
አዲስ አበባ፡– ከ2010 ዓ.ም ጅምሮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለመገንባት 3 ቢሊዮን 683 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ። 380 ትምህርት ቤቶች ጉዳት እንደረሰባቸው ገልጸዋል።
በክልሉ ትምህርት ቢሮ የሥርዓተ ትምህርት እና ትምህርት ተቋማት ምክትል ኃላፊ አቶ መሐመድ ኡሱማን ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በክልሉ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት 120 ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ሲወድሙ ፤ 140 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በትምህርት ቤቶቹ ላይ የደረሰውን ጉዳት ተከትሎ ለ112 ሺህ 945 ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው መፈናቀላቸውን አመልክተው ፤ ችግሩን ለመፍታት በትላልቅ ዛፎች ጥላ ስር እና በአነስተኛ ዳሶች ውስጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል ።
የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዳይስተጓጎል ሰፊ ጥረቶች እያደረገ እንደሚገኝ ፤ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን በመሥራት 348 ሺህ ተማሪዎችን ለመቀበል በተሠሩ ሥራዎች 327 ሺህ 167 ተማሪዎችን መቀበል መቻሉን አመልክተዋል ። በዚህም በአሁኑ ወቅት በ625 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በ93 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማር ሂደቱ መቀጠሉን አስታውቀዋል ።
የጥራት ችግር ለትምህርት ስብራት ምክንያት መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው ፤ ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ትምህርት ባለሙያዎችን በማስተባበር ሰፊ ሥራዎች በመሥራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ከዚህ ውስጥ ለመምህራን የክህሎት ማሻሻያ ጨምሮ በሁሉም ትምህርት ዓይነቶች የአቅም ማጠናከሪያ ሥልጠናዎች እየተሰጠ እንደሚገኝ አመልክተዋል። የሠለጠኑ መምህራን በበኩላቸው ማጠናከሪያ (ቲቶሪያል) ክፍሎችን እንደሚሰጡ ገልጸዋል።
የ6ኛ ክፍል ፈተና እንደ ክልል መስጠት አለመጀመሩን ያመለከቱት ምክትል ሃላፊው ፤ በዚህ ዓመት ፈተናውን ከ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ጋር አብሮ ለመስጠት ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል ። ይህንን ለማሳካት ሀገር አቀፍ ፈተና በሚሰጥባቸው ቦታዎች ሁሉ ከመደበኛው ትምህርት ጎን ለጎን የማጠናከሪያ ትምህርት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ህብረተሰቡን እና ባለሀብቶችን በማስተባበር ሰፊ ሥራዎች እየተሠሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪም የመማሪያ የመጻህፍት እና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ተደራሽነትን ማረጋገጥ ፤ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ማስጠበቅ ቢሮው በትኩረት ከሚሠራባቸው ሥራዎች ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሱ መሆናቸውንም አቶ መሐመድ ኡሱማን አስታውቀዋል።
የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል እና ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ግንባታ ለማሳለጥ
ገመቹ ከድር
አዲስ ዘመን ሰኞ ግንቦት 11 ቀን 2017 ዓ.ም