ቴክኖሎጂን – ከህልም ወደ ተጨባጭ እውነት

ከ2010ሩ ሀገራዊ ለውጥ ማግስት ኢትዮጵያ ልማቷንም፤ ሉዓላዊነቷንም ልታረጋግጥ ትችል ዘንድ አቅም ብላ ከለየቻቸው መስኮች መካከል አንዱ ዲጂታላይዜሽን ነው፡፡ ይሄን ተከትሎም ኢትዮጵያ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ”ን ቀርፃና አፅድቃ ወደ ሥራ ገብታለች፡፡ ይሄ ደግሞ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድሎችን በመጠቀም ፈጠራ የታከለበትና በእውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚ ለመገንባት የሚያስችል፤ የዲጂታል አካታችነትንም የሚያረጋገጥ እንዲሆን ተደርጎ እየተተገበረ ያለ ነው፡፡

ይሄ የዲጂታላይዜሽን ጉዞ ደግሞ ዘርፈ ብዙ ፋይዳዎች ያሉት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ለምሳሌ፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውን ብንመለከት፤ የዲጂታላይዜሽን እውን መሆንን ተከትሎ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ከፍ ያለ አበርክቶው እየተገለጠ ይገኛል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ፤ ባለፉት 9 ወራት በዲጂታል መንገዶች 7 ነጥብ 73 ቢሊዮን ብር መቆጠቡ፤ 26 ነጥብ 77 ቢሊዮን ብር በዲጂታል በኩል ብድር መሰጠቱ፣ እና የ12 ነጥብ 51 ትሪሊዮን ብር ግብይት መከናወኑ አብነት ነው፡፡

ከዚህ ጋር አብሮ ሊታይ የሚችለው፤ ዲጂታላይዜሽን በመንግሥት አሠራርና አገልግሎት ላይ ግልጽነትን፣ ቅልጥፍናና ውጤታማነትን የሚያጎናጽፍ መሆኑ ነው፡፡ በዚህ ረገድ መንግሥት የወሰዳቸው ርምጃዎች አበረታች ውጤት የታየባቸው ሲሆን፤ ሙስናን፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን፣ የሀብት ስወራና ግብር ማጭበርበርን የመሳሰሉ ጉዳዮችን መቀነስ አስችሏል፡፡ በቅርቡ ተግባራዊ የሆነው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የዚህ አብነት ነው፡፡

በሌላ በኩል፣ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና የፈጠራ አቅምን ከማጎልበት አኳያ እየተጫወተ ያለው ከፍ ያለ ሚና ጉልቶ የሚጠቀስ ነው፡፡ በዚህ በተለይ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት እድገት ጋር ተያይዞ፤ ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ከተቀባይነት ወደ ራስን መቻል እየተሸጋገረች፤ አልፎም ለሌሎች መትረፍ የምትችልበትን አቅም እየገነባች ያለችበትን ግስጋሴ ፈጥሮላታል፡፡

ምክንያቱም፣ በእነዚህ ስድስት ዓመታት ጉዞ ብቻ፤ በርካታ ወጣቶች ቴክኖሎጂን ተዋውቀዋል ብቻ ሳይሆን ያወቁትን ወደ ተግባር እየቀየሩ ይገኛሉ፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያ ዛሬ በግብርናው፣ በጤናው፣ በምህንድስናው፣ በሕዋ ሳይንሱ፣ በድሮን እና በሮቦቲክስ ቴክኖሎጂው ጭምር ከፍ ያሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ያሉት፡፡

ዛሬ ላይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ሳይሰደዱ በሀገራቸው ሆነው የውጭ ሀገር ሥራዎች ላይ መሳተፍ ችለዋል፡፡ ቴክኖሎጂዎችን ቀድተውና አላምደው መሥራትን ቀላል ኃላፊነት አድርገዋል፡፡ ዓመታትን አገልግሎት መስጠት ያቆሙ የጦር አውሮፕላኖችን ሳይቀር ሕይወት ዘርተው ወደ ሥራ እንዲገቡ አድርገዋል፡፡

ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ሶፍትዌር ዲዛይኖችን ነድፈው እውን አድርገዋል፡፡ ከሚሳዬል እስከ ድሮን የዘለቀ ፈጠራን የራሳቸው አድርገው ይዘው ወጥተዋል፡፡ በሳይበር ቴክኖሎጂ እና በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዘውም ኢትዮጵያን የመጠበቅ፤ ኢትዮጵያን የማላ ቅ፤ ኢትዮጵያን የቴክኖሎ ጂ ማዕከል የማድረግ መንገድን ጀምረዋል፡፡

በተለይ ከሰው ሠራሽ አስተውሎት ጋር ተያይዞ እንደ ሀገር የተጀመሩ ሥራዎች ከፍ ያለ እምርታ የታየባቸው ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ውጤቶችን በግብርናው፣ በጤናው፣ በደህንነትና በሌሎችም መስኮች ጥቅም በሚሰጥ መልኩ በራሷ አቅም ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡

ከሰሞኑ የታየው የድሮን መብራት ትርዒትም፣ የዚሁ የዲጂታላይዜሽን ግስጋሴው፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎት ከፍታው ውጤት ነው፡፡ ምክንያቱም በዚህ የአዲስ አበባን ሰማይ አድምቀው ባመሹት እና በሺዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች የተሳተፉበት ትርዒት፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እያዘዙ የተከናወነ አይደለም፡፡ በሰው ሠራሽ አስተውሎት ታግዞ አስደማሚ እይታን መፍጠር የተቻለበት እንጂ፡፡

እነዚህ እና መሰል የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 መንገድ ውጤቶች ሲታዩ፤ ኢትዮጵያ ትናንት ሕልም የሆነባት ቴክኖሎጂ ዛሬ ላይ ወደሚጨበጥ እውነት እየተሸጋገረ መሆኑን አስረጂዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በዚህ እና በሌሎችም መልኩ እየተገለጠ ያለው የኢትዮጵያ የዲጂታል ጉዞ፤ የሰው ሠራሽ አስተውሎትም መንገድ ታዲያ፤ በቀጣይ የበለጠ ልቆ ሊገለጥ፤ ከራስ አልፎ ለሌሎች የመትረፍ እና ኢትዮጵያ በሌላ ገጽ ለአፍሪካውያን የመቻል አቅም ምሳሌ የምትሆንበትን ልዕልና እንዲያጎናጽፍ እየተሠራ ይገኛል፡፡

ይሄ እየተሠራባቸው ካሉ ጉዳዮች አንዱ፣ የአምስት ሚሊዮን ኮደሮች ኢኒሼቲቭ ሲሆን፤ ይሄ ኢኒሼቲቭ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች የዲጂታል ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ከዚህ በተጓዳኝ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ተቋም እና ሌሎች ተቋማት በተለይም እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሉት በዚህ ላይ በትኩረት እየሠሩ ይገኛል፡፡ በመሆኑም ሕልም የነበረውን ቴክኖሎጂ ወደ ተጨባጭ እውነት የተቀየረበትን ጉዞ የበለጠ ማላቅ እና ኢትዮጵያን የዘርፉ ማዕከል የማድረግ ሥራው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል፡፡

አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You