
በቱርክ የተካሄደው የሩሲያና የዩክሬን ባለሥልጣናት ውይይት ጉልህ የሆነ ውጤት ሳያስገኝ ተጠናቋል። ከሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት በተጨማሪ የአሜሪካ ተወካዮችም ኢስታንቡል ተገኝተው ነበር። የሩሲያና የዩክሬን ባለሥልጣናት ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ ከሦስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። የሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ከሦስት ዓመታት በፊት ከተጀመረ ወዲህ የሁለቱን ሀገራት ባለሥልጣናት ፊት ለፊት በማገናኘት ለማደራደር የተደረጉ ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል። የሁለቱን ሀገራት ውይይት ያስተባበሩት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳንና ሌሎች ባለሥልጣናት ናቸው። የሀገራቱ ተወካዮች ለሁለት ሰዓታት የዘለቀውን ውይይት የጀመሩት እጅ ለእጅ ሳይጨባበጡ ነው።
የባለሥልጣናቱ ውይይት በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ ጉልህ የሆነ ውጤት ያስገኛል ተብሎ የተጠበቀ አልነበረም። ውይይቱ ትልቅ ውጤት ባይጠበቅበትም በከባድ ጦርነት ውስጥ በሚገኙት በሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት መካከል የፊት ለፊት ግንኙነት መጀመሩ ግን ትልቅ ርምጃ መሆኑ ተገልጿል። የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን ልዑካኑ ወደ ሰላም ወይም ወደ ተጨማሪ ሞትና ውድመት የሚወስዱ ሁለት አማራጮች ብቻ እንዳሏቸው አሳስበው ነበር። የተኩስ ማቆም ስምምነት ላይ መድረስ ወሳኝ ርምጃ እንደሚሆንና ለሁሉም ወገን ጥቅም እንዳለው በመግለፅ፣ ሀገራቱ ተኩስ ለማቆም እንዲስማሙ ጠይቀዋል።
ሁለቱ ሀገራት ፊት ለፊት እንዲገናኙ ሃሳቡን ያመነጩት የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ናቸው። ይሁን እንጂ ፑቲን ለንግግር ቱርክ ሳይገኙ ቀርተዋል። የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ወደ ቱርክ አቅንተው ከሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ጋር እንደተነጋገሩ ታውቋል።
ፑቲን ለውይይት ኢስታንቡል አለመገኘታቸው ሩሲያ ተኩስ ለማቆምም ሆነ ለዘላቂ የሰላም ስምምነት ፍላጎት እንደሌላት ማሳያ እንደሆነ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ተናግረዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሩሲያን ቸልተኝነት እንዲገነዘብና በተለይ አሜሪካ በሩሲያ ላይ ጫና ማሳደሯን መቀጠል እንዳለባትም አሳስበዋል።
በውይይቱ እንደተገኘ ውጤት ሊቆጠር የሚችለው ሁለቱ ሀገራት የእስረኞች ልውውጥ ለማድረግ መስማማታቸው ነው። ሀገራቱ እያንዳንዳቸው አንድ ሺህ እስረኞችን ለመለዋወጥ የተስማሙ ሲሆን፣ ይህ ከጦርነቱ መጀመር በኋላ ትልቁ የእስረኞች ልውውጥ እንደሆነ ተገልጿል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ በኢስታንቡሉ ውይይት ብዙም ተስፋ እንደሌላቸው ተናግረው ነበር። ሩቢዮ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ‹‹ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ፑቲን በቀጥታ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እስካልተወያዩ ድረስ እዚህ ለውጥ የምናገኝ አይመስለኝም›› ብለዋል።
ሩቢዮ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከፈረንሳይ እና ከጀርመን አመራሮች ጋር በኢስታንቡል ተወያይተዋል። የዩክሬን አጋር የሆኑ ምዕራባውያን ሀገራት ሩሲያ ለተኩስ አቁም ስምምነት ዝግጁ እንድትሆን እየጠየቁ ይገኛሉ። ከዚህ በተጨማሪም ሀገራቱ ለዩክሬን ወታደራዊ ድጋፍ መስጠት እንደሚቀጥሉ እና በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ እንደሚጥሉም አስታውቀዋል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሰሞኑን በመካከለኛው ምስራቅ በጉብኝት ላይ ሳሉ፣ እርሳቸው እና ፑቲን በአካል እስኪገናኙ ድረስ በሰላማዊ ንግግሮቹ ላይ ከፍተኛ መሻሻል የማይታሰብ መሆኑንና ከፕሬዚዳንት ፑቲን ጋር በተቻለ ፍጥነት መገናኘት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
‹‹እኔና ፑቲን እስክንገናኝ ድረስ ምንም ነገር አይከሰትም። እኔ ከሌለሁ አይሄድም። እናም እኔ እና እሱ እስክንገናኝ ድረስ ተወደደም ተጠላም ምንም ነገር ይከሰታል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች እየሞቱ ስለሆነ መፍትሄ ማግኘት አለብን›› ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪም ፕሬዚዳንቱ በኢስታንቡሉ ውይይት ላይ ለመገኘት ወደ ቱርክ ሊያቀኑ እንደሚችሉ ቢጠቁሙም በኋላ ግን የመካከለኛው ምስራቅ ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ ዋሺንግተን እንደሚመለሱ ተናግረዋል።
ከሦስት ዓመታት በላይ የዘለቀውን ደም አፋሳሹንና አውዳሚውን የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ለማስቆም የተሞከሩ ጥረቶች እስካሁን ፍሬ ሊያፈሩ አልቻሉም። ‹‹ወደ ዋይት ሃውስ በተመለስኩ በመጀመሪያው ቀን ጦርነቱን አስቆመዋለሁ›› ብለው ቃል ገብተው የነበሩት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ስልጣን በያዙ 120 ቀናት ቢሆናቸውም ጦርነቱን ማስቆም አልሆላቸውም፡፡
በእርግጥ ፕሬዚዳንቱ ጦርነቱን ለማስቆም ብዙ ጥረቶችን ማድረጋቸው አይካድም። ተፋላሚዎቹ ተኩስ የማቆም እንዲሁም ዘላቂ የሰላም ስምምነት እንዲፈራሙ ምቹ ሁኔታዎችን የሚፈጥሩ ውይይቶች እንዲዘጋጁ አድርገዋል። የ30 ቀናት ተኩስ የማቆም እቅድም ይፋ አድርገዋል። የ 30 ቀናት የተኩስ ማቆም እቅዱ ባለፈው መጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ የአሜሪካና የዩክሬን ተወካዮች በሳዑዲ አረቢያ ካደረጉት ውይይት በኋላ በአሜሪካ ይፋ የተደረገ እቅድ ነው።
እቅዱ አሜሪካ አቋርጣው የነበረውን የወታደራዊ ድጋፍ አቅርቦት እና የስለላና ደህንነት መረጃዎችን ለዩክሬን ማጋራቷን የሚያስቀጥል፣ አሜሪካን ከዩክሬን ውድ ማዕድናት ተጠቃሚ የሚያደርገው ስምምነት እንዲፈረም የሚያፋጥን፣ የሰላማዊ ሰዎችን ከእስር መለቀቅና የእስረኞችን ልውውጥ የሚያመቻች እንዲሁም ሁለቱም ወገኖች ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ ለመድረስ ለሚደረገው ድርድር የሚወክሏቸውን ተደራዳሪዎች እንዲሰይሙ የሚያስችል ቃልኪዳን ነው።
ይህ እቅድ በዩክሬን በኩል ተቀባይነት ሰያገኝ፣ ሩሲያ እቅዱን ለመቀበል ብዙ ቅድመ ሁኔታዎችን አቅርባ ነበር። አሜሪካም ‹‹ስለእቅዱ ዝርዝር ማብራሪያ እፈልጋለሁ›› ወዳለችው ሞስኮ ልካ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እቅዱን እንዲቀበሉ ለማግባባት ሞክራለች።
ታዲያ ጦርነቱን ለማስቆም የተሞከሩ ጥረቶች ይህ ነው የሚባል የረባ ለውጥ አለማምጣታቸው የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ሳያበሳጭ አልቀረም። የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ማርኮ ሩቢዮ በሁለቱ ሀገራት ግጭት ጉዳይ በፍጥነት ስምምነት ላይ መደረስ እንዳለበት ደጋግመው ተናግረዋል። ‹‹አለበለዚያ ግን ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ያህል ጊዜ ማሳለፍ እንዳለብን መወሰን ይኖርባቸዋል›› ብለው ነበር። ከዚህ በተጨማሪም የአሜሪካ የሰላም ጥረት ፍሬ የማያፈራ ከሆነ ሀገራቸው ከተኩስ አቁምና ከሰላም ስምምነት አደራዳሪነት ሚናዋ ልትወጣ እንደምትችል ተናግረውም ነበር፡፡
ፕሬዚዳንት ትራምፕም አሜሪካ ከሩሲያ-ዩክሬን አደራዳሪነት ሚናዋ ልትወጣ እንደምትችል ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል። ሞስኮ ወይም ኪዬቭ ተኩስ የማቆሙን ጥረት አስቸጋሪ የሚያደርጉት ከሆነ ሀገራቸው ጦርነቱን ለማስቆም የምታደርገውን ጥረት ልታቋርጥ እንደምትችል ለጋዜጠኞች ተናግረው ነበር።
ከፑቲን ጋር ተገናኝተው ካልተወያዩ በስተቀር በጦርነቱ ጉዳይ ዓለም የረባ ለውጥ እንዳይጠብቅ ያሳሰቡበት ፕሬዚዳንት ትራምፕ፣ ከሩሲያው አቻቸው ጋር ፊት ለፊት መገናኘታቸው ምን ዓይነት የተለየ ውጤት ሊፈጥር እና በጦርነቱ ላይ ወሳኝ የተባለ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል ለብዙዎች ግልጽ አይደለም።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን እሁድ ግንቦት 10 ቀን 2017 ዓ.ም