
አዲስ አበባ፡- ፋይዳ ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚ ዘርፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትልቅ እድል መፍጠሩን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዲጂታል ማንነት ላይ ትኩረቱን ያደረገው አይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ሲጀመር ባደረጉት መክፈቻ ንግግር እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ዘመናዊ፣ አካታች እና መሠረታዊ የዲጂታል ማንነት መለያ ሥርዓት ዘርግታለች፡፡ ይህም ዜጎች በዲጂታል ኢኮኖሚ ላይ ያላቸውን ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ ዲጂታል ማንነትን ማረጋገጥ አስፈላጊ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ፋይዳ የዲጂታል ማንነት ሥርዓት ካርድ ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ግላዊ መረጃዎች ምሥጢራዊነት በመጠበቅና አስፈላጊ የሆነውን ብቻ በማጋራት ማንነትን የሚያረጋግጥ ልዩ መለያ ቁጥር ነው፡፡ በፋይናንስ፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ቴሌኮምን ጨምሮ ከሌሎችም የሕዝብ አገልግሎቶች ጋር በማስተሳሰር ዜጎች ለሚፈልጉት አገልግሎት መደላድል ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ራዕይ እየተመራን እጅግ አስፈላጊ ውሳኔ ወስነናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ዘመናዊ፣ አካታች ዲጂታል የማንነት ሥርዓት መገንባትና ለእያንዳንዱ ነዋሪ ተደራሽ ማድረግ ነው፡፡ ፋይዳ አማራጭ ሳይሆን ሰዎችን ከአገልግሎቶች፣ ከማኅበረሰቦች፣ ከተቋማትና ከመንግሥታት ጋር የሚያገናኝ አስፈላጊ መሠረተ ልማት መሆኑንም አስረድተዋል።
ፋይዳ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን የሆነ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ትልቅ አበርክቶ እንዳለው ጠቁመው፤ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና ውስጥ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወትም ተናግረዋል፡፡
የዲጂታል ማንነት መለያ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዓላማው በኅብረት በመሰለፍ የአፍሪካን እምቅ አቅም ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኮንፈረንስ ማዕከልነት ባሻገር የራሷ ማንነት ያላት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እጅግ ውብ በሆኑ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች እንዲሁም ከመልክዓ ምድሯ ልምድ መውሰድ የሚቻል ስለመሆኑም አንስተዋል።
ተሳታፊዎች ወደመጡበት አካባቢ ሲመለሱም ሁሉም ሰው አስተማማኝ የዲጂታል ማንነት መለያ እንዲኖረው በቁርጠኝነት ሊሠሩ እንደሚገባም አመልክተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ ኢትዮጵያ ከተበታተነው የመታወቂያ ሥርዓት አልፋ፣ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ወደተጀመረው አስተማማኝ፣ ሁሉንም ያካተተ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ መሸጋገሯን አጽንዖት ሰጥተዋል። ለፋይዳ እስካሁን ከ15 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተመዝግበዋል። 90 ሚሊዮን ሰዎችን ለመመዝገብ ታቅዶ እየተሠራ ነው። ፋይዳ ሁሉም ዜጎች – በተለይ ሴቶች፣ ወጣቶች እና የተፈናቀሉ ማኅበረሰቦች አስፈላጊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
እንደ ፋይናንስ፣ ጤና እና ትምህርት ባሉ ቁልፍ ዘርፎች የተቀናጀው ፋይዳ፣ 9 ነጥብ 6 ትሪሊዮን ብር በዲጂታል ግብይት እንዲዘዋወር እያገዘ መሆኑንም ገልጸዋል።
ዲጂታል ማንነት ላይ ያተኮረው አይዲ ፎር አፍሪካ ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ትናንት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።የአይዲ ፎር አፍሪካ ሊቀመንበር ጆሴፍ አቲክ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማረጋገጥ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ ነው። የዛሬው ቀን የአፍሪካውያን የዲጂታል ማንነትን ለማረጋገጥ ጉዞ የምንጀምርበት አዲስ ምዕራፍ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
በጉባኤው ለልማት መታወቂያ፣ አይዲ 4 (ID4) እንቅስቃሴን በተመለከት ሁሉም የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲወጣ የምናስገነዝብበት ነው ብለዋል።
የአፍሪካ መሪዎች የዓለምን ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግንባታ ትኩረት ሰጥተው ለመሥራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውንም አመልክተው፤ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ሽግግርን እውን ለማድረግ ዲጂታል ማንነትን ማረጋገጥ ቅድሚያ የሚሰጠው ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ዲጂታል ማንነት ላይ በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም የአፍሪካን ሁለንተናዊ ልማትና የዜጎች ኑሮ ለማሻሻል ወሳኝ ሚና እንዳለው ነው ያስታወቁት።
ይህ መድረክ የወደፊቷን ዲጂታል አፍሪካ ለማረጋገጥ ሁሉም አፍሪካዊ ማንነቱን ለማረጋገጥ ቁርጠኝነታችንን የምናሳይበት ነው ብለዋል።
ID4Africa ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ ልማትን፣ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን እና ሰብአዊ ጥረቶችን የሚያበረታቱ ጠንካራ እና ኃላፊነት የሚሰማቸው የማንነት ዐውዶችን በመገንባት፣ የአፍሪካ ሀገራትን ለመደገፍ ቁርጠኛ የሆነ የፓን አፍሪካ እንቅስቃሴ ነው።
ለ11ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ እየተካሄደ በሚገኘው ጉባኤ ላይ ከ105 ሀገራት የተውጣጡ ከሁለት ሺህ 200 በላይ ተሳታፊዎች እየተካፈሉ መሆናቸው ተመላክቷል።
ፋንታነሽ ክንዴ
አዲስ ዘመን ረቡዕ ግንቦት 13 ቀን 2017 ዓ.ም