
– መምህራን ቅድሚያ ይሰጣቸዋል
– ሠራተኛው 25 በመቶ እንዲቆጥብ ይጠበቃል ፤ባንክ 75 በመቶ ብድር ያቀርባል
አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ25/75 በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የቤቶች ልማት ፕሮጀክት በጋራ ለማልማት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ። የስምምነት ፊርማውን የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በጋራ አካሂደዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ በስምምነት ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ቤት የሌላቸው የመንግሥት ሠራተኞችን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ነው። የመንግሥት ሠራተኛው 25 በመቶ እንዲቆጥብ የሚጠበቅ ሲሆን፤ 75 በመቶ በባንክ ብድር ይቀርባል ብለዋል።
የብድሩ ጊዜ ለ20 ዓመት የሚከፈል መሆኑን ጠቅሰው፤ 41 ሺህ በከተማዋ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል። ከፕሮጀክቱ የአዲስ አበባ መምህራን ቅድሚያ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ገልጸዋል።
በመኖሪያ ቤት እጦት እየተቸገሩ የሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች ፕሮጀክቱ ጥያቄያቸውን የሚመልስ በመሆኑ እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ የመንግሥት ሠራተኞችን የቤት ችግር መቅረፍ የሚያስችል መሆኑን አመልክተው፤ ባንኩም 120 ቢሊዮን ብር ብድር እንደሚያቀርብ ጠቁመዋል። የብድር ወለዱ 14 በመቶ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለ20 ዓመት የሚቆይ መሆኑን ገልጸዋል።
በፕሮጀክቱ ለሦስት ዓመት የግንባታ ጊዜና አንድ ዓመት ደግሞ የብድር መክፈያ የእፎይታ ጊዜ ተሰጥቷል ብለዋል።
ስምምነቱ የመንግሥት ሠራተኞችን በተመጣጣኝ ዋጋ የቤት ባለቤት የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ አላስፈላጊ ወለድ የሌለው መሆኑንም ተናግረዋል።
የቤት ዕድሉ ቅድሚያ ተጠቃሚ ለመሆን በማህበር ተደራጅተው ቅድመ ሁኔታዎችን ያሟሉት የከተማዋ መምህራን መሆናቸው በተሰጠው መግለጫ ላይ የተገለጸ ሲሆን፤ በሂደት ሁሉም ቤት የሌላቸው የከተማ አስተዳደሩና የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የመርሃ ግብሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል።
ማርቆስ በላይ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 17 ቀን 2017 ዓ.ም