ ዓመት ከመንፈቅ በላይ ስትዘጋጅበት ቆይታለች በተባለው በዚህ ጥቃት በሩሲያ ላይ ከሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ ኪሳራ አድርሻለሁ ብላለች። ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ‹‹የዩክሬን ትግል ማርሽ ቀያሪ ጥቃት›› ብለው ያሞካሹት ይህ ዘመቻ፣ ዩክሬን ድሮኖችን ወደ ሩሲያ ግዛቶች አስርጋ በማስገባት የፈፀመችው ጥቃት እንደሆነ ተገልጿል። በጥቃቱ ሩሲያ ካሏት ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መካከል ሲሶውን ያህል እንዳጣች የዩክሬን ባለሥልጣናት ተናግረዋል። ሩሲያ በበኩሏ በዩክሬን ጥቃት እንደተፈፀመባት አምና የደረሰባት ጉዳት ግን የዩክሬን የደኅንነት ቢሮ በገለጸው ልክ የሚጋነን እንዳልሆነና ብዙዎቹን ድሮኖች ማክሸፏን ገልፃለች።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የሁለቱ ሀገራት ተወካዮች የመጀመሪያውን ዙር የፊት ለፊት ውይይት በዚያው በቱርክ አካሂደው ነበር። ከሁለቱ ሀገራት ተወካዮች እንዲሁም ውይይቱን ካስተባበሩት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳንና ሌሎች የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በተጨማሪ የአሜሪካ ተወካዮችም ኢስታንቡል መገኘታቸው የሚታወቅ ነው።
የሩሲያና የዩክሬን ባለሥልጣናት ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ፊት ለፊት የተገናኙበትና ለሁለት ሰዓታት የዘለቀው የመጀመሪያው ዙር ውይይት ጉልህ የሆነ ውጤት ሳያስገኝ ቢጠናቀቅም፣ በከባድ ጦርነት ውስጥ በሚገኙት በሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት መካከል የፊት ለፊት ግንኙነት እንዲጀመር ያስቻለ ትልቅ ርምጃ ተብሎ ተወድሷል።
ሁለቱ ሀገራት ፊት ለፊት እንዲገናኙ ሃሳቡን ያመነጩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ነበሩ። ይሁን እንጂ ፑቲን ለንግግር ቱርክዬ ሳይገኙ ቀርተዋል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ዘለንስኪ ወደ ቱርክ አቅንተው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር ተነጋግረው እንደነበር ይታወሳል። ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ የሩሲያው መሪ ፑቲን ለውይይት ኢስታንቡል አለመገኘታቸው ሩሲያ ተኩስ ለማቆምም ሆነ ለዘላቂ የሰላም ስምምነት ፍላጎት እንደሌላት ማሳያ እንደሆነ እና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሩሲያን ቸልተኝነት ተገንዝቦ በተለይ አሜሪካ በሩሲያ ላይ ጫና ማሳደሯን መቀጠል እንዳለባትም አሳስበዋል። በመጀመሪያው ዙር ውይይት እንደስኬት ሊቆጠር የሚችለው ሁለቱ ሀገራት፣ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ትልቁ ነው የተባለውን፣ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ እስረኞችን ለመለዋወጥ መስማማታቸው ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሦስት ሳምንታት በፊት በመካከለኛው ምሥራቅ በጉብኝት ላይ ሳሉ፣ እርሳቸው እና ፑቲን በአካል እስኪገናኙ ድረስ በሩሲያ-ዩክሬን ውይይት ላይ ከፍተኛ መሻሻል የማይታሰብ መሆኑንና ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በተቻለ ፍጥነት መገናኘት እንደሚፈልጉ ተናግረው ነበር። ‹‹እኔና ፑቲን እስክንገናኝ ድረስ ምንም ነገር አይከሰትም። እኔ ከሌለሁ አይሄድም። እናም እኔ እና እሱ እስክንገናኝ ድረስ ተወደደም ተጠላም ምንም ነገር ይከሰታል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች እየሞቱ ስለሆነ መፍትሔ ማግኘት አለብን›› ብለዋል።
ከሳምንት በፊት ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከሁለት ሰዓታት በላይ የዘለቀ የስልክ ውይይት አድርገው ነበር። ከውይይቱ በኋላም ሁለቱም መሪዎች የስልክ ውይይታቸው ገንቢና መልካም እንደነበር በየፊናቸው ተናግረው ነበር። ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር እንደሚጀምሩም ፕሬዚዳንቱ ገልፀው ነበር። በተለይም ፕሬዚዳንት ፑቲን ሀገራቸው ለጦርነቱ ሰላማዊ አማራጭን እንደምትደግፍ እንዲሁም ከዩክሬን ጋር ለመሥራት እና ወደፊትም የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆናቸውንም መግለፃቸው ይታወሳል።
ትራምፕና ፑቲን ዘለግ ላለ ጊዜ በስልክ ተወያይተው ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር እንደሚጀምሩ ተስፋ ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፈው ሳምንት በዩክሬን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ክፉኛ እንደተበሳጩ መናገራቸው የሚታወስ ነው። ከዚህም አልፎ ትራምፕ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነትን እንዲያስቆሙ የሁለት ሳምንታት ቀነ ገደብ እንደሰጡና ይህ የማይሆን ከሆነ ግን ሀገራቸው በሩሲያ ላይ ከባባድ ማዕቀቦችን እንደምትጥል አስጠንቅቀዋል።
ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩት ጥረቶች ሁሉ ትርጉም ያለው ውጤት ማስገኘት አልቻሉም። ሁለቱም ሀገራት የሚፈፅሟቸውን ጥቃቶች አጠናክረው ቀጥለዋል። ሩሲያ ተኩስ ለማቆም ያስችላል ባለችው ዝርዝር እቅድ ውስጥ የተካተቱት ቅድመ ሁኔታዎቿም በዩክሬንና በምዕራባውያን አጋሮቿ ተቀባይነት ያገኛሉ ተብሎ አይታሰብም። ጦርነቱን ለማስቆም የተሻለ አቅም አላት ተብላ የምትታመነው አሜሪካ ከአንድ ወር በፊት ከዩክሬን ጋር የተፈራረመችው ለብሔራዊ ጥቅሟ የሚበጃት የማዕድን ስምምነት፣ አሜሪካ ከዩክሬን የማዕድን ሀብት ተጠቃሚ እየሆነች ለዩክሬን የጦር መሣሪያና የመረጃ ድጋፍ እንድታቀርብ የሚያስችል በመሆኑ ጦርነቱ እንዲቀጥል የማድረግ ሚናው ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ ‹‹ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ›› ተብሎ ተሰይሞ የነበረውና በጥቂት ጊዜያት ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተነግሮለት ከሦስት ዓመታት በፊት የተጀመረው የሩሲያ-ዩክሬን ግጭት፤ ዛሬም ሕይወት እየቀጠፈና ንብረት እያወደመ ቀጥሏል። ለዚህም ነው ብዙ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ‹‹ሩሲያና ዩክሬን የመስማማት ተስፋ አላቸው? ዘላቂ የተኩስ አቁም ብሎም የሰላም ስምምነትስ ይፈራረሙ ይሆን…?›› ብለው አበክረው የሚጠይቁት።
በአንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 27 ቀን 2017 ዓ.ም