ኢድ አል-አድሃ (አረፋ) የመታዘዝ ጥግ የታየበት ታላቅ በዓል !

የአረፋ በዓል በሂጅራ ዘመን አቆጣጠር በ12ኛው ወር በ10ኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው። የአረፋ በዓል የሚከበርበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖርም ጎልቶ የሚወጣው ነቢዩ ኢብራሂም (ዐ.ሰ) አንድያ ልጃቸውን እስማኤልን እንዲሰዉ ከፈጣሪያቸው የወረደላቸውን ትዕዛዝ ለመፈጸም ያሳዩትን ቁርጠኝነት እና ታዛዥነትን ለመዘከር የሚታሰብ መሆኑ ነው።

ነቢዩ ኢብራሂም በነቢይነት ዘመናቸው የእምነታቸውን ጽናት የሚፈታተን አንድ ነገር አጋጠማቸው። ይሄውም አንድያ ልጃቸውን መስዋዕት ያደርጉ ዘንድ ከአላህ ዘንድ መታዘዛቸው ነበር። የልጃቸው ፍቅር ክፉኛ ቢያስጨንቃቸውም ትዕዛዙ የፈጣሪያቸው ነውና ሊፈጽሙ ከመካ ወደ አረፋ ተራራ ወጡ። ልጃቸውን መስዋዕት ለማድረግ ቆረጡ፤ በፈጣሪያቸው ትዕዛዝ ላይ አንዳችም ሳያመነቱ ትዕዛዙን ለመፈጸም ተነሱ።

ነቢዩ ኢብራሂም በብዙ ዱዓና የፈጣሪ ተማፅኖ ያገኙትን ብቸኛ ልጃቸውን እስማኤልን ሊያርዱት አጋደሙት። እርሱም ሳያንገራግር ለዕርድ ተዘጋጅቶ ተኛ። ነቢዩ ኢብራሂም ልጁን ሊያርዱት ሲሞክሩ ግን ቢላዋው አላርድ ቢላቸው እንደገና ቢላዋውን ገዘገዙት /ሣሉት/፤ ነገር ግን ጭራሽ ፈጽሞ ዶለዶመ ታዛዡ ልጅ የሆነው ነገር አልገባውም።

አባቱ ቶሎ ስላላረዱትም ተገረመና “አባዬ!፣ ምናልባት የአባትነት ፍቅር ይዞህ ይሆናል በቶሎ ያላረድከኝ፤ እስቲ ዓይኔን በጨርቅ ሸፍነውና እርዱን ሞክር” አላቸው።

በዚህን ጊዜ ግን ከወደ ሰማይ ጥሪ መጣ። የአላህ መልዓክ “ኢብራሂም ታላቅነትህን አስመስክረሃልና እርዱን አቆየው” በማለት አወጀ። በምትኩም መልዓኩ ታዞ ያመጣውን በግ እንዲያርዱና ልጁን ወደ ቤት እንዲወስዱት ነገራቸው። በዚህም መሠረት በጉ ታረደ።

ኢብራሂምና እስማኤልም ወደ መካ ከተማ ተመለሱ። ሁለቱ ሰዎች ለአላህ መታዘዝን በግልጽ ያሳዩባት ያቺ ዕለት የዒድ አል-አድሃ /አረፋ/ በዓል ሆና እንድትከበርም ተወሰነ። በየዓመቱም እየተከበረ ዛሬ 1446ኛ ዓመተ ሂጅራ ደርሷል።

በዚህ ታላቅ በዓል ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ክንውኖች አሉ። አንደኛው የበዓሉ ገጽታ ከፍተኛ ሆነ መረዳዳት የሚታይበት በዓል መሆኑ ነው።

በዚህ በተከበረ ቀን የመስዋዕትነት ተምሳሌት የሆነ በግ ማረድ ይኖራል። ከታረደውም በግ 1/3ኛውን ለድሃ የማካፈል ግዴታ ያለበትና ሁሉም በዓሉን በእኩልነት የሚያሳልፍበት በዓል ነው። በዚህ ዕለት ሁሉም ጠግቦ እና ተደስቶ እንዲውል ሙስሊሞች ያላቸውን በማካፈል ያሳልፉታል።

