
አዲስ አበባ፡– ኢትዮጵያ የክትትል እና ምዘና ሥርዓቷን አጠናክራ በመቀጠል ለአጀንዳ 2063 ስኬት የድርሻዋን ትወጣለች ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ አስታወቁ።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ጥሩማር አባተ የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማኅበር (Africa evaluation Excellence) የተመሠረተበትን 25ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ ለተከታታይ ሦስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየው ኮንፍረንስ ትናንት ሲያጠናቅቅ እንዳሉት፤ የምዘና ሥርዓት ቴክኒካል ብቻ ሳይሆን መረጃ ላይ የተመሠረተ ፖሊሲን ለማውጣትም ሆነ ውሳኔን ለመስጠት በእጅጉ የሚረዳ፤ ለመልካም አስተዳደር፣ ለሁሉን አቀፍ እድገትና ቀጣይነት ያለው ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ባለፉት ሦስት ቀናት በምዝና እና ክትትል ዘርፍ ሲካሄድ የቆየው አሕጉር አቀፍ ኮንፍረንስም የእውቀት እና የልምድ ልውውጥ የተደረገበት፣ አዳዲስ ሃሳቦች የፈለቁበት እንደሆነ ጠቅሰዋል። መድረኩ የሀገሪቱን ችግሮች መፍታት የሚያስችል የልምድ እና የእውቀት ሽግግር የተደረገበት እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ መረጃን መሠረት ያደረገ ፖሊሲን ለመቅረጽና ውሳኔን ለመስጠት በሚያስችል መልኩ የክትትል እና ምዘና ሥርዓቷን አጠናክራ የምትቀጥል ስለመሆኑ በመድረኩ ተናግረዋል።
የአፍሪካ ኅብረት ላስቀመጠው አጀንዳ 2063 እና ለዘላቂ የልማት ግብ 2030 ስኬቶች ሰላም የሰፈነባት፣ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ፣ መቀራረብና እና መተባበር የሚታይባት አፍሪካን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት ኢትዮጵያ የድርሻዋን የምትወጣ መሆኑንም ገልጸዋል። የምዘና ሥርዓትን መከተል ምን መሥራት እንዳለብን እና እንደሌለብን የሚያመላክት እና ማንም ወደ ኋላ እንዳይቀር የሚያደርግ ነው ብለዋል።
ይህ መድረክ የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማኅበር 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል የሚከበርበት ብቻ ሳይሆን አፍሪካ ብቁ አመራሮችና ሀገር በቀል ሙያተኞችን እያበቃች መሆኑም የሚታይበት እንደሆነ አስረድተዋል።
የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማኅበር የምዘና ሥርዓት በአፍሪካ እንዲስፋፋ ያደረገ እና እውነተኛ አሠራር ጎልቶ እንዲወጣ ያስቻለ፣ ልዩነትን ያከበረ፣ የሕዝቦች ፍላጎትና ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ያስቻለ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት በቀጣይም ሥነ ምግባራዊና ሙያዊ ተግባራትን በመፈጸም፣ የቴክኒካል አጋርነት በመፍጠር፣ የተቋማትን ግንኙነት በማጠናከር እና አካባቢያዊ ግንኙነትን በማጠናከር የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማኅበር አሠራርን የሚደግፍ መሆኑን ተናግረዋል። የአፍሪካን ራዕይ ለማሳካት ሁሉም ባለድርሻ መማር፤ የተማረውን እንደየአካባቢው ሁኔታ መተርጎም፣ እና በእውቀት ላይ ተመሥርቶ መምራት ይገባዋል ብለዋል።
የአፍሪካ ምዘና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሚሼል ዱዮድራጎ በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ባደረጉት ንግግር፤ ከአርባ በላይ የሚሆኑ ተቋማት የቋንቋ ልዩነት ሳይገድባቸው የምዘና ሥርዓትን በመተግበሩ ሂደት እርስ በርስ በመደጋገፍ፣ በመነጋገርና የመፍትሔ ሃሳቦችን በመለዋወጥ የሀገሪቱን አንድነት የማጠናከር ሥራ ሠርተዋል።
የምዘና ሥርዓት ትግበራው አሕጉር አቀፍ ሁኔታዎችን ከግምት ያስገባ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በቀጣይም የምናስባትን አፍሪካ እውን ለማድረግ የምዘና ሥርዓታችን ከአሕጉሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንዲጣጣም ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍና በሁሉም ደረጃ እንዴት የምዘና ሥርዓትን ተግባራዊ ማድረግ ይቻላል? እንዴት ተቋማትን መርዳት ይቻላል? የሚለውን አስቀድሞ ማሰብ እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
አፍሪካውያን የጋራ እቅዳችን የሆነውን አጀንዳ 2063 ተግባራዊ ለማድረግ የምዘና እና ክትትል ሥራ ከፍተኛ ድጋፍ የሚያደርግ መሆኑን አመልክተው፤ የሰሞኑ መድረክም የበለፀገች፣ ሰላሟ እና አንድነቷ የተጠበቀ አፍሪካን እውን ለማድረግ ዩኒየኑ ያስቀመጣቸውን ግቦች ለማሳካት በሚረዳ መልኩ የልምድ ልውውጥ እና የእውቀት ሽግግር የተደረገበት፤ ወደፊት ለምንሠራው ሥራ ጠቃሚ ግብዓት የተገኘበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ኢያሱ መሰለ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም