የዲጂታል ኢትዮጵያ ምስክሮች

በሰው ልጅ የሥልጣኔ ጉዞና በዓለም የዕድገት ታሪከ ከትላንት እስከ ዛሬ ያለ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን የተለወጠ ማኅበረሰብና ያደገ ሀገር የለም። በአሁን ወቅትም በተግባር የተደገፈ ሳይንሳዊ ምርምርና የፈጠራ ውጤት ዓለምን እጅጉን ቀላልና ለሰው ልጅ ምቹ አድርጓታል፡፡

በቅርብ ዓመታት ውስጥ አስደናቂና ፈጣን እድገት ያስመዘገቡ ሀገራት ሁለንተናዊ ስኬት ዋነኛ ምክንያት የቴክኖሎጂ እውቀትና ክህሎትን በመጠቀም ገበያ መር ኢኮኖሚን መገንባታቸውና የቴክኖሎጂ አቅም የማካበታቸው ድምር ውጤት ነው፡፡

አንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው። ዛሬ በሣይንስና ቴክኖሎጂ በልጽገው ሁለንተናዊ ልማትን በማምጣት የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ያጐለበቱ ሀገራት ልምድ የሚያሳየንም ይህንኑ ሐቅ ነው፡፡

የቴክኖሎጂን ሁለንተናዊ ገፀ በረከት ለመቋደስ ወሳኝ ከሆኑት መሠረቶች መካከል ደግሞ የዲጂታል ሥነ ምህዳሩን መገንባት እና የዲጂታል ክህሎት ማጎልበት አንዱና ዋነኛው ነው። በኢትዮጵያ ቀደም ባሉት ዓመታት በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የሚያካትቱ የዲጂታል ክህሎት ፕሮግራሞች ተቀርፀው በስፋት አልተተገበሩም። ይህም አካታች የዲጂታል ኢኮኖሚ ልማትን እውን ከማድረግ አንጻር ትልቅ ተፅእኖ ሲፈጥር ቆይቷል። ይሁንና ባለፉት ስድስት ዓመታት በተለይም የወጣቶችን ዲጂታል አቅም በመገንባት ኢትዮጵያ በዲጂታል ዘመን ወደ ኋላ የቀረችበትን ዘመናት ለማካካስና የሀገሪቱን ነገ ለማሳመር ዘርፈ ብዙ ጥረቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በሰኔ ወር 2012 ዓ.ም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ቀርፃ እና አፅድቃ ወደ ሥራ ገብታለች። ዲጂታል ኢትዮጵያ የዲጂታል ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል ነው፡፡

ከሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳና የአስር ዓመት የልማት ዕቅድን ከመሳሰሉ ቁልፍ ሀገራዊ ስትራቴጂዎች ጋር እንዲሁም እንደ አፍሪካ ህብረት አህጉራዊ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ ካሉ ዓለም አቀፍ ስትራቴጂዎች ጋር የተሳሰረም ነው፡፡

ዲጂታል ኢትዮጵያ የመንግሥትን፣ የግሉን ዘርፍና የልማት ኤጀንሲ ተዋንያንን በአንድ ላይ በማሰባሰብ፣ መሠረታዊ የዘርፍ ተነሳሽነቶችን በመለየት የሀገሪቱን ዲጂታል ኢኮኖሚ ጉዞን ለማሳለጥ እንዲሁም የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በግንባር ቀደምትነት ለመምራት የሚችሉና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ሊጠቀሙ የሚችሉ ስትራቴጂያዊ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎችን ለይቷል። ግብርና፣ የማምረቻ ዘርፍ፣ የመረጃ ቴክኖሎጂና ቱሪዝም ቅድሚያ ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል ናቸው።

ስትራቴጂያው ግብርናው እሴት እንዲጨምር የሚያግዙ የቴክኖሎጂ ሥርዓቶችን መዘርጋትና መተግበር፤ በግብርና ዘርፍ ቴክኖሎጂ ሥራ ፈጠራን መደገፍ እና ማበረታታት፤ በማምረቻው ዘርፍ አዳዲስ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን የመፍጠር እና ጥቅም ላይ ማዋል፤ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሻሻል የሎጀስቲክ ሥራ አመራርን በቴክኖሎጂ ማጎልበት፤ ከፍተኛ አቅም እና ተሰጥኦ ላላቸው ማዕከላት መሠረተ ልማት ማቅረብና የመረጃ ቴክኖሎጂ ፓርክን በማዋቀር እና በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ በማስገባት የሚሉትን ያካተተ ነው፡፡

የቱሪዝም ዲጂታላይዜሽን ግብረ ኃይል በማቋቋም የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ዲጂታላይዝ ማድረግ፣ የቱሪስት ፍሰትን እና የቆይታ እና ተሳትፎ መጠኑን ማሻሻል፤ የቱሪዝም ዘርፍ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የበይነ መረብን ከመጠቀም እና ዲጂታል ክፍያን ከመቀበል አንስቶ ሌሎችንም የዲጂታል ቴክኖሎጂዎች አጠቃቀምን ማጎልበትንም የሚያጠቃልል ነው፡፡

ስትራቴጂው በዋናነት የዲጂታል መሠረተ ልማት፤ ዲጂታል መታወቂያ፣ ዲጂታል ክፍያዎች እና የሳይበር ደህንነት የሚጨምረው አስቻይ ሲስተምች ልማት፤ ኤሌክትሮኒክ መንግሥት እና ኢኮሜርስን የሚያካትተው የዲጂታል ፕላትፎርሞች ልማት፤ የፋይናንስ ተደራሽነት፣ የዲጂታል እውቀት እና የዲጂታል ፖሊሲ እና ሕግ ማሕቀፍ የተካተቱበት የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ልማት በስፋት ይመለከታል፡፡

በኢትዮጵያ ዲጂታላይዜሽን አሠራር ትርጉም ባለው መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ያለመው ይህ ስትራቴጂ፣ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ለውጦች እንዲመዘገቡ ጉልህ አቅም ተፈጥሯል።

በኢትዮጵያ የሚፈለገውን እድገትና ለውጥ ለማምጣት ዲጂታል ምጣኔ ሀብት ዋነኛ ምሰሶና ስትራቴጂ ሆኖ ተቀይሷል። በዚህ ደግሞ ከዲጂታል ዘመን ጋር አብሮ መሄድ የሚያስችሉ የኃይል፣ የዳታ፣ የዲጂታል መታወቂያና ሌሎች አስቻይ ሁኔታዎች በሕግ፣ በስትራቴጂና በተቋማት መሠረት እየያዙ ናቸው።

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያን ነገ ለማሳመር በተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በተለይም የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት በመዘርጋት፣ የዲጂታል አገልግሎት በማስፋት እንዲሁም የዲጂታል መታወቂያ ተደራሽ በማድረግ አመርቂ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም ለአብነት ከ15 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን እና ነዋሪዎቿ የዲጂታል መታወቂያ ይዘዋል፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ የዲጂታል መሠረት ተብለው ከተለዩት ጉዳዮች የበይነ መረብ ግብይትን ኢ-ኮሜርስ አንዱ ነው። ባለፉት ሶስት አራት ዓመታት በኢንተርኔት እና የሞባይል አገልግሎቶች መስፋፋት እና የዲጂታል ሕግ እና የሬጉላተሪ ማሕቀፎች ሥራ ላይ መዋልን ተከትሎ ከፍተኛ እድገት ካሳዩ ዘርፎች ውስጥ ኢ-ኮሜርስ ይገኝበታል። ኢትዮጵያም የሀገር ውስጥና የውጭ ንግዷን ለማሳደግ ኢ-ኮሜርስ ላይ በቁርጠኝነት እየሠራች ትገኛለች፡፡

መንግሥት የሀገሪቱን የንግድ ምህዳር በማስፋት የገበያ ሥርዓቱን እንዲዘምን የተለያዩ የሕግ ማሻሻያዎችን እያደረገም ይገኛል። በኢትዮጵያ የበይነ መረብ ግብይትን (ኢ-ኮሜርስ) የተሳለጠና ፍትሐዊ ለማድረግ ለሁሉም ምቹ የሆነ የአሠራር ሥርዓትን ለመዘርጋትም እየሠራ ነው። የብሔራዊ የኢ-ኮሜርስ ስትራቴጂ ረቂቅ ሠነድ ዝግጅቱም የነገዋን ዲጂታል ኢትዮጵያ እውን የማድረግ ምስክር ነው፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመንና የዜጎችን የኑሮ ጫና ለማቃለል አብዛኛው የሕዝብ አገልግሎት ዲጂታል እንዲሆኑ እየተደረገ ነው። ቴሌብር አማካኝነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተለይም በገጠር አካባቢዎች ያሉ ድሃ ማህበረሰቦች ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ በማስቻል የፋይናንስ አካታችነት ላይ ለውጥ ማምጣት ተችሏል።

የኤሌክትሮኒክ መንግሥት አገልግሎት የሚመራበት የቀጣይ 5 ዓመት ስትራቴጂ እና የመንግሥት ተቋማት ተቋማዊ መዋቅር ተዘጋጅቶ ግብዓት እየተሰበሰበ ይገኛል። ከ2016 እስከ 2020 ዓ.ም ተግባራዊ የሚደረግው ስትራቴጂ የመሠረተ ልማት ግንባታ፣ መተግበሪያ ልማት፣ የሰው ኃይል ልማት፣ አወቃቀር እና በጀትን አካትቶ በመያዝ የመንግሥትን የዲጂታላይዜሽን ራዕይ ያስቀመጠ ነው። ይህም የኢትዮጵያን የዲጂታል ሽግግር ለማፋጠን ከሁነኛ አቅሞች አንዱ ነው፡፡

ወቅታዊውም ሆነ ቀጣዩ ዓለም ከሁሉም በላይ የዲጂታል ክህሎትን የግድ የሚል ነው። ዘመኑ ቴክኖሎጂ የሥራ መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የለውጥ አራማጅ የሆነበት ምዕራፍ ላይ ደርሷል። የኢትዮጵያ ነገ ዲጂታል ነው። የሀገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በወጣቶች እጅ እንደሚሆንም ይታወቃል። የነገዋን ኢትዮጵያ የሚቀርፁት የፈጠራ ባለሙያዎች እና ተመራማሪዎችም ወጣቶች ናቸው።

የኢትዮጵያን ነገ ለማሳመር አሁን ላይ ወጣቶችን ለማብቃት፣ ፈጠራን ለማጎልበት እና የዲጂታል ዘመንን ግዙፍ አቅም ለመጠቀም መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ከሚያሳዩ ፕሮግራሞች መካከልም፣ ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር አጋማሽ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ይፋ የተደረገው የ5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የኮደርስ ሥልጠና ፕሮግራም አንደኛው ነው። በዚህ ፕሮግራም ዋነኛ አላማው ወጣቱ ትውልድ በዲጂታል ሥነ ምህዳሩ ውስጥ ንቁ ተሳታፊና አምራች እንዲሆን የሚያስችሉ ክህሎቶችን ማስታጠቅና ማብቃት ነው፡፡

21ኛው ክፍለ ዘመንን የሚመጥኑ ወጣቶችን ለማፍራት የተወጠነው ይህ ፕሮግራም፣ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው መስክ ወደፊት እንድትገሰግስ በር የሚከፍት ብሎም የሀገሪቱን የዲጂታል ኢኮኖሚ ትርጉም ባለው መልኩ ለማጎልበት ከፍተኛ አቅም የሚፈጥር ነው።

በኢትዮጵያ ክህሎት ያለው የሰው ኃይልን በመገንባት ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች በአገልግሎቱ ዘርፍ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ያግዛል። በዲጂታል መንገድ የሚራመድ ዘመናዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥን እውን በማድረግ ረገድ ያለው አበርክቶም እጅጉም ከፍተኛ ነው፡፡

ዲጂታል ዘመን እያደገ ሲሄድ በተቋማት ላይ የሚሰነዘሩ የሳይበር ጥቃቶችም እየጨመሩ መምጣታቸው ርግጥ ነው። ኢትዮጵያ የሳይበር ደህንነትን ለሚያስጠብቁ ሥራዎች ልዩ ትኩረት ሰጥታለች። ለዚህም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር፣ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ጠንካራ ተቋማት እየተፈጠሩ ናቸው። ዛሬ ላይም የኢትዮጵያን ነገ የሚያሳምሩ፣ ሀገሪቱ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ተወዳዳሪ እንድትሆንም ለቀጣዩ ትውልድ መሠረት የሚሆኑ ሥራዎች እየተከናወኑ ናቸው፡፡

ዛሬ ላይ የሰው ሠራሽ አስተውሎት/ጉዳይ ከሳይንስ አልፎ የማሕበራዊ፣ የኢኮኖሚ፣ የደህንነት፣ የሳይበር ጦርነት፣ የወታደራዊ ዝማኔ፣ የሉዓላዊነትና የልዕለ ኃያልነት እርካብ መቆናጠጫ ከመሆን አልፎ የጂኦፖለቲካ ሚዛን መለኪያ እየሆነ ይገኛል፡፡

በዓለም አቀፍ ደረጃ “AI” አሁን ላይ ከባድ ማዕበል አስነስቷል። ለክርክር በማይቀርብ መልኩ መጭው ዘመን የ “AI” ነው። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የእያንዳንዳችን የሕይወት ቅንጣት መንካቱ በአኗኗራችንና በግንኙነታችን ላይ የዝሆን ዳናውን ማሳረፉ አይቀሬ ነው። ይህ እንደመሆኑ በርካታ ሀገራት AI ላይ ጊዜና ገንዘባቸውን ፈሰስ በማድረግ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ ተጠምደዋል፡፡

ኢትዮጵያን በአፍሪካ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ግንባር ቀደም የሚያደርጋትን ደረጃ እውን ለማድረግ እየተጋች ትገኛለች። ለዚህ ውጥን ስኬትም የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አቋቁማለች። ተቋሙ ከእድሜ አንጻር ገና ቢሆንም እየተንቀሳቀሰ ያለው ግን ከዚያ በላይ እንደሆነም እየተመለከትን እንገኛለን፡፡

ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር እና የኢትዮጵያ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ ያዘጋጁት የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ኤክስፖ (ETEX 2025) የዲጂታል ኢትዮጵያ ውጤታማ ጉዞ ማሳያ ከሆኑት አንዱ ነው። በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በተካሄደው ታላቅ የቴክኖሎጂ መድረክ በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርት በግብርና በኢንዱስትሪ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች፣ ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ተስፋ ሰጪ የፈጠራ ሥራዎች ለእይታ ቀርበዋል፡፡

በዲጂታል አሠራሮች የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የዲጂታል እውቀት በማኅበረሰቡ ውስጥ ከመዝራት ባሻገር የኢትዮጵያን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ገፅታዎች የሚያጎሉ የተለያዩ አሳታፊ ተግባራት እና የውይይት መድረኮችም ተካሂደዋል፡፡

“ኢቴክስ 2025” ኤክስፖ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃና በኢትዮጵያ ምን ዓይነት ሥራ እየተሠራ ነው የሚለውን ለማሳየት እንዲሁም በርካቶች ዘርፉ ምን ላይ እንዳለ እንዲገነዘቡ ትልቅ አቅም የፈጠረም ነው። ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዲጂታል መልክዓ ምድር ላይ ግንባር ቀደም ተዋናይ ለመሆን የያዘችውን አቋም የሚያንፀባርቅና ስለዲጂታል ኢትዮጵያ ጉዞ ምስክር የሚሆን ነው፡፡

ቴክኖሎጂ፣ ፈጠራና የሳይበር ደህንነት ብሔራዊ አጀንዳ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳያ ነው። የኢትዮጵያ የዲጂታል ለውጥ ጉዞ የስትራቴጂክ ራዕይና የማይናወጥ ቁርጠኝነት ምስክር ነው። ሀገሪቱ ጠንካራ፣ ደህንነቱ የተጠበቀና ሁሉን አቀፍ የሆነ ዲጂታል ምህዳር በመገንባት ረገድ እየተራመደችበት ያለውን መንገድ የሚያስመለክትም ጭምር ነው። በአጠቃላይ “ኢቴክስ 2025” ኤክስፖ ዲጂታል ኢትዮጵያን ለማረጋገጥ የተያዘው ግብ ለማሳካት ጫፍ ላይ መድረሱን አመላካች ነው፡፡

መንግሥት ዲጂታል ቴክኖሎጂ አማራጮችን አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ በትኩረት እየሠራ ነው። በተለይ ስታርት አፖችን መደገፍ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘቡ በፖሊሲ፣ የቴክኖሎጂ ማዕከላትን በማስፋፋት እንዲሁም ምቹ አሠራርን በማስተዋወቅ ረገድ የተለያዩ ሰፊ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።

ይሁንና ወጣቶች የፈጠራ ሃሳባቸውን ይበልጥ ወደ ተግባር የሚለውጡበት መደልድል በመፍጠር ረገድ ቀሪ ሥራዎች ስለመኖራቸው የሚካድ አይደለም። በአሁን ወቅት ይህም ውስንነትን ለመለወጥም ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

ሃሳብና ፋይናንስ ሲገጣጠሙ ውጤታማ መሆን ቀላል ይሆናል። መንግሥት በባንኮች በተለይም በልማት ባንክ በኩል በቴክኖሎጂ ላይ ለተመሠረቱ የፈጠራ ሃሳቦች ፈንድ የሚያቀርብበትን አሠራር ማመቻቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ለጀማሪ የቴክኖሎጂ ፈጠራ ባለሙያዎች ምርምርና የተለያዩ ሥራዎች፣ ከታክስ ሥርዓት፣ ከፋይናንስ አስተዳደርና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ የሚደረጉ ማበረታቻዎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። በቴክኖሎጂው መስክ ውጤታማ የሚሆኑ የፈጠራ ሃሳቦችን ለመደገፍ የስታርት አፖች የሚሆን ፋይናንስ የሚሰባሰብበት ብሔራዊ ፈንድ ለማቋቋም የተጀመሩ ጥረቶችም ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው፡፡

በተለይ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ሁለንተናዊ ፋይዳና አቅም ጠንቅቆ የሚረዳና የሚጠቀም ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የግድ ነው። ሀገራዊ ስትራቴጂ የዲጂታል መሠረቶችን ከማልማት አንጻር የተሳካ ጉዞ ላይ ቢሆንም የለሙትን የዲጂታል መሠረቶች በመጠቀም አዳዲስ እሴቶችን በመፍጠር ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አንጻር ይበልጥ መሥራት ተገቢ ነው፡፡

ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው። በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።

ታምራት ተስፋዬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You