
በሀገራት መካከል የኢኮኖሚ ውሕደትን በማበረታታት ቀጣናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰብን ለመፍጠር ወሳኝ ሚና እንዳለው የተነገረለት፤ የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ የ (ኮሜሳ) ኤግዚቢሽን ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በኤግዚቢሽኑ ከሀገር ውስጥ ፤ ከምስራቅ እና ከደቡብ አፍሪካ ሀገራት ሴት አምራቾች በስፋት ተሳትፈዋል።
ኤግዚቢሽኑን ከተሳተፉ መካከል ዲዛይነር ነቢያት ወ/ሠንበት አንዷ ነች። የነጋዴ ልጅ ናትና የተማረች ነጋዴ የመሆን ትልቅ ፍላጎት ይዛ ነው። ሴት ልጅ ፈጣን እና ጎበዝ መሆን ይጠበቅባታል ትላለች። ከሕዝብ አስተዳደር በተጨማሪ ፋሽን እና ዲዛይን በመማር ነቢ የባህል ልብስ ዲዛይን የተሰኘ ካምፓኒ አቋቁማለች።
የዲዛይን ካምፓኒው መስራች እና ባለቤት ነች ፤ በጥልፍ፣ በስፌት እና በሂሳብ ሥራ በቋሚነት 15 ሠራተኞችን ቀጥራ ታሠራለች። የተለያዩ ዲዛይኖችን በማውጣት የሙሽራ እና ሌሎችም ቅንጡ የባህል ልብሶችን እየሠራች ለገበያ ታቀርባለች ።
የሴት ነጋዴዎች አባል በመሆን የምስራቅ አፍሪካ እና የደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ (ኮሜሳን) በመቀላቀል፤ ኢትዮጵያን ወክላ በራሺያ እና በማዳጋስካር በተዘጋጁ ኤግዚቢሸኖች ላይ ተሳትፋለች። ሰሞኑን ኢትዮጵያ ላይ በተካሔደው የኮሜሳ ኤግዚቢሽን ላይም ሥራዋን ይዛ ቀርባለች ፤ በእግዚቢሽኑ ላይ መሳተፏ ከፍተኛ መነሳሳት እንደፈጠረባት ትናገራለች።
እግዚቢሽኑ የአባል ሀገራት ነጋዴዎችን እና አምራቾችን ማግኘት አስችሏታል ፤ በየሀገሩ ኢትዮጵያን ወክላ በተሳተፈችባቸው ኤግዚቢሽኖች ትላልቅ ትምህርቶች ማግኘቷን ትናገራለች። ከሀር ትል የሚሠራ ጨርቅ ማምረት በሚያስችል ኢንቨስትመንት ላይ መሳተፍ ትፈልጋለች ።
ለዚህ ግን ማሽን ከውጪ ገዝቶ ለማስገባት የተጣለው ቀረጥ እና የማምረቻ ቦታ እጦት ፈተና እንደሆነባት፤ መንግሥት የሀገር ውስጥ ሴት አምራቾችን አቅም ለመገንባት ድጋፍ ካላደረገ ያሰቡበት ለመድረስ አዳጋች እንደሚሆንባቸው አሁናዊ ተጨባጭ እውነታዎች ማሳያ እንደሚሆኑ ትናገራለች።
ኤግዚቢሽን በተሳተፈችባቸው ሀገሮች የሴት አምራቾች እውቀት አነስተኛ ቢሆንም ፤ በራስ መተማመናቸው እና ገበያ ለማግኘት የሚያደርጉት ጥረት ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲነፃፀር ከፍ ያለ ነው። ይህ የሆነው እርስ በእርሳቸው ስለሚደጋገፉ እና የመንግሥትም ድጋፍ ከፍተኛ በመሆኑ ነው ትላለች።
ሌላኛዋ የኤግዚብሽኑ ተሳታፊ ኤደን ሃይሉ ትባላለች። በአዲስ አበባ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በማኑፋክቸሪንግ ኢንጂነሪንግ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች። የቆዳ ውጤቶችን ማምረት ከመጀመሯ በፊት ቆዳ እና የቆዳ ምርቶች ልማት ኢንስቲትዩት ውስጥ ተቀጥራ ሠርታለች። በዛም ተማሪዎችን የማሠልጠ እና ኢንዱስትሪውን የመደገፍ ሥራን አከናውናለች።
በተለይ ጫማ የሚሠሩ ፋብሪካዎችን ማማከር እና በቆዳ ኢንዱስትሪ የሚማሩ ተማሪዎችን የማስተማር ልምድ አላት። ህንድ ሄዳ ፋሽን ላይ በማተኮር ሁለተኛ ዲግሪዋን አግኝታለች ፤ ባለቤቷም ተመሳሳይ ፍላጎት ስለነበረው ተቀጥራ መሥራቷን አቁማ፤ ከባለቤቷ ጋር በመሆን ሃንፋላ ሌዘር የተባለ ድርጅት አቋቁመው ሥራ ከጀመሩ አራት ዓመታትን አስቆጥረዋል።
ለ10 ሰው የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል ፤ ይህም ሆኖ ውስን ገበያ ይዞ የመሥሪያ ቤት እና የሱቅ ኪራይ ወጪ መሸፈን እና የሠራተኛ ደሞዝ መክፈል ከፍተኛ ፈተና እንደሆነባቸው ትናገራለች። ቆዳን የማምረት ሂደት ከባድ በመሆኑ ሽጦ ማትረፍ እና ገበያው ላይ መቆየት ትልቅ አቅም እንደሚጠይቅ ታስረዳለች።
ሥራው የሚፈልገው ጥረት እና ገበያ ለማግኘት ያለው የዋጋ ውድድር ተመጣጣኝ አለመሆኑን ፤ በተለይ ግብዓቶች በአብዛኛው ሀገር ውስጥ አለመኖራቸው እና በየጊዜው ዋጋቸው የሚጨምር መሆኑ የዘርፉ ፈተና ነው ስትል ገልፃለች።
“ያለድጋፍ ጀማሪ የቆዳ አምራችነት አዳጋች ነው። በሌዘር ኢንዱስትሪ ለመሳተፍ ሰብሮ ለመውጣት ከፍተኛ አቅም ይፈልጋል። የተወሰኑ የግብዓት አስመጪዎች መኖራቸውን በመጠቆም፤ አስመጪዎቹ እንደፈለጉ ዋጋውን የሚቀያይሩ በመሆናቸው ቋሚ ገበያ ለማግኘት አዳጋች ሆኗል” ብላለች።
እንደርሷ እምነት ፤ በቆዳ ኢንዱስትሪ በመንግሥት በኩል የሚሰጡ ሥልጠናዎች አምራቾች ከዜሮ ጀምረው ምን መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳውቁ ናቸው። ሆኖም የተማሩትን ለመተግበር እና ኢንዱስትሪውን ለማስፋት፤ በተለይ የሀገር ውስጥ ምርት ያለበትን የውበት እና የጥራት ውስንነት ለማቃለል፤ የግብዓት እጥረትን በተመለከተ አስቦ ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችል ሥርዓት መፍጠር ይገባል።
ከችግሩ ተነስቶ መፍትሔ ማምጣት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መሥራት ይገባል። ችግሮችን ለዘለቄታው ለመፍታት ድጋፍ የሚፈልጉ ኢንቨስትመንቶች ችግሮቻቸው ምንድን ነው ? ብሎ ለይቶ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል ትላለች።
ለቆዳ ምርቶች ቆዳውን ማስዋቢያ ኬሚካሎች፣ ዚፕ እና ቁልፍን የመሳሰሉ ግብዓቶች እዚሁ ሀገር የሚመረትበትን ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ብዙ እሴት የሚጨምርባቸው የቆዳ ቦርሳም ሆነ ጫማ እንዲሁም ጃኬቶችን የመሳሰሉ ምርቶችን ለማምረት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን የሚያስገቡ አስመጪዎችን በተለያየ መልኩ ማበረታታት እንደሚገባ ታነሳለች ።
ኤግዚቢሽኖች ተሳታፊዎች የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ከማስቻል ባለፈ ፤ በሌሎች ሀገሮች ገበያ ለማግኘት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል የምትለው ኤደን ፤ በምስራቅ አፍሪካ በብራንድ ደረጃ ተፅዕኖ ለመፍጠር ድርጅታቸው ሃንፋላ ሌዘር አቅዶ እየሠራ መሆኑን ትናገራለች።
ምሕረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም