አከራካሪው የዘረመል ምህንድስና የግብርና ምርት በምሁራን ዕይታ

ዜና ትንታኔ

በዓለም አቀፍ ደረጃ በዘረመል ምህንድስና የተሻሻሉ ምርቶች (ጂኤምኦዎች) በዘመናዊ ግብርና፣ በምግብ ዋስትና እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ ስለሚያደርሷቸው ጉዳቶች እና ጥቅሞች በርካታ ውይይቶችና ክርክሮች ይደረጋሉ፡፡

የምርቶቹ ተቃዋሚዎች ከጂኤምኦዎች ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ ስለሚችሉ አደጋዎች ሲያብራሩ፤ የረዥም ጊዜ የጤና ችግሮችን ያስከትላል፡፡ የአካባቢ ተፅዕኖ እና ሌሎች ጉዳዮችን እንደሚያስከትል እያነሱ ስጋታቸውን በጥናት አስደግፈው ይሞግታሉ።

በሌላኛው ጎራ ያሉ የምርቱ ደጋፊዎች ለምርት መጨመር፣ ፀረ ተባይን ለመቀነስ እና የተሻሻሉ የአመጋገብ ይዘቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ጥቅሞችን ይሰጣሉ ሲሉ ይገልጻሉ። እነዚህ ጥቅሞች እንደ ረሃብ እና የሀብት እጥረት ያሉ ዓለም አቀፍ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ወሳኝ ናቸውም ይላሉ።

ወደእዚህ ክርክር ስንገባ፣ ምርቶቹ በእኛ የምግብ ሥርዓት እና በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚችላቸው ሚና ለመረዳት ሁለቱንም ጉዳቶችና ጥቅሞች ማመዛዘን አስፈላጊ ነው። በእዚህ ጉዳይ በያዝነው ሳምንት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ በዘረመል ምህንድስና ዘዴ የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ጥቅምና ጉዳት ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ አካሂዷል። በእለቱም የተገኙት የግብርና ሳይንስ ተመራማሪዎች ቴክኖሎጂው ላይ ያላቸውን እውቀት አጋርተዋል፡፡

የግብርና ሳይንስ ተመራማሪው ዶክተር ፀደቀ አባተ እንደሚሉት፤ በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ያለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር በ2050 ዓ.ም 205 ሚሊዮን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል። ይህንን ሕዝብ ለመመገብ እስከ 60 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ሰብል ያስፈልጋል።

እየተመረተ ያለውም ምርት ከሕዝብ ቁጥሩ ጋር የማይጣጣም ነው። ነገር ግን ይህንን ምርት ለማሻሻል መፍትሔው ሀገር በቀል ቴክኖሎጂን በመጠቀም እና ‘ኮሜርሻላይዝድ ፋርሚንግ’ በማስፋፋት ምርቱ እንዲጨምር ማድረግ እንጂ በዘረመል ምህንድስና የሚመረቱ ምርቶች በማስፋፋት በፍፁም የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አይቻልም ይላሉ። የምግብ ዋስትናችን ሊረጋገጥ የሚችለው በራሳችን ምርምር ነው። ልማትም በሦስተኛ ወገን አይረጋገጥም ብለዋል።

እንደ ዶክተር ጸደቀ ገለጻ፤ ከውጭ የምናስገባው የፓልም ዘይት ነው። እኛ ግን የምንልከው ሰሊጥ ነው። ሁለቱ በጥራት አይገናኙም። የሀበሻ ሱፍ ዘይት ከኦሊቭ የተሻለ ነው። ነገር ግን ይሄንን ምርት ለማሻሻል እና ለኅብረተሰቡ በበቂ ሁኔታ እንዲደርስ ለማድረግ ምን መደረግ አለበት? የሚለው አስፈላጊ ጥያቄ ነው። በዘረመል ምህንድስና የግብርና ምርት ይጨምራል የሚለው አስተሳሰብ መሬት ላይ ካለው እውነታ የራቀ ነው።

በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የምርጥ ዘሮች በዘረመል ምህንድስና ከሚመረቱ ወይም ከውጭ ከሚመጡ ዘሮች የተሻለ ውጤት እንዳላቸው ዶክተር ጸደቀ ተናግረዋል።

በዘረመል ምህንድስና የበለፀጉ ምርቶችን የተጠቀሙ ከአፍሪካ ሀገራት የቡርኪና ፋሶ፣ የታንዛኒያ እና የህንድ አርሶ አደሮች ላይ ለከፍተኛ ኪሳራ ማጋለጡን ተናግረዋል። በመጨረሻም ላቲን አሜሪካን፣ አውሮፓ እና አንዳንድ የኤዥያ ሀገራት ለምን በእዚህ ቴክኖሎጂ የሚመረቱ ምርቶችን ተጠየፉት? ስለሚለው ራሳችንን መጠየቅ  ይገባናል ብለዋል።

ተመራማሪ ፕሮፌሰር ፍሬው መክብብ በበኩላቸው፤ በዶክተር ፀደቀ አባተ ሃሳብ አይስማሙም። ይልቁንስ ኢትዮጵያ ላይ እየተሠሩ ያሉ የባዮቴክኖሎጂ ሥራዎች የሚደነቁ ናቸው ይላሉ። የባዮቴክኖሎጂ ሥራዎች ሲሠሩም የሕግ ማሕቀፎች እንደሚያስፈልግም ይናገራሉ። በባዮቴክኖሎጂ የሚገኙ ውጤቶች ጥቅም ላይ የሚውሉት ጉዳት እንደማያደርሱ ሲረጋገጥ ብቻ መሆኑንም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያም ለሚቀጥሉት 20 ዓመታት በዘርፉ ላይ ሊሠሩ ስለሚገቡ ሥራዎች አቅዳ ለመፈጸም እየተንቀሳቀሰች ነው። ከእቅዶቿ ውስጥ አንዱ በአፍሪካ የባዮ ቴክኖሎጂ ሃብ መሆን አንዱ ነው። የቴክኖሎጂው ጥቅም ላይ መዋል በቀላሉ የሚታይ ሳይሆን የሕልውና ጉዳይ መሆኑንም ፕሮፌሰሩ ይናገራሉ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ በኢትዮጵያ በዘረመል ምህንድስና የሚመረቱ የግብርና ምርቶች ጥቅማቸው እና ጉዳታቸው በሚገባ ተጠንቶ በዓለም የምግብ ድርጅት እና በዓለም የጤና ድርጅት ይሁንታን ያገኙ ናቸው። በዘረመል ምህንድስና የሚመረቱ ምርቶችም ከባቢ አየርን የማይጎዱ፣ ኢኮኖሚካል ጠቀሜታ ያላቸው እና ምርትን በማብዛት ገበሬውን የሚጠቅሙ ናቸው።

በመድረኩ የተሳተፉት የግብርና ሳይንስ ተመራማሪው ፕሮፌሰር ጥልዬ ፈይሳ በበኩላቸው፤ የዘረመል ምህንድስና ቴክኖሎጂ በተለይ በሕክምና ሳይንስ በከፍተኛ ደረጃ ውጤታማ የሆነ ቴክኖሎጂ መሆኑን ይናገራሉ። በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ዜጋ የምግብ ዋስትናውን አላረጋገጠም። ስለዚህ ይህንን የግብርና ግብአት በመጠቀም የሀገሪቱን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ይገባልም ይላሉ።

ቴክኖሎጂውም በግብርና ምርቶቹ ውስጥ የሚገኘውን ንጥረ ነገር ‘የኒውትሪሽን’ ለማሻሻል፤ የሚመረተውን ምርት ለማብዛት የሚጠቅም ይሆናል። ጥቅም ላይ ከመዋሉም በፊት የስጋት ቁጥጥር ዘዴ ‘ሪስክ ኮንትሮል ሜትድ’ እና የስጋት ለይታ ‘ሪስክ አይደንቲፊኬሽን ሜትድ’ ያለው መሆኑን ይገልጻሉ።

ብራዚልን ጨምሮ ሌሎች የዓለማችን ሀገራት በዘረመል ምህንድስና የሚመረቱ ምርቶችን ከማምረት ባለፈ ለሌሎች ሀገራት ኤክስፐርት ያደርጋሉ፤ በዘረመል ምህንድስና የሚመረቱ ምርቶች ምንም አይነት የጤና ጉዳት የማያመጡ እና ውጤታማነታቸው በተግባር የተረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል። ኢትዮጵያም ቴክኖሎጂውን በየትኛውም ሀገር ተጽእኖ ሳይደረግባት የምትጠቀም መሆኑን ፕሮፌሰር ጥልዬ ይናገራሉ።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ፤ ቴክኖሎጂውን ተግባራዊ እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ሥራውን በሀገራዊ ኃላፊነት ወስደው የሚሠሩ ናቸው፤ ቴክኖሎጂው ለሀገር የማይጠቅም ቢሆን ተግባራዊ የሚያደርጉበት ምክንያት የላቸውም ብለዋል።

መክሊት ወንድወሰን

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ግንቦት 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You