
አዲስ አበባ፡– ከ60 በላይ ኩባንያዎች ጋር በመስማማት ለተመራቂዎች የሥራ ዕድል ማመቻቸቱን የአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ገለፀ፡፡
የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች የሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል ኃላፊ አየለ ማንደፍሮ (ዶ/ር) ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳሉት፤ ዩኒቨርሲቲው በዋናነት መደበኛ ትምህርት ከማስተማር ባሻገር ከአንደኛ ዓመት እስከ ምረቃ የሚገኙ ተማሪዎች በቂ ዕውቀትና ክህሎት እንዲያዳብሩ የተለያዩ ሥልጠናዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡
ተማሪዎች ተመርቀው ከመውጣታቸው በፊት ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር እንዲገናኙ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ማዕከሉ ነው ያሉት ዶክተሩ፤ ማዕከሉ ከኩባንያዎች ባደረገው ውይይትም ከ60 በላይ ኩባንያዎች ተመራቂዎችን ለመቅጠር መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜም የዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር (ሊንኬጅ) እና የተማሪዎች ሙያ ማበልፀጊያ ማዕከል ባዘጋጁት መርሐ ግብር ላይ በመገኘትም 45 ኩባንያዎች የሥራ ቅጥር ቃለ መጠይቅ እያደረጉ ነው ሲሉ ገልፀዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው 900 ገደማ ተመራቂዎች እንዳሉት በመግለፅ፤ ከተመራቂዎች መካከል 19 ቡድኖች የራሳቸው የፈጠራ ክህሎት ያላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከቀጣሪ ኩባንያዎች መካከል በዩኒቨርሲቲው የተመረቁ መሆናቸውን በመጥቀስ፤ ቀጣሪዎች ከተመራቂዎች ጋር ትስስር ሲፈጥሩ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
የሥራ ዕድል ፈጠራው ዋና ዓላማ ተማሪዎች ግቢውን ለቀው ከመውጣታቸው በፊት ምን መሥራት እንደሚኖርባቸው ከወዲሁ ዝግጁ ሆነው በሥራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል ኩባንያዎች ዩኒቨርሲቲው ድረስ መጥተው የራሳቸው መመዘኛ በመጠቀም ቅጥር መፈጸማቸው አቅም ያላቸውን ሠራተኞች ለማግኘት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርላቸው አመልክተዋል፡፡
ተመራቂ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው የሠሯቸው የፈጠራ ሥራዎች ለመቀጠር ብቻ ከመዘጋጀት ይልቅ አምራችነታቸውን የሚያሳዩ ናቸው ያሉት አየለ (ዶ/ር)፤ ዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎችን ከቀጣሪ ኩባንያዎች ጋር በማገናኘት ዕውቀታቸው ወደ ገንዘብ እንዲለውጡ እያደረግን ነው ብለዋል፡፡
ሔርሞን ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 12 ቀን 2017 ዓ.ም