ሩሲያ እና ዩክሬን የተኩስ አቁም ንግግር እንደሚጀምሩ ትራምፕ ተናገሩ

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ንግግር እንደሚጀምሩ ተናግረዋል። ትራምፕ ይህን ያሉት የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በሚያበቃበት ሁኔታ ላይ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ከሁለት ሰዓታት በላይ የዘለቀ የስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።

ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በመካከለኛው ምስራቅ በጉብኝት ላይ ሳሉ፣ እርሳቸው እና ፑቲን በአካል እስኪገናኙ ድረስ በሩሲያ-ዩክሬን ንግግር ላይ ከፍተኛ መሻሻል የማይታሰብ መሆኑንና ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በተቻለ ፍጥነት መገናኘት እንደሚፈልጉ መናገራቸው ይታወሳል።

ሁለቱም መሪዎች የስልክ ውይይታቸው ገንቢና መልካም እንደሆነ ገልጸዋል። ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፑቲን ጋር ያደረጉት ውይይት እጅግ መልካም መሆኑን ገልፀው፣ ሞስኮና ኪዬቭ ተኩስ አቁም ለማድረግ አፋጣኝ ድርድር እንደሚጀምሩ ተናግረዋል። የተኩስ አቁም ለማድረግ በሁለቱ ወገኖች በኩል የሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ከስምምነት ሊደረስባቸው እንደሚገባም አሳውቀዋል።

‹‹ሩሲያ እና ዩክሬን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ለማድረግ ውይይት ይጀምራሉ። ከተኩስ አቁም ስምምነት በላይ ጦርነቱን ለማስቆም ንግግር ያደርጋሉ። ይህን ለማድረግ በሚቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች ዙሪያ ሁለቱ ሀገራት ውይይት ያደርጋሉ። ምክንያቱም ከሌላው በላይ ስለጉዳይ የሚያውቁት እነሱ ናቸው›› ብለዋል። ፕሬዚዳንት ፑቲን በበኩላቸው ሀገራቸው ለጦርነቱ ሰላማዊ አማራጭን እንደምትደግፍ ተናግረዋል። ከዩክሬን ጋር ለመሥራት እና ወደፊትም የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ዝግጁ መሆናቸውንም ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ከዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ እና ከአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ጋር ተወያይተዋል። ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸው ከሩሲያ ጋር ለመደራደር ዝግጁ መሆኗን ተናግረዋል። ሙሉ የሆነና እና ቅድመ ሁኔታ የሌለው የተኩስ አቁም እንዲደረግም ጥሪ አቅርበዋል። ‹‹ተወካዮቻችን ሃቀኛ የድርድር ውሳኔዎችን ለመወሰን ዝግጁ ናቸው። አስፈላጊው ነገር ሩሲያ ትርጉም ላለው ድርድር ዝግጁ እንድትሆን ማድረግ ነው›› ብለዋል።

አሜሪካ ለጦርነቱ መፍትሄ ለመፈለግ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አስተዋፅዖ ማበርከቷን እንድትቀጥልም ጠይቀዋል። አሜሪካ ጦርነቱን ለማስቆም በሚደረጉ ንግግሮች ውስጥ ተሳታፊ ሆና መቀጠሏ ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል። የአሜሪካ ከዚህ ሚናዋ ወደ ኋላ ማለት የሚጠቅመው ፑቲንን ብቻ እንደሆነም ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪም በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀቦች እንዲጣሉባት ተማፅነዋል።

የዩክሬን አጋር የሆኑ የአውሮፓ መሪዎች ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፑቲን ጋር በመወያየታቸው አመስግነዋቸዋል። የአውሮፓ ኅበረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሊየን ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር ስለነበራቸው ውይይት እርሳቸውን ጨምሮ ለዩክሬን፣ ለጀርመን፣ ለፈረንሳይ፣ ለኢጣሊያና ለፊንላንድ መሪዎች ገለፃ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል። ‹‹ፕሬዚዳንት ትራምፕ በዩክሬን ሰላም ለማስፈን ለሚያደርጉት ከፍተኛ ጥረት አመሰግናለሁ። አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ውስጥ ተሳታፊ ሆና መቀጠሏ አስፈላጊ ነው። በዩክሬን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ቮሎድሚር ዘለንስኪን መደገፋችንን እንቀጥላለን›› ብለዋል።

የጀርመን መራኄ መንግሥት ፍሬድሪኽ ሜትስ የአውሮፓ አህጉር በሩሲያ ላይ ጫና ለማሳደር ተጨማሪ ማዕቀቦችን እንደሚጥል አሳውቀዋል። መራኄ መንግሥቱ ከትራምፕ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ‹‹አውሮፓና አሜሪካ በዚህ ጉዳይ ላይ በኅብረት ቆመዋል። የዩክሬንን የተኩስ አቁም ጥረት እንደግፋለን›› ብለዋል።

የፊንላንዱ ፕሬዚዳንት አሌክሳንደር ስተብ በበኩላቸው፣ የአውሮፓ መሪዎች ከትራምፕ ጋር ያደረጉት የአንድ ሰዓት ቆይታ ‹‹ገንቢ›› እንደነበር ገልፀው፣ በመካሄድ ላይ ስላሉት ድርድሮች፣ ስለተኩስ አቁም እና ዘላቂ ሰላም መወያየታቸውን አመልክተዋል። በአውሮፓና በአሜሪካ መካከል ጥብቅ የሆነ ትብብርን ማስቀጠል አስፈላጊ እንደሆነና ፊንላንድ የዩክሬንን ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና የግዛት አንድነትን መደገፏን እንደምትቀጥል አብራርተዋል።

ሩሲያና ዩክሬን የሚያደርጉትን ድርድር ቫቲካን እንደምታስተናግድ ተገልጿል። የኢጣሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የአሜሪካና የአውሮፓ መሪዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሊዮ ፲፬ኛ ቫቲካን የሩሲያ-ዩክሬን ድርድርን ለማስተናገድ ያላቸውን ዝግጁነት እንዳደነቁ ተናግረዋል። ሩሲያና ዩክሬን ጦርነቱን ለማቆምና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሚያደርጉ ንግግሮች እንዲጀመሩ የሚያስችሉ ስራዎች መከናወን እንደጀመሩ እንዲሁም ኢጣሊያ ንግግሮቹን ለማመቻቸት ኃላፊነቷን እንደምትወጣ የጠቅላይ ሚኒስትሯ ቢሮ መግለጫ አመልክቷል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ አድራሻው፣ ‹‹በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት የምትወከለው ቫቲካን ድርድሮችን ለማስተናገድ ፍላጎት እንዳላት ገልፃለች። ሂደቱ ይጀመር›› ብለው ጽፈዋል። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሳነ ሊቃነ ጳጳሳት ስለሰላም መስፈን አስፈላጊነት ጥሪ ማድረጋቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ቫቲካን ጦርነቶች እንዲቆሙ በዲፕሎማሲ ስራ በቀጥታ ስትሳተፍ ማየት ግን ብዙም የተለመደ አይደለም።

ትራምፕ ከፑቲን ጋር ያደረጉት የሥልክ ንግግር አሜሪካ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እልባት እንዲያገኝ ለማድረግ ሚናዋን እንደምትቀጥል ያሳያል ተብሏል። ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩ ጥረቶች ይህ ነው የሚባል የረባ ለውጥ አለማምጣታቸው የአሜሪካ ባለስልጣናትን ሳያበሳጭ እንዳልቀረና ጦርነቱን ለማስቆም ሲያደርጉት የነበረውን ተሳትፎም ሊያቋርጡ ይችላሉ ተብሎ ሲነገር እንደነበር ታውቋል።

አንተነህ ቸሬ

አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You