ሌላኛው ገጽታው ቤተሰብ፤ ዘመድ አዝማድ በጋራ የሚያሳልፉት በዓል መሆኑ ነው። በዓሉን ከሃይማኖታዊ ትሩፋቱ ባለፈ የቤተሰባዊ እሴት ማጠናከሪያ እና መሰባሰቢያ በዓል ተድርጎ ስለሚታሰብ በተለያየ ምክንያት ተለያይተው የሚኖሩ ቤተሰቦች ይሰባሰቡበታል። ሕጻናት በበዓል አልባሳት ደምቀው ስጦታ ለጎረቤቶቻቸው በማበርከት ያሳልፋሉ።

በተለይም ኢትዮጵያን ለየት የሚያደርጋት እስላምና ክርስቲያኑ በመጠራራት በዓሉን በጋራ የሚያከብሩባት ድንቅ ሀገር መሆኗ ነው። ኢትዮጵያ ለእስልምና ሃይማኖት መስፋፋት ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያበረከተችና በእንግዳ ተቀባይነቷም ዝንተዓለም ስሟ የሚነሳ ሀገር ናት። ይህን መነሻ በማድረግም ሃበሾችን መሠረት ያደረጉ ከ23 በላይ የቁርዓን አንቀጾች፣ በሃበሾች ቋንቋም ከ30 በላይ የቁርዓን አንቀጾች እንዲወርዱ፤ በተጨማሪም በነብዩ መሐመድ /ሰዐወ/ ሰበብ ስለ ሃበሾች ክብር ከ27 ያላነሱ ነቢያዊ ሃዲሶች እንዲነገሩ ምክንያት እንደሆኑ ይነገራል።

በአጠቃላይ ኢድ አል-አደሃ (አረፋ) የአብሮነት እና የመረዳዳት በዓል ነው። በተለይም በኢትዮጵያ የኢድ አል-አድሃ (አረፋ) አከባበር ለየት የሚልባቸው እሴቶች አሉት። ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተለያዩ እምነቶችን በፀጋ የተቀበለችና የተለያዩ እምነት ተከታዮችም ተከባብረው የሚኖሩባት ታሪካዊ ሀገር ናት። አረፋን በመሳሰሉ የበዓል ወቅት ደግሞ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ የክርስትና ዕምነት ተከታዮች የሆኑ ጎረቤቶችን በመጥራት በዓሉን በጋራ ማሳለፍ የተለመደ ነው። ይህ አንዱ ኢትዮጵያዊ ዕሴት ሲሆን ለዘመናትም ሲወርድ ሲዋረድ ዛሬ ላይ የደረሰ ድንቅ መገለጫችን ነው።

ከአረፋ በዓል ዕሴቶች አንዱና ዋነኛው የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ነው። የእስልምና እምነት በአረፋ ወቅት ድሆችን ከሚያስብበትና በዓሉንም በደስታ እንዲያሳልፉ በአማኞች ላይ ግዴታ ከጣለባቸው ትዕዛዞች አንዱ ከሚታረደው ከብት 1/3ኛው ላጡና ለተቸገሩ ወጎኖች የሚሰጥ መሆኑ ነው። ይህ ደግሞ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖች በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ የሚያስችልና የመረዳዳት ዕሴትንም የሚጨምር ነው።

በተለይም በአሁኑ ወቅት በግጭት እና ሌሎች ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያቶች የተፈናቀሉ በርካታ ወገኖች በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ይገኛሉ። ስለዚህም እነዚህን ወገኖችን መደገፍና ተባብሮ ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው መመለስ አንዱ በአረፋ ወቅት የሚከወን ተግባር ሊሆን ይገባል!

አዲስ ዘመን ዓርብ ግንቦት 29 ቀን 2017 ዓ.ም

 

Recommended For You