
ዜና ትንታኔ
ኢትዮጵያ በእንስሳት ሀብት ከዓለም አምስተኛ፣ ከአፍሪካ ቀዳሚ መሆኗን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ይሁንና ሀገሪቱ የእንስሳትን ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ በተለይ ወተትን ለዜጎቿ በብዛትና በጥራት ተደራሽ ማድረግ አልሆነላትም።
ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት ዓመታዊ የዜጎች የነፍስ ወከፍ የወተት ተጠቃሚነት ልኬት 200 ሊትር ሊሆን እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ለአብነት በከፍተኛ ተጠቃሚነት የምትታወቀው በፊንላድ፣ የዜጎች ዓመታዊ የነፍስ ወከፍ ወተት ተጠቃሚነት ልኬት 430 ሊትር ሲሆን ኬንያ 115 ነው፡፡የዩጋንዳ 65 ሊትር ሲሆን የኢትዮጵያ ከ35 ሊትር የሚበልጥ አይደለም፡፡
በኢትዮጵያ ከመሰል የተደራሽነት ችግር ባለፈ ከምርት እስከ ገበያ ባለው ሂደት የወተት ጥራትና ደህንነትን ከማስጠበቅ ጋር ተያይዞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግልፅ ድክመቶች እየተስተዋሉ ችግሩም እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ስለመምጣቱ ይነገራል፡፡
የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የእንስሳት ነክ በሽታዎች ምርምር ዲቪዥን ኃላፊና የጸረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ከፍተኛ ተመራማሪ ዶክተር ይመር ሙሉጌታ፣ባሳለፍነው ግንቦት 04 በተለይ ባልታሸጉ የወተት ምርቶች ላይ ለአደገኛ በሽታዎች የሚያጋልጡ የባክቴሪያ ዓይነቶች መገኘታቸውን መግለፃቸው የሚታወስ ነው፡፡
ለመሆኑ ‹‹ወተት እንዴት ይበከላል?ጉዳትና መፍትሄውስ? የሚል ጥያቄ በማንሳት ለዘርፉ ባለሙያዎች ጥያቄ አቅርበናል፡፡
በፌዴራል ደረጃ በአዋጅ 1112/2011 በተሰጠው ስልጣን መሠረት ኅብረተሰቡ የሚጠቀማቸውን ምግብና መድኃኒቶች ጥራት፣ ደህንነት የሚከታተልና የሚያስጠብቀው የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ነው፡፡ የተቋሙ የእንስሳት ተዋእፆና አልሚ ምግብ አምራቾች ኢንስፔክሽን ኃላፊ አቶ መሐመድ ሁሴን፣ ማንኛውም ምግብ አቅርቦቱ ጥራትና ደህንነቱን በጠበቀ መልኩ ገበያ መቅረብ ተጠቃሚ ጋር መድረስ አለበት፡፡ ወተትን የመሳሰሉ በተለይ በቀላሉ ለብክለት የሚጋለጡ ምርቶች ደግሞ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይፈልጋሉ››ይላሉ፡፡
እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ፣ ኢትዮጵያ ከእንስሳት ሀብት መሆን ባለበት ልክ እየተጠቀመች አይደለም፡፡ሀገሪቱ በተለይ ወተት ልማት ላይ ይበልጥ መሥራት፣ ከእዚህ ጎን ለጎንም ለገበያ ሰንሰለቱ ከእርሻ እስከ ጉርሻ ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሀገሪቱ የወተት ልማትና ገበያ ሰንሰለት በአግባቡ እየተመራ አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ከሚመረተው ወተት ሕጋዊ በሆነ መልኩ ጥራትና ደህንነቱን ጠብቆ ለገበያ የሚቀርበው ከ5 በመቶ አይበልጥም፡፡ይህም በተለይ የምርት ጥራትና ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት የቁጥጥር ሥራን እጅግ ከባድ አድርጎታል፡፡
‹‹እንደ ሀገር የወተት ምርት የሚሰበሰብ፣ የሚጓጓዝና የሚሰራጭበት መንገድ ለብክለት የተጋለጠ ነው›› የሚሉት አቶ መሐመድ፤ ኢኮኖሚያዊ ጥቅምን ማእከል በማድረግ የሚፈፀሙ ሕገ ወጥ ተግባራትም የወተት ጥራትን ደህንነቱን አደጋ ላይ የጣሉ መሆናቸውን ያስረዳሉ፡፡
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ፤ ጥራትና ደህንነቱን አስጠብቀው የሚጓዙ እንዳሉ ሁሉ የወተትን ሙሉ በሙሉ ካልሆነም በ50 በመቶ ወሳኝ ንጥረ ነገሮች በሚነጥቅ መልኩ እስከ 60 በመቶ ውሃ ይጨመራል፡፡ከውሃም ባሻገር የወተቱን እድሜ ለማስረዘምና የቀለም ምጣኔውን ለማስተካከል የሚበረዙና የሚቀላቀሉ አደገኛ ኬሚካሎችም አሉ፡፡ እነዚህ ግብአቶች ለሰው ልጅ ጤና እጅጉን አደገኛ ከፍ ሲልም ለሞት የሚዳርጉ ናቸው፡፡
ወተት እንደታለበ የቅዝቃዜ ሰንሰለቱን ጠብቆ ተጠቃሚው ዘንድ መድረስ አለበት፡፡ ይሁንና በሀገሪቱ ከእዚህ በተቃርኖ ጥሬ ወተትን ከ6 እስከ 12 ሰአት ረጅም ርቀት ማጓጓዝ፣ ከተደራጁት ማህበራት ውጪ ምርትን መሰብሰብ፣ ክትባት የወሰዱ ላሞች የእረፍት ጊዜያቸውን ሳይጨርሱ ማለብ ይስተዋላል፡፡ይህም ለአፍላቶክሲን መጋለጥን ጨምሮ ከባድ የጤና ጉዳትን ያስከትላል፡፡
የወተት ምርት ጥራትና ደህንነት በማስጠበቅ ሂደት ከአምራቾች ባሻገር አቀነባባሪዎች ዘንድም ግልፅ ውስንነት ይስተዋላል፡፡ በተለይም ምርት ተቀብለው የሚያከማቹበት አሠራር፣ የሚጠቀማቸው ፓኬጂንግ (የምርት ማሸጊያዎች) ከደረጃ (ስታንዳርድ) አንፃር እና የውስጥ ጥራትና ደህንነት በማረጋገጥ ረገድ ግልፅ ውስንነት ይታይባቸዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከእርባታ እስከ ገበታ የወተት ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ ከቅድመ ፈቃድ አሰጣጥ እስከ ገበያ ቅኝት የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑንና በተለይ በተለያዩ የፍተሻ መመዘኛ ውስንነት የታየባቸው 8 ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ሥራ እንዲያቆሙና እንዲያስተካክሉ ማድረጉን የሚጠቁሙት አቶ መሐመድ፤ ከወተት ገበያው አድማስና ሕገ ወጥ ጉዞ ጋር ተያይዞ የቁጥጥር ሥራው በአንድ አካል ብቻ የማይሠራና ሁለንተናዊ ጥምረትን የሚጠይቅ ስለመሆኑ ነው ያስገነዘቡት፡፡
መሰል ፈተናዎች የተደቀኑበትን የሀገሪቱ የወተት ልማት እንቅስቃሴ ለማጎልበት ከመንግሥት ባሻገር የተለያዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ይሳተፋሉ። ከተዋናዮቹ መካከልም በኔዘርላንድስ መንግሥት የሚደገፈው ኤስኤንቪ (SNV) የተሰኘ ድርጅት አንዱ ነው፡፡ አቶ አስናቀ ጌታሁንም በድርጅቱ የብሪጅ ፕላስ ፕሮጀክት የምሥራቅ ሸዋ ሚሊክ ሼድ አማካሪ ናቸው።
የሀገሪቱ የወተት ጥራትና ደህንነት ችግር ከእርባታ እስከ ገበታ የሚዘልቅ መሆኑን የሚጠቁሙት አቶ አስናቀ፤ ‹‹የሀገሪቱ የወተት ጥራትና ደህንነት ዋነኛ ፈተና ሕገ ወጥ የወተት ምርት አጓጓዥ ነው፤ የምርት ስርጭት የሕዝብ ትራንስፖርቶችን ሳይቀር የሚጠቀም፣ ከፕላስቲክ የተሰሩ መያዣዎችን (ጄሪካኖች) የሚጓጓዝ፣ የቤት ለቤት አቅርቦቱም በአብዛኛው በፕላስቲክ ጠርሙስ ጋር የተጣበቀ ነው›› ይላሉ፡፡ የወተት መበረዝና መከለስ ፣የወተት ምርት ገበያውን በአግባቡ ለመቆጣጠር የሚያስችል ጠንካራ የሕግ ክፍተት፣የቤት ለቤትን ጨምሮ ሕገ ወጥ የወተት ንግድ ተጨማሪ ፈተናዎች መሆናቸውንም ያብራራሉ።
በጄሪካን የሚቀርብ ወተት በተለይም በአግባቡ ለማፅዳት አስቸጋሪ በመሆኑ ለከፍተኛ ብክለት የተጋለጠ ስለመሆኑ የሚያስገነዝቡት አቶ አስናቀ፤ ይህን መሰል የአቅርቦት ሂደት ከሚያስከትለው ከባድ ችግር አንፃር ሊታረም የሚገባው ስለመሆኑም አፅእኖት ይሠጡታል፡፡የድርጅቱን መሰል ክፍተቶች ለመድፈን አቅም ግንባታን ጨምሮ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ መሆኑን ጠቁመው፤ ይሁንና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚመለከታቸው አካላት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩ እንደሚገባም ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
የወተት ጥራትና ደህንነት ከእርባታ እስከ ገበታ ለማረጋገጥ አስተያየት ሰጪዎቹ መፍትሄ የሚሉትን ሲጠቁሙም፤ ምርት ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ በአግባቡ ማወቅና በመረጃ አስደግፎ መያዝ፣በተለይም ወተትን በጀሪካን ጨምሮ ከቦታ ቦታ ያለበቂ ጥንቃቄ እያንቀሳቀሱ በየቤቱ የሚያከፋፍሉ አካላትን ማስቆም፣ የወተት ጥራትና ደህንነቱ ሲጓደልና ለብክለት ሲጋለጥ ስለሚያስከትለው ከባድ አደጋ፣አምራች፣አከፋፋዩም ሆነ ተጠቃሚው በቂ መረጃ እንዲኖረው ማድረግ የሚሉትን ከመፍትሔዎቹ ከቀዳሚ ተርታ አስቀምጠዋል፡፡
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 12 ቀን 2017 ዓ.ም