
ለሕዝብ ጥቅም ቆመናል በሚል ሽፋን ለራሳቸው ጥቅም የቆሙ ቁማርተኞች የበዙበት ዘመን ላይ እንገኛለን:: ሕዝብ ሳይሾማቸው እራሳቸውን ያነገሱ ነጻ አውጪ ነን ባዮች በየስርቻው ሲፈለፈሉ ይታያሉ:: የእገሌ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር፤ የእገሌ ብሔር ተሟጋች፤ የእገሌ ሕዝብ የሕልውና ጠበቃ ወዘተ የሚሉ ስሞችን በመደርደር በሕዝብ ስም የግላቸውን ጥቅም የሚያሳድዱ ጉደኞች እዚህም እዚያም ይገኛሉ::
እነዚህ ቁማርተኞች ሌት ተቀን የሕዝብን ስም በመጥራት፤ በመማል እና በመገዘት የራሳቸውን ንዋይ የሚያሳድዱ ጥቅመኞች ናቸው:: ሕዝብ ጫንቃ ላይ እንደመዥገር ተጣብቀው ኃብቱን፤ ሕይወቱን፤ ወጣትነቱንና እና ወደፊት ተስፋውን እየነጠቁት ይገኛሉ::
እነዚህ ኃይላት ጥቅማቸው እና የስልጣን ጥማቸውን የሚያስጠብቅ ወገን እስካገኙ ድረስ ለሀገር ሉአላዊነት እና ለሕዝብ ጥቅም ደንታ የላቸውም:: እነዚህ አጥፊ ቡድኖች ከጥንስሳቸው ጀምሮ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ቆርጠው የተነሱ በመሆናቸው ከውጭ ወራሪዎች ጋር በማበር የሀገሪቱን ሉአላዊነት አሳልፈው ለመስጠት ሌት ተቀን የሚሠሩ ናቸው::
ቡድኖቹ ግትር ፖለቲካን የሚከተልና ከምስረታው ጀምሮም ውይይትን እንደሰላም አማራጭ የማይመለከቱ ናቸው:: ሁሉንም ነገር በኃይል የመፍታት ልምድ ያላቸው ከመሆኑም በሻገር ከውይይት እና ምክክር ይልቅ ቃታ መሳብ የሚቀናቸው ናቸው::
እነዚህ ቡድኖች በየጊዜው እየጫሩ በሚለኩሱት እሳት በርካታ ወጣቶች በግፍ አልቀዋል፤ አካለ ጎዶሎ ሆነዋል፤ ለስደት ተዳርገዋል:: የእነዚህ ቡድኖች ፍላጎት የሚፈጸመው በግጭት እና በጦርነት ውስጥ በመሆኑ የሰላምን ወሬ መስማት አይፈልጉም:: ያለ ጦርነት ሕልውና ስለሌላቸው ለሰላም የተዘረጉ እጆችንም ሲነክሱ ቆይቷል:: ቡድኖቹ የስልጣን ጥማቸውን ከማርካት፤ የዘረፋ ሰንሰለታቸውን ከማጠናከር፤ የአፈና መዋቅራቸውን ከማስፋፋት ውጪ የሕዝብ ስቃይ እና መከራ የሚሰማቸው አይደሉም::
ይልቁንም የእነሱ የጥፋት አጀንዳ የሚቀጥለው ግጭት እና ሁከት ሲበራከት እና አለመረጋጋት ሲሰፍን ነው:: ሞት፤ ስደት፤ መፈናቀል፤ መራብ፤ መታረዝ፤ የመሳሰሉት ቀውሶች የእነሱ መደበቂያ ዋሻዎች ናቸው:: የእነሱ ምስ የሚሞላው ብዙዎች ሲያልቁ እና ሲረግፉ ነው:: ለእነሱ ያረጀ እና ያፈጀ ፖለቲካ ሲባል ብዙዎች ሲማገዱ ነው::
እነዚህ ሰዎች ሚሊዮኖችን ያስጨርሳሉ እንጂ እነሱ አይሞቱም:: ሶስት አራት ጦርነቶች ውስጥ ቢኖሩም እነሱ በእነዚህ ጦርነቶች ውስጥ ያብባሉ እንጂ አይሞቱም:: ፈሪ ዘላላም ይኖራል እንዲል ምሳሌው እነሱ ሚሊዮኖችን ያስጨርሳሉ እንጂ አንዳችም ነገር አያጋጥማቸውም::
ይልቁንም ጦርነቶች ማብቂያ ባገኙ ቁጥር ለሌላ ጦርነት መዘጋጀት አንዱ መገለጫቸው ነው:: የሚሎዮኖች ዕልቂት ለእነሱ ቁጥር ብቻ ነው:: እራሳቸው በሚቀሰቅሱት ጦርነት የሚረግፈውን ወጣት በአሃዝ በማስደገፍ መተንተን እና የዕልቂት ብዛትንም እንደ ጀግንነት ጥግ የሚወስዱ በላኤ ሰቦች ናቸው::
ሕዝብ ሳይሾማቸው ለሕዝብ ቆመናል የሚሉ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ችግርን በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ነውጠኛ ደጋፊዎችን የማሰባሰብ ሴራ ውስጥ በመግባትም በሕዝብ ውስጥ ለመሸሸግ ይሞክራሉ:: እነዚሁ ኃይላት ኃላፊነት የጎደላቸው ስለሆኑም ግጭትና መገዳደልን ጨምሮ የሀገርን ተስፋ የሚያጨልሙ ድርጊቶች እንዲበራከቱ ያደርጋሉ:: ለሀገርና ለሕዝብ ከማሰብ ይልቅ ከመጠን ያለፈ ራስ ወዳድነት ስለተጠናወታቸውም ቆመንለታል ያሉትን ሕዝብ ሳይቀር በቁሙ ሲዘርፉ ይታያሉ::
እነዚህ የግጭት ነጋዴዎች ከመተማመን ይልቅ ጥርጣሬ፣ ከትብብር ይልቅ መገፋፋት፣ በግልጽ ከመነጋገር ይልቅ መተማማት ስለሚቀናቸው የማኅበራዊ ሚዲያዎች እና ሌሎች የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ሕዝቡን አላስፈላጊ ወደ ሆነ ጥርጣሬ ውስጥ በመክተት አንዴ በብሔር ሌላ ጊዜ በሃይማኖት እየከፋፈሉ የዘመናት አብሮነቱን ሊነጥቁት ሲሯሯጡ ይታያሉ:: በእነዚህ ስግብግቦች የተነሳ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከባድ ጊዜን ለማሳለፍ ተገዶ ቆይቷል::
እነዚሁ ፖለቲከኞች ነን ባዮች የዚህን ኩሩ ሕዝብ የዘመናት ዕሴቶች ለመናድ የሚሯሯጡ ናቸው:: ልዩነቶችን ጌጡ አድርጎ የኖረውን ሕዝብ እርስ በራሱ እንዳይተማመን እና እንዲጋጭ የሚያደርጉ ትርክቶችን በመፍጠር በሀገሪቱ ሁከትና ብጥብጥ እንዲነግስ ያለመታከት በመሥራት ላይ ይገኛሉ:: ብዙዎቹ ፖለቲከኞች የራሳቸው አንድም ሃሳብ ሳይዙ በተላላኪነትና በባንዳነት ተፈርጀው ለግል ጥቅማቸው ሲሉ አንዱን ብሔር በሌላው ላይ በማስነሳት ሀገርን ለማፍረስ ቆርጠው የተነሱ ናቸው::
በዚህ ድርጊታቸውም የዜጎችን በሰላም የመኖር መብት አደጋ ላይ የጣሉና የሀገርን ሰላምና ደህንነት የሚያውኩ ሙከራዎችም ተከስተዋል:: በሕዝብ ሕይወት ላይ ቁማር መጫወት እና አለፍ ሲልም ግፍ እና በደል ከፈጸመ የውጪ ኃይል ጋር ቁርኝት በመፍጠር ተጋላቢ ፈረስ ሆኖ ሀገርን ለማወክ መሞከር የብዙዎቹ ነፍጥ አንጋቢ ቡድኖች መገለጫ ባሕሪ ነው:: ሰዎችን አፍኖ ገንዘብ መጠየቅ እና ወርቅን በመሳሰሉ ሕገወጥ የኮንትሮባንድ ሥራ ውስጥ መሳተፍ መለያ ባሕርያቸው ነው::
ሰሞኑን ለፋና ብሮድካስቲንግ ቃለመጠይቅ የሰጡት የቀድሞ የትግራይ ግዜያዊ አስተዳር ፕሬዚዳንት ጌታቸው ረዳ ያስተላለፉት መልዕክትም ከላይ ያነሳነውን ሃቅ የሚያጠናክር ነው:: በክልሉ የሚገኙኘ ጥቂት ባለስልጣናት የሕዝቡን ጥቅም እርግፍ አድርገው በመተው የራሳቸውን ሃብት በማከማቸት ላይ ይገኛሉ:: በኮንትሮባንድ የወርቅ ንግድ ውስጥ በመሰማራት፤ ሰዎችን አፍኖ ገንዘብ በመጠየቅ እና በሕገወጥ ሰዎች ዝውውር እንዲሁም በመልሶ ማቋቋም ስም የሚመደበውን በጀት ወደራሳቸው ኪስ በማስገባት በትግራይ ሕዝብ ላይ ይቅር የማይባል በደል ፈጽመዋል::
በመንግሥት እና በሕወሓት በኩል የፕሪቶርያ ስምምነት ቢፈረምም ስምምነቱ ገና ከጅምሩ ወደ መሬት እንዲወርድ በማይፈልጉ ግለሰቦች አማካኝነት ስምምነቱ እክል ገጥሞታል:: በፕሪቶርያው ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ አንድ መከላከያ ሰራዊት እንደሚኖር ከስምምነት የተደረሰ ቢሆንም በሕወሓት ወገን ግን አሁንም በበርካታ ሺ የሚቆጠር ታጣቂ ትጥቅ አልፈታም:: ሰራዊት አልተበተነም::
እነዚህ ቡድኖች ሰብአዊነት እና ፖለቲካን በመቀላቀል የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ አካባቢያቸው እንዳይመሰሉ ተግዳሮት ሲፈጥሩ ተስተውለዋል:: ከዚሁ ጎን ለጎንም በጦርነቱ የተሳተፉ ወጣቶች በመልሶ ማቋቋም ወደ ሰላማዊ ሕይወታቸው እንዶመለሱ የሚደረገውንም ጥረት ሲያስተጓጉሉ ታይተዋል:: ግዜያዊ አስተዳደሩ የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጣም እንቅፋት በመሆን ክልሉ ዳግም ወደ ግጭት እና ጦርነት እንዲገባ ሲገፋፉ ተስተውለዋል::
ከሁሉ በከፋ መልኩ ክልሉ ያለውን በጀት ለልማት እንዳያውለው ከ200ሺ በላይ ሠራዊት በማከማቸትና እና በመቀለብ በወር እስከ 8 ቢሊዮን ብር በመገፍገፍ ትግራይ በድህነት አረንቋ ውስጥ እንድትቆይ የተደረገበት መንገድ ከተስዋሉ ችግሮች ውስጥ አንዱ ነው::
ስለዚህም እነዚህ የተሳሳቱ አካሄዶች ፈር ሊይዙ ይገባል:: የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ፍላጎት ከተቀረው ወገኑ ጋር በሰላም፤ በእኩልነትና በፍትሃዊነት መኖር ነው:: የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ጠላት ድህነት ነው:: የትግራይ ሕዝብ ምኞት ኃላቀርነትና ብልሹ አሠራሮችን ማስወገድ ነው:: የትግራይ ሕዝብ ዋነኛ ምኞት ንጹህ የመጠጥ ውሃ፤ የኤሌትሪክ አቅርቦት፤መንገድና መሰል የመሰረተ ልማቶች መስፋፋት ነው:: ሆኖም ከእነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቱ በተቃራኒ እኔ አውቅልሃለሁ በሚል የትላንቱን ጭቆናና እና ኋላቀርነት ማስቀጠል የሚፈልጉ ወገኖችን መታገል የዘመኑ ጥያቄ ሆኗል::
ይህ አምድ በተለያዩ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዜጎች ነፃ ሀሳባቸውን የሚሰጡበት ነው።በዓምዱ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የዝግጅት ክፍሉን አቋም አያመለክቱም።
በአሊሴሮ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም