ፕሬዚዳንቱ የዩክሬናውያንን ‘ደም መፍሰስ’ ለማስቆም ለፑቲን እንደሚደውሉ ገለጹ

ዶናልድ ትራምፕ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ለማስቆም ሰኞ ዕለት ከሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ እንደሚነጋገሩ ገልጸው፤ ርምጃው “የሚፈስሰውን ደም” ለማስቆም ያለመ ነው ብለዋል። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ ከፑቲን ጋር ከተነጋገሩ በኋላ የዩክሬኑን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን እና አንዳንድ የኔቶ ሀገራት መሪዎችን እንደሚያነጋግሩ አስታውቀዋል።

ምንም እንኳን የእስረኞች ልውውጥ ላይ ከስምምነት ቢደረስም ሩሲያ እና ዩክሬን ከሦስት ዓመታት በኋላ የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ንግግራቸውን አርብ ዕለት በኢስታንቡል አካሂደው ያለውጤት ተበትኗል። ፑቲን ኢስታምቡል ከተገኙ በቱርክ በሚደረገው ውይይት ላይ እንደሚሳተፉ ትራምፕ ቢገልጹም የሩሲያው ፕሬዚዳንት ግን ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆኑም።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ጦርነቱን ለማስቆም ዕድል ሊኖር የሚችለው እርሳቸው እና ፑቲን ፊት ለፊት ሲነጋገሩ ብቻ ነው ሲሉ ከጠቆሙ በኋላ ነው። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ሰኞ ዕለት በፑቲን እና በትራምፕ መካከል ለሚደረገው የስልክ ንግግር ዝግጅት መደረጉን ለሩሲያ የዜና ወኪሎች አረጋግጠዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከዚህ ቀደም በጉዳዩ ላይ በስልክ ተነጋግረዋል። ፔስኮቭ ለታስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት “ውይይቱ በጥሩ መስመር ላይ ነው።” ትራምፕ በትሩዝ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ውጤታማ ቀን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። የተኩስ አቁም ይኖራል። እናም ይህ በጭራሽ መከሰት ያልነበረበት በጣም ኃይለኛ ጦርነት ያቆማል።”

የአውሮፓ መሪዎች ሩሲያ ለ30 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንድትደርስ እየጠየቁ ነው። የዩናይትድ ስቴትስ እና የሩስያ መሪዎች የተኩስ አቁም ስምምነትን እንዲሁም በመካከላቸው ሊኖር ስለሚችለው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ሞስኮ ትራምፕ በሚፈልጉት ፍጥነት ባትንቀሳቀስም የአሜሪካን የሽምግልና ጥረቶች በደስታ መቀበሏን ቅዳሜ ዕለት በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ እና በሩሲያ አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ መካከል በነበረው የስልክ ውይይት አስታውቃለች። በኢስታንቡል የተደረገውን ውይይት ተከትሎ ዩክሬን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሙሉ የተኩስ አቁም እንዲደረስ ጥሪዋን በድጋሚ አቅርባለች።

እንደ አንድ የዩክሬን ባለሥልጣን ገለጻ ክሬምሊን የተኩስ አቁም እንዲደረስ ኪየቭ ወታደሮቿን “ከግዛቷ ሰፊ ክፍል እንድታስወጣ ማስገደድን ጨምሮ” አዲስ እና ተቀባይነት የሌላቸውን ጥያቄዎችን አቅርባለች ብለዋል። የሩሲያው የልዑካን ቡድን መሪ እና የፑቲን ረዳት የሆኑት ቭላድሚር ሜዲንስኪ በንግግሮቹ ደስተኛ መሆናቸውን እና ግንኙነታቸውን ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላን በሱሚ ግዛት የመንገደኞች አውቶቡስን በመምታት ዘጠኝ ሰዎችን ገድለዋል። ይህንን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ዜሌንስኪ በሞስኮ ላይ ጥብቅ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል። የአውቶብሱን ጥቃት “በሰላማዊ ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ ግድያ ነው” ብለዋል። ሩሲያ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ባትሰጥም የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሱሚ ግዛት “ወታደራዊ ይዞታዎች” መመታታቸውን ዘግበዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